1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2021 ዓም የአውሮጳና ጀርመን ዐበይት ክንውኖች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 19 2014

2021ጀርመን ከባድ የተፈጥሮ አደጋ ያስተናገደችበት፣ውጤቱ አጓጊ የነበረ ምርጫ ያካሄደችበት፤እንደ እናት የሚወደዱትንና የሚከበሩትን የ16 ዓመት መሪዋን የሸኘችበትና በዓይነቱ የተለየ ሶስት ፓርቲዎች የተጣመሩበት አዲስ መንግሥት የመሰረተችበት ዓመት ነበር። የአውሮጳ ኅብረት ደግሞ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የመነጋገሪያ ርዕስ ያደረገበትም ዓመት ነው።

https://p.dw.com/p/44vob
Bildgalerie 50 Jahre Römische Verträge I Frankreich: Europäisches Parlament, Straßburg
ምስል Daniel Kalker/picture alliance

የዓመቱ የአውሮጳና ጀርመን ዐበይት ክንውኖች

ከሦስት ቀናት በኋላ አምና በምንለው በጎርጎሮሳዊው  2021 ከአውሮጳ  ዐበይት ጉዳዮች  አንዱ ብሬግዚት ነበር።አውሮጳውያን በተለይም የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ዓመቱን አንድ ብለው የጀመሩበት ጎርጎሮሳዊው ጥር አንድ 2021 ዓም ለ47 ዓመታት የኅብረቱ አባል የነበረችው ብሪታንያ በይፋ ከኅብረቱ የተሰናበተችበት እለት ነበር። ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት እንድትወጣ ብሪታንያውያን በህዝበ ውሳኔ ካጸደቁ ከአራት ዓመት ተኩል በኋላ ጥር አንድ ቀን 2021 እውን በሆነው ብሪግዚት የብሪታንያ ዜጎች በኅብረቱ አባል ሃገራት ፣የአባል ሃገራት ዜጎችም በብሪታንያ የመኖር እና የመስራት ነጻነታቸው ተገድቧል። በመለያየቱ ሰበብ ብሪታንያና  ጎረቤት ፈረንሳይ በአሳ ማጥመድና በስደተኞች ጉዳይ ሲወዛገቡ ቆይተዋል። ምንም እንኳን የአጭር ጊዜ ቆይታ ቪዛ ባያስፈልገውም፣ የቀድሞው በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ቀርቷል።የሸቀጦች ዝውውር በብሪታንያና በአውሮጳ ኅብረት ድንበሮች እንዲሁም በብሪታንያም በሰሜን አየርላንድና በብሪታንያ ድንበሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ተግባራዊ መሆን ከጀመረ እነሆ የፊታችን ቅዳሜ አንድ ዓመት ይሆነዋል።
በብሬግዚት የተጀመረው 2021 በአውሮጳ በተለይ ኮቪድ-19ን በመከላከል ላይ ያተኮረ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል።ኮሮና ከ1 ሚሊዮን 809 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ባጠፋበት በአውሮጳ እንደ ጎርጎሮሳዊው 2020 ሁሉ በ2021ም ኮሮና የአውሮጳ ሀገራት ተግዳሮት ሆኖ ቢቀጥልም በዓመቱ በተለይ የአውሮጳ ኅብረት ፀረ-ኮቪድ 19 ክትባትን ወጥ በሆነ መንገድ ለማዳረስ ያደረገው ጥረት ካለፈው ዓመቱ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው የኅብረቱ ኮሚሽን ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል ገንዘብ መመደቡ በኮቪድ ምክንያት ኤኮኖሚያቸው የተጎዳ ሀገራት እንዲያገግሙ እገዛ አድርጓል።ይህ ህብረቱ ካከናወናቸው የተሳኩ ስራዎች አንዱ እንደሚባል ነው ገበያው የተናገረው  
2021 ጀርመን ከባድ የተፈጥሮ አደጋ ያስተናገደችበት፣ ውጤቱ አጓጊ የነበረ ምርጫ ያካሄደችበት ፣ እንደ እናት የሚወደዱትንና የሚከበሩትን የ16 ዓመት መሪዋን የሸኘችበትና በዓይነቱ የተለየ የተባለ ሶስት ፓርቲዎች የተጣመሩበት መንግሥት የመሰረተችበት ዓመት ነበር።
ባገባደድነው በ2021 ዓም ሁለተኛው ወር ላይ ነበር ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር ሀገሪቱን ሲመራ የነበረው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አዲስ ሊቀ መንበር የመረጠው። በዚሁ ምርጫ የኖርድራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር  አርሚን ላሼት የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩትን የቀድሞዋ የጀርመን መራኄ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን እንዲተኩ ተመረጡ። ያኔ በፓርቲው ውስጥ የነበረውን ክፍፍል አስቀርተው መፍትሄ የማግኘት ሃላፊነት የተጣለባቸው ላሼት ፓርቲውን ወክለው በመስከረሙ የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ቢሳተፉም አላሸነፉም። ከሽንፈቱ በኋላ ፓርቲው ባካሄደው ጉባኤ አንጋፋውን የፓርቲውን አባል ፍሬድሪሽ ሜርዝን የላሼት ተተኪ አድርጎ መርጧል።  
በ2021 በተለይ በአውሮጳ የበጋ ወር ሐምሌ ምዕራብ ጀርመንን ያጥለቀለቀው ጎርፍና ማዕበል ከመቶ ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ይኽው አደጋው በምዕራብ ጀርመኖቹ ራይንላንድ ፋልስና፣ ኖርድራይን ቬስትፋለን፣ በተባሉት የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች እንዲሁም በጎረቤት ኔዘርላንድስና ቤልጅየም ያደረሰው ጥፋት ከፍተኛ ነበር።በከባዱ ዝናብ ሰበብ አነስተኛ ወንዞችና ምንጮች ገደፋቸውን አልፈው በርካታ መንደሮችን እንዳልነበሩ አድርገዋል። በአደጋው በጀርመን ብቻ ከ180 በላይ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ብዙዎች መኖሪያ ቤቶቻቸውንና ልዩ ልዩ ንብረቶቻቸውን አጥተዋል። ክርስቲያን ኤይድ የተባለው ድርጅት እንዳስታወቀው በአደጋው የደረሰው ጥፋት 43 ቢሊዮን ዮሮ ይገመታል። ይህ ብቻ አይደለም አደጋው በከፋባቸው አካባቢዎች  መብራት ውኃና የሞባይል አገልግሎት ለብዙ ቀናት ተቋርጦ ነበር። በጎርፍ አደጋውም ምክንያት የመድን ድርጅቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ንብረቶች ወደ 8.2 ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ከፍለዋል።ይህ እስከዛሬ የመድን ድርጅቶች ለአደጋዎች ካወጡት ገንዘብ ከፍተኛው ነው ተብሏል። በዚህ የተነሳም 2021 ለጀርመን የመድን ድርጅቶች እጅግ ውዱ ዓመት ተብሏል።  ከዚህ ውስጥ 7.7 ቢሊዮን ዩሮ ለመኖሪያ ቤቶች እና ለንግድ ድርጅቶች የተከፈለ ሲሆን ጉዳት ለደረሰባቸው መኪናዎች ደግሞ 450 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ከፍሏል።   
2021 ፣ ጀርመን ናምቢያን ቅኝ በገዛችበት ዘመን  የዘር ማጥፋት መፈጸሟን ያመነችበት ዓመትም ነበር። በአምስተኛው ወር ግንቦት መጨረሻ ላይ ነበር የያኔው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ጀርመን ከጎርጎሮሳዊው 1884 እስከ 1915 ናሚብያን ቅኝ በገዛችበት ወቅት በብዙ ሺህዎች በሚቆጠሩ ናሚብያውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ የዘር ማጥፋት ሲሉ ያመኑት።  በናምብያውያን ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ፣የዘር ማጥፋት ያሉት ማስ ለድርጊቱም ይቅርታ ጠይቀዋል። ለሰለባ ዝርያዎችም በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠትም ነበር ቃል የገቡት። 
«ዛሬ እነዚህን ድርጊቶችም የዘር ማጥፋት ብለን በይፋ እንጠራቸዋለን። ይህን በማድረጋችን ለታሪካዊ ሃላፊነታችንም እውቅና እንሰጣለን። ከጀርመን ታሪካዊና የሞራል ሃላፊነት በመነሳት፣ የናሚብያን ህዝብና የድርጊቱ ሰለባዎችን ዝርያዎች ይቅርታ እንጠይቃለን። በሰለባዎች ላይ ለደረሰው መጠኑ ለማይለካ በደል እውቅና በመስጠት በአመዛኙ ለናሚብያና ለሰለባዎች ዝርያዎች፣ለግንባታና ለልማት መርሃ ግብሮች የሚውል አንድ ቢሊዮን አንድ መቶ ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንሰጣለን።»
 ይህን የጀርመንን  ውሳኔ የናሚብያ መንግሥት አወድሷል። የዘር ማጥፋት ሰለባ ናሚብያውያን ዝርያዎችና ናሚብያውያን የፖለቲካ አራማጆች ግን ገንዘቡ በቂ አይደለም ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። ናሚብያው ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ አራማጅ ቡድኖች ጀርመን ካሳውን በቀጥታ ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች  ባለመስጠቷ ስምምነቱን ተችተዋል።
ወደ አውሮጳ ኅብረት ስንመለስ  በዓመቱ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ችግር በጋራ በመቋቋም ጠንክሮ የወጣው ኅብረቱ ፣በውጭ የፖለቲካ መርሁ ከቤላሩስ ከሩስያ ከአሜሪካና ከቻይና እንዲሁም ከቱርክ ጋር ያለው ግንኙነት በዓመቱ ሲያነሳቸው የቆዩ ጉዳዮች ነበሩ። ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ግን ኅብረቱ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የመነጋገሪያ ርዕስ ማድረጉን የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ያስታውሳል። 
ከዚህ ዓመት የጀርመን ዐበይት ክንውኖች ዋነኛው ፣ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው በመስከረም የተካሄደው የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ ነው። ለ16 ዓመታት ጀርመንን የመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አንጋፋ ፖለቲከኛ አንጌላ ሜርክል ባልተወዳደሩበት በዚህ ምርጫ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አሸንፎ ፓርቲው ለመራኄ መንግሥትነት በእጩነት ያቀረባቸው ኦላፍ ሾልትዝ ስልጣኑን በቅርቡ ተረክበዋል። ውጤቱ አጓጊ በነበረው በዚህ ምርጫ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ በርካታ ህዝብ ድምጽን ሰጥቷል። ምርጫውን ያሸነፈው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲም ከአረንጓዴዎቹና ከነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር በዓይነቱ የተለየ የተባለ ጥምር መንግሥት ከመሰረተ ጥቂት ሳምንታት አልፈዋል።የአዲሱ የጀርመን መንግስት ምስረታ ሂደት ከከዚህ ቀደሞቹ የመንግሥት ምስረታ ድርድሮች በተለየ ብዙ ውጣ ውረድ ያልታየበት፣ውዝግብም ያልተሰማበት ነበር። ከሁለት ወራት ድርድር በኋላ ሶስት የተለያየ መርህ የሚከተሉ ፓርቲዎች ተግባብተው በጥምረት ጀርመንን ለመምራት መስማማታቸው በእጅጉ ተወድሷል። በመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስልጣን ዘመን የስራና የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትርና ምክትል መራሄ መንግሥት ሆነው ያገለገሉት  ሾልዝ ሜርክልን የመተካት በተለይም ጀርመን በአውሮጳ የመሪነቱን ቦታ ይዛ እንድትቀጥል የማድረግ ብቃታቸው ሲያነጋግር ቢቆይም በቅርቡ እንደተናገሩት ግን መንግሥታቸው እንደ ሜርክል መንግሥት ሁሉ አውሮጳን የማጠናከር እቅድ አለው።
 ጀርመንን ለ16 ዓመት የመሩት ሜርክል በ2021  መጨረሻ ነው በክብር የተሸኙት።በጀርመን ታሪክ ለመራኄ መንግሥትነት የበቁ የመጀመሪያዋ ሴት ፖለቲከኛ ሜርክል ከፍተኛ ተሰሚነት ካላቸው የአውሮጳ መሪዎች አንዷ እስከመባል ደርሰዋል።ራሳቸውን ከፖለቲካው ካገለሉ የቆዩት ሜርክል ስልጣናቸውን ለተተኪው ኦላፍ ሾልዝ ሲያስረክቡ ምክርም ሰጥተዋቸው ነበር።
« የተከበሩ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እንኳን ደስ አለዎ ከልምዴ እንደማውቀው ለዚህ ሃላፊነት መብቃት አስደሳች ነው። ስራው አስደሳች አጓጊና ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን መገመት ይችላሉ። ስራውን ሙሉ በሙሉ በደስታ ካከናወኑት ለዚህ ሀገር ሃላፊነት ከሚወስዱበት ምርጥ ስራዎች አንዱ ነው።ለስርዎ በስራዎ ከልብ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ። ለሀገራችንም መልካም እድል እንዲገጥምዎትት እመኛለሁ።»

BG Merkels letzter Tag
ምስል Sean Gallup/Getty Images
Deutschland | Schloss Bellevue - Ernennungsurkunde Scholz
ምስል Emmanuele Contini/Getty Images
Türkei Kastamonu | Dronenaufnahme von Flutschäden
ምስል Umit Yorulmaz/AA/picture alliance

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ