1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2011 ሒደት አጭር ቅኝት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2004

የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ሲግም-የሠረቀዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ፣ የጃፓኖችን የዕዉቀት-ሥልጣኔ ምጥቀት በተፈጥሮ ክርን አስደቁሶ፣ ዓለምን ለሰልፍ እንዳሳደመ፣ በሞስኮዎች ሰልፍ ሊጠልቅ ሳምንታት ቀሩት

https://p.dw.com/p/S1gY
ቱኒዚያምስል picture-alliance/dpa


12 12 11

ለፍልስጤሞች፥የነፃነት-ጥያቄያቸዉ ለስልሳ-አራተኛ ዓመት የመዳፈኑ-ፅልመት ነዉ።ለዘመናት የደደረዉ የዓረብ ፖለቲካዊ ሥርዓት ግን ሠላማዊ-ትግልን ከጦርነት በቀየጠ ማዕበል መጥለቅለቁ እርግጥ ነዉ። ለአፍቃኖች በቦምብ-ጥይት ያረሩበትን ዘመን-ባንድ ከመጨመር ሌላ-ዘንድሮም አምና ነዉ። ሐያሉ ዓለም ቢን ላደንን እና ቃዛፊን የመግደል-ማስገደሉ ደስታ፣ በሥልተ-ምርቱ ንቅዘት-ክሰረት መጨናጎሉ ግን ሐቅ ነዉ።የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ሲግም-የሠረቀዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ፣ የጃፓኖችን የዕዉቀት-ሥልጣኔ ምጥቀት በተፈጥሮ ክርን አስደቁሶ፣ ዓለምን ለሰልፍ እንዳሳደመ፣ በሞስኮዎች ሰልፍ ሊጠልቅ ሳምንታት ቀሩት።ከሰሐራ-በስተደቡብ ያሉትን የአፍሪቃ ሐገራትና አዉሮጳን ትተን በተቀረዉ ዓለም አመቱን የተከናወኑትን አበይት ፖለቲካዊ ሁነቶች ባጭሩ እንቃኛለን።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ለብራዚሎች የዛሬዉ አርጌ ዓመት የአዲስነቱ ብርቀት ገፊ ነበር።የሪዮ ዲ ሔኖሮ ክፍለ ግዛት የወረደበትን ዝናብ ማስተናገድ አቅቶት ምድር፥-ጉባ፣ ኩይሳዉ ተንዶ ከዘጠኝ መቶ በላይ ሰዎችን ገደለ።ጥር አስራ አንድ።

ለቱኒዚያ ሕዝብ ግን አመቱ ገደኛ ብጤ ነበር።ጥር አስራ-አራት።እርግጥ ነዉ የፕሬዝዳት ዘይን ኤል አቢዲን ቤን ዓሊ ሥርዓት በደል-ግፍ-አንገፍግፎት እራሱን በእሳት ያጋየዉ መሐመድ ቡአዚዚ ከሞተ፥ የዚያን ቀን አስረኛ ቀኑ።የቡአዚዚን ዓላማ አንግበዉ ሲታገሉ የዚያ ሥርዓት ታጣቂዎች የጥይት እራትየሆኑት በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶችም የዚያን ዕለቱን ሁነት ለመታዘብ አልታደሉም።

ትግል፥ ፍልሚያ መስዋዕትነታቸዉ ግን ከንቱ አልቀረም።ቱኒዚያን ለሃያ-ሰወስት ዘመን ፈጥርቀዉ የገዟት ቤን ዓሊ ሥልጣን ሐገራቸዉን ጥለዉ ፈረጠጡ።ቲዚያ ፈነደቀች።ሕዝቧ ቤን ዓሊን በምግባራቸዉ ጠራቸዉ «ገዳይ» እያለ---


የቱኒዚያ ሕዝብ በሰላማዊ የአደባባይ ትግል ጥር-ላይ የተቀዳጀዉን ድል-ጥቅምት ሃያ ሰወስት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በነፃነት በሰጠዉ ድምፅ አጠናከረዉ።የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጀምር።

የትኒሺቱ ዓረባዊት ሐገር ሕዝብ አብዮት በድፍን ዓረብ ለመሰራጨት አፍታ-አልፈጀም።የትልቂቱን የጥንታዊቱን፥የሐያሊቱን ሐገር ሕዝብ ያክል ግን የፀና ወይም የቀናዉ አልነበረም።የግብፅ ሕዝብ።
ጥር-ሃያ አምስት ድፍን የግብፅ ከተሞች በሕዝብ ማዕበል ተጥለቀለቁ።በተለይ የካይሮዉ ተሕሪር አደባባይ።

Ägypten Kairo Tahrir Platz Demonstration
ካይሮ-ተሕሪርምስል dapd

«ሆስኒ ሙባረክ ይዉደም።ዳቦ፥ ነፃነት፣ ሰብአዊ መብት፥ ወይም አመፅ»

የፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ መንግሥት እንደ ብዙ ብጤዎቹ ሁሉ ሕዝባዊዉን አብዮት ለማዳፈን በመቶ የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን አስገደለ።በሺሕ የሚቆጠሩ አሳሰረ።ብሶት ያስቆጣዉ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ግን አልተበገረም።ግድያ፣ አፈና እመቃዉን፣ በገንዘብ የማባበሉን ሴራዉ እየበጣጠሰ ለዉሎ አደር-አመፅ ተሕሪር አደባባይ ከተመ።

የካቲት አስራ-አንድ።የሆስኒ ሙባረክ የሰላሰ ዘመን ሥርዓት ተገነደሰ።አፈና፥ ጭቆና ሥቃይ ሰቆቃ ያንተከተከዉ ሕዝብ የዚያን ቀን የድል ብስራት፥ የተስፋ ደስታ ያንተከትከዉ ገባ።

የሙባረክ አገዛዝ መንኮታኮት ለግብፅ ሕዝብ ታላቅ ድል፣ በአንገናዊ አገዛዝ ለሚሰቃየዉ ለዓረብ ለአፍሪቃ ሕዝብ ጉሉሕ አብነት፥ ከሁሉም በላይ ታማኞቻቸዉን ቀስ በቀስ ላጡት ለምዕራባዉን ከፍተኛ አስተምሕሮት ነበር።የቱኒዚያና የግብፅ ሕዝብ ትግል ከድል ዋዜማ እስኪደርስ ለቱኒዝና ለካይሮ ታማኞቻቸዉ ዙሪያ መለስ ድጋፍ ሲሰጡ የቆዩት የፓሪስ፣ የለንደን-ዋሽግተንና የተከታዮቻቸዉ ሐገራት መሪዎች የየሐገሮቻቸዉን ጥቅሞች ከታማኞቻቸዉ ሥርዓቶች ጋር መቅበር እንደሚያፈልጉ የዚያን ዕለት በግልፅ አስታወቁ።

ከመጪዉ ጋር ሠልፋቸዉን ለማሳመር የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ዋናዉ የመጀመሪያዉም ናቸዉ።የካቲት አስራ-አንድ።

«በሕወታችን ታሪክ ሲፈፀም ለማየት የምንታደልባቸዉ ጥቂት አጋጣሚዎች ናቸዉ።ይሕ ከነዚያ አጋጣሚዎቹ አንዱ።ይሕ ከነዚያ ጊዚያቶች አንዱ ነዉ።የግብፅ ሕዝብ ተናገረ፥ድምፁ ተሰማም።እና ግብፅ ከእንዲሕ የእስከንግዲሕዋ አትሆንም።»

ግብፅ በርግጥ የነበረችዉን አልሆነችም።ያ ጀግና ሕዝብ ግን የአብዮቱን ዉጤት፥ሙባረክን ከተኩት ጄኔራሎች እጅ ፈልቅቆ ለማዉጣት ግን ዳግም መታገል፣ ተጨማሪ ወጣቶቹን መስዋዕት ማድረግ ነበረበት።ሆስኒ ሙባረክና ሙባረክን የተኩት ጄኔራሎች ከዘጠኝ መቶ በላይ ወጣቶች አስገድለዋል። ሕዝቡ ግን በዳግም ትግል-ተጨማሪ መስዋዕትነቱ ጄኔራሎቹን አንበርክኮ-ሕዳር ላይ ለመጀመሪያዉ ዲሞክራሲያ ምርጫ ድምፁን ሰጠ።ዳግም ድል።

የአልጄሪያ ገዢዎች በድርድር-አታለዉ፥ የሞሮኮ፥ የዮርዳኖስና የኦማን ነገስታት በጥገናዊ ለዉጥ፣ ደልለዉ፥ የኩዌት፣ የስዑዲ አረቢያና የቀጠር ነገስታት በገንዘብ አባብለዉ የየሐገራቸዉን ሕዝባዊ አብዮት አዳፈኑት።የየመንና የባሕሬን ሕዝብ ግን በቱኒዚያና በግብፅ ብጤዎቹ አቋም ፀና።ዓረብ በሕዝባዊ አብዮት ሲናጥ፣ ተፈጥሮ ግን የዓለምን ትኩረት ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ወደ ሩቅ ምስራቅ ወረወረችዉ።ጃፓን።

መጋቢት አስራ-አንድ።የሳይስንስ ቴክኖሎጂይቱ ምድር፣ የዓለም ሁለተኛይቱ ሐብታም ሐገር በተፈጥሮ ቁጣ ፊት ኢምንት ሆነች።ምሥራቃዊ ግዛትዋን ያርገፈገፈዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከባሕር ነዉጥ ጋር ተዳምሮ አስራ-ስድስት ሺሕ ሕዝብ ፈጀ።አራት ሺሕ እስካሁን የደረበት አልታወቀም። በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሐብት ንብረት ወደመ።

አደጋዉ ካጠፋዉ ሕይወት፥ ሐብት ንብረት በላይ ፉኮሺማ የነበሩ የኑክሌር ማዕከላትን ማፈራረሱ ለዓመታት የማይነቀል መዘዝ ያስከትላል መባሉ ነዉ-ትልቁ ስጋት።አደጋዉ እንደ ኑክሌር ማዕከላቱ ሁሉ የሥልጣናቸዉን መሠረት አናግቶ ከጠቅላይ ሚንስትርነት ያስወገዳቸዉ ናኦቶ ካን ያኔ እንዳሉት ሥጋቱ የሚቃለልበት ጊዜ-አለመታወቁ ነዉ-የእስካሁኑ ጭንቀት።

«የአቶም ጨረሩ ያደርሳል የተባለዉ አደጋ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ሰወስት፥ አምስት ምናልባትም በብዙ አስርታት የሚቆጠር አመታት ይፈጅ ይሆናል።የሐገሪቱ የአቶሚክና የሐይል አጠቃቀም ሥለሚቀጥልበት ሁኔታ በጃፓን ሕዝብ መካካል አስቸኳይ ዉይይት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነዉ።»

Libyen Gaddafi Archiv 2009
እንዲሕ ነበሩምስል dapd

የአዉቶሚክ ቦምብን ዘግናኝ ጥፋት የቀመሰችዉ ብቸኛ ሐገር በኑክሌር ጨረር ሰዉ፣ እንስሳ እፅዋትን በማንጨርጨር ፉኮሺማ-ቼርኖቤልን ይቀድማል-ይከተላል እንዳሰኘ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ከፍፃሜዉ ደረሰ።

ምዕራባዉያኑ ሐገራት የራባት፣ የአልጀርስ፣ የአማን፣ የኩዌይት፣ የሪያድ፣ የዶኸ፥ የማናማ ወዳጆቻቸዉ የየሕዝባቸዉን አመፅ ማፈናቸዉን ሲደግፉ፣ የሰነዓ ታማኞቻቸዉን እመቃ በአደራዳራኒት ሰበብ አለፉት።

መጋቢት አስር፥ የቤንጋዚ ሕዝብ እንደ ጎረቤቶቹ ለተቃዉሞ አደባባይ ወጣ።አመፁ ብልጭ ከማለቱ የሕዝቡ ጥያቄ ተገቢነት፣ የሙዓመር ቃዛፊ ሰብአዊ መብት ረጋጭነት፣ አረመኔ፣ ጨፍጫፊነት የፓሪስ፥ ለንደን፥ የዋሽንግተን፥ ዶሐ የጧት ማታ አብይ ርዕሥ ሆነ።

የፓሪስ፣ ለንደን ዋሽግተን መሪዎች ሊቢያን የሚወጉ-ምናልባትም አንዳዶች እንደሚሉት «የነዳጅ ሐብቷን የሚቆጣጠሩበትን» ሕጋዊ ሽፋን ለማግኘት ሲራወጡ፣ የሪያድ፣ የዶሐ፣ የኩዌይት፣ የአቡዳቢ ታማኞቻቸዉ፥የማናማ ብጤያቸዉን እንዲረዳ ያዘመቱት ጦር፥ የማናማን አደባባይ ያጥለቀለቀዉን ሕዝብ በታንክ-ሔሊኮብተር ይጨፈልቀዉ ገባ።የሩቁ ታዛቢ አይደለም ሰልፈኛዉ እራሱ ይሕ ይሆናል ብሎ አላሰበም ነበር።የማይታማን አሉት አንዱ።

«ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ የምናየዉ የማይተማን ነዉ።ተዋጊ ሐፓቺ ሔሊኮብተሮች ሠልፈኛዉን ከሰማይ ከበዉታል፥ ወታደሮቹ ይደበድቡታል።አምቡላንሶች ቁስለኞችን እንዳያነሱ፥ ሐኪሞች ሆስፒታል የደረሱ ቁስለኞችን እንዳያክሙ ወደ ሆስፒታል እንዳይገቡ ተከልክለዋል።ሥለዚሕ የዚሕ ዓለም ሕዝብ እንዲረዳን እንጠይቃለን።እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን።ተገቢ መብታችንን እንጂ ሌላ ነገር አልጠየቅንም።»

ማናማ በደም ጨቀየች። ሰማንያዎች ረገፉ።ብዙ መቶዎች ቆሰሉ።ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዲሞክራሲ ፅናት ቆመናል የሚሉት የዋሽግተን፣ ለንደን፣ ፓሪስና የተባባሪዎቻቸዉን መሪዎችን ያስጨነቀዉ የሊቢያ እንጂ የባሕሬን ሕዝብ አልነበረም።

መጋቢት አስራ-ሰባት።የቃዛፊን ጨቋኝነት በአርባ-ሁለተኛዉ ዓመት ያወቁ-የመሰሉት ምዕራባዉያን ሐገራት በሊቢያ ላይ የበረራ-እግድ የተሰኘዉን ማዕቀብ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አሥፀደቁ። በሳልስቱ ሊቢያ በምዕራባዉን ቦምብ-ሚሳዬል ትነድ ገባች።

መጋቢት ሃያ-አንድ፥-የፈረንሳይ፥ የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የሊቢያን አየር ሐየር ሐይል በአራት ቀን እድሜ ማሽመድመዱን የዩናይትድ ስቴትሱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ማይክ መለን አስታወቁ።

«ቃዛፊ ከእንግዲሕ ተዋጊ አዉሮፕላንም ሆነ ሔሊኮብተር ማብረር አይችሉም።ሥለዚሕ የበረራ እግዱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ሆኗል ማለት እንችላለን።»

የበረራ እገዳዉ ሙሉ በሙሉ ገቢር ከሆነ-ድደባዉ መቆም ነበረበት።ግን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ወትሮም ሰበብ እንጂ አላማ ሥላልነበር የዉሳኔዉ አስፈፃሚዎች ፍላጎት ዓላማ ከግብ እስኪደረስ የፈረንሳይ፥ የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የጀመረዉን ድብደባ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ተረክቦ ሊቢያን መረምረሙን ቀጠለ።

የኔቶ-ጦር ካየር፥ ከባሕር በሚያዘንበዉ ቦምብ ሚሳዬል፥ የቃዛፊ መንግሥትና በኔቶ የሚደገፉት አማፂያን ከምድር የሚረጩት መድፍ፥ ጥይት-ሊቢያና ሊቢያዉያንን ሲያጋዩ የየመን ሕዝብ የሰላሳ-ሁለት ዘመኑን ፈላጭ-ቆራጭ ሥርዓት ይገዘግዘዉ ያዘ።የፕሬዝዳት ዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ ሥርዓት-ማርጀት ማፍጀቱን ከቀድሞዉ የሥርዓቱ አገልጋይ ከመሐመድ አቡልአሆም ቀድሞ የመሰከረ አልነበረም።

«በአደባባይ የምናየዉ፥ ወጣቶቻችን ለእዉነኛ ፍትሕ የሚያደርጉትን የተቃዉሞ ሠልፍ ነዉ።ከዚሕ ተምረን ለዉጡን መቀበል አለብን።ወደድንም ጠላንም ለዉጡ አይቀርም።»

የየመን ሕዝብ ትግል አላባራም።የዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ ፀጥታ አስከባሪዎች የገደሉት-ሰላማዊ ሰዉ ቁጥር በትንሽ ግምት ከአራት መቶ በልጧል።ሳሌሕም ቆስለዋል። ለየመን ሕዝብ እንደ ባሕሬን ሁሉ የደረሰለት ግን የለም።ከሕዝባዊዉ አብዮት መሪዎች አንዷ ታላቁን የሰላም ኖቤል ሽልማት ከሌሎች ጋር ተጋርታለች።አቡልአሆም የተነበዩት ለዉጥ ግን እስካሁን የለም።

ግንቦት አንድ።ሊቢያ ከምድር ካየር-መንደዷን ቀጥላለች።የመን በሕዝቧ ጩኸት፥ በገዢዎቿ ጥይት ትተረማሰለች።የዓለም ወዛደሮች ዓመታዊ ግብራቸዉን በየአደባባዩ ሰልፍ-አድረሰዉ ሲመለሱ ከዋሽግተን ያልተጠበቀ ዜና ተሰማ።፡
«እንደምን አመሻችሁ።በዛሬዉ ምሽት ለአሜሪካ ሕዝብና ለመላዉ ዓለም የሚከተለዉን ዘገባ አሰማለሁ።ዩናይትድ ስቴትስ ባደረገችዉ ዘመቻ-በሺ ለሚቆጠሩ ንፅሐን ወንዶች፥ ሴቶችና ሕፃናት ሕይወት ተጠያቂ የሆኑትን አሸባሪዉ የአልቃኢዳ መሪ ኦስማ ቢን ላደን ተገድለዋል።»

የድል-ብስራት።ከብዙዎቹ የአረብ ሕዝብ ዘግይቶ በገዢዎቹ ላይ ያመፀዉ የሶሪያ ሕዝብ ትግል ለወራት ብልጭ ድርግም ሲል አዝግሞ-ሰኔ ላይ ድብልቅልቁ ወጣ።

የሕዝቡ ተቃዉሞ ሲግም ምዕራባዉያን ሐገራት የፕሬዝዳት በሽር አልአሰድን መንግሥትና ባለሥልጣናቱን በተከታታይ ማዕቀብ ቀጡ።የአረብ ሊግም እንዲሁ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈሰዉ ሳምንት እንዳስታወቀዉ የአሰድ መንግሥት አመፁን ለመደፍለቅ በወሰደዉ እርምጃ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አራት ሺሕ ደረሰ።አመፁም፥እመቃዉም፥ ማዕቀቡም ቀጥሏል።

የአረብ ሕዝብ የየሐገሩን የዘመነ-ዘመናት ፓለቲካዊ ሥርዓት ለመለወጥ እየወደቀ-ሲነሳ ፍልስጤሞችም የዘመናት ጥያቄቸዉን እንደገና አነሱት።ኒዮርክ ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላላ ጉባኤ መስከረም-ሃያ ሁለት።
«የተከበሩ ፕሬዝዳት፥ ንግግሬን ከመጀመሬ በፊት፥-እንደ ፍልስጤም መንግሥትና እንደ ፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ፕሬዝዳትነቴ፥ ርዕሠ-ከተማዉን እየሩሳሌም ያደረገ፥ የድሕረ-ሰኔ አራት 1967ቱ ድንበር የሚያዋስነዉ የፍልስጤም መንግሥት፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሙሉ አባል እንዲሆን ለዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ማመልከቴን አስታዉቃለሁ።»

ፕሬዝዳት ማሕሙድ አባስ።አባስ በይፋ-ከማመልከታቸዉ በፊት የፍልስጤሞችን ጥያቄ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ አዳፍነዉት ነበር።መስከረም

«ለብዙ አስርታት የቆየዉን ግጭት ለማስወገድ አጭር-አቋራጭ እንደ ሌለ አምኛለሁ።ሰላም ከባድ ሥራ ነዉ።ሠላም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫና ዉሳኔ አይርድም።እንዲሕ ቀላል ቢሆን ኖሮ እስካሁን ሰላም በፀና ነበር።»

እስራኤል የተመሠረተችዉ ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫና ዉሳኔ ነበር።ኦባማ ያዳፈኑትን የፍልስጤሞች የአባልነት ጥያቄ የእስራሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጨርሶ ቀበሩት።

ኒዮርክ የታደሙት የአለም-ፖለቲከኛ ዲፕሎማቶች ሥልሳ-ሰወስት ዓመት እንደለመዱት እስራል፥ ፍልስጤም ሲሉ የካፒታሊስቱ ሥርዓት፥ በተለይም የገንዘብ ተቋማቱ ብዝበዛና ገፈፋ ያንገሸገሻቸዉ ወጣቶች-እዚያዉ ኒዮርክ ለተቃዉሞ አደሙ።መስከረም አስራ-ሰባት የኒርክ ወጣቶች ዙኮቲ በተሰኘዉ አደባባይ እንደዘበት የጀመሩት አድማ-ተቃዉሞ ድፍን ዓለምን አዳርሷል።ሰሞኑን ግን ከመንግሥታቱ ጫና ጋር የሰሜኑ ንፍቀ-ክበብ ብርድ አቀዝቅዞታል።


መስከረም አስራ-ዘጠኝ የፓኪስታን ግዛት በጎርፍ ተጥለቀለቀች።አራት መቶ ሰላሳ-ሰዉ ሞተ።ብዙ ሺዎችን አፈናቀለ።ጥቅምት አምስት፥-አሜሪካዊዉ የኮፒዉተር ሊቅና አፕል የተሰኘዉ የኮፒዉተር ፕሮግራምም ፈላስማ፥ የኩባንያዉ መስራች ስቲቭ ጆብስ በሐምሳ ስድት አመታቸዉ ሞቱ።

እንደገና ሊቢያ።የምዕራባዉን ጦር ቦምብ-ሚሳዬሉን ማዝነብ ሲጀምር-ለሙዓመር ቃዛፊ መጀመሪያ ቃል ነበር።

«ለሊቢያ ከነዚሕ አይጦችና ቅጥረኞች እኔና ጓዶቼ እጅግ በጣም እንሻላለን።በስተመጨረሻዉ መስዋዕት እሆናለሁ።»

USA Finanzkrise Demonstration Occupy Miami Flash-Galerie
ዎል-ስትሪትን አንቆጣጠርምስል dapd

ቃልም-ገቢር ሆነ።ጥቅምት ሃያ። የሊቢያ የአርባ አንድ አመት ገዢ ሲርት-ተወልደዉ ሲርት ተገደሉ።ስልሳ ዘጠኝ አመታቸዉ ነበር።የሊቢያዉ ጦርነት ባንዳዶች ግምት ከሰላሳ ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዉ አልቋል።

ዓለም፥ አረብ፥ ጃፓን፥ ቢን ላደን-ቃዛፊ፥ ፍልስጤም እስራኤል ሲል ችላ ያላት አፍቃኒስታን አስር አመት የለመደችዉን የእልቂት ፍጅት ዑደት በሰላም-ተስፋ ለማጀብ ያሕል ዓለም ቦን ላይ ለጉባኤ ታደመላት።ታሕሳስ-አምስት። በሳምንቱ ሩሲያ ዉስጥ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ተደረገ።

በምርጫዉ የቀድሞዉ ፕሬዝዳት፥ ያሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር፥ የወደፊቱም እጩ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን የሚመሩት ፓርቲ አሸንፏል ተባለ።ተቃዋሚዎች ግን ሐሰት አሉ።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ደጋፊያቸዉን ለተቃዉሞ ሰልፍ-በድሮዎቹ ቀይ አደባባዮች አሰለፉት።ቅዳሜ።

እና በአደባባይ ሰልፍ-የተጀመረዉ ሁለት ሺሕ አመት፥ ከአፍሪቃ በስተቀር የአደባባይ ሰልፍን በመላዉ ዓለም አዳርሶ-ባደባባይ ሰልፍ ሊያበቃ-አስራ-ስምንት ፈሪ አለ ዛሬ።ዑደቱ ቀጥሏል።እኔ በዚሑ ልሰናበታችሁ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።በዘመኑ ለምታሰሉ መልካም አዲስ አመት።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ



ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ