1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ7 ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ተጠየቀ  

ዓርብ፣ የካቲት 8 2011

ለ79ነኛ ጊዜ በአዊ ብሔረሰብ ዞን እንጅባራ ከተማ ሰሞኑን በድምቀት የተከበረዉ የ7 ቤት አገው የፈረሰኞች ማኅበር መረሃ ግብር በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ተጠየቀ። የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር የተመሰረተው አባት አርበኞች ጣሊያንን በአድዋ ድል ከነሱ በኋላ የፈረሶችን ውለታ ለማስታወስ ነዉ።  

https://p.dw.com/p/3DOxz
Äthiopien Injibara -Agau "Horse Riding Association"
ምስል DW/A. Mekonnen

የ7 ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር

 

የ7 ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ለ79ነኛ ጊዜ በአዊ ብሔረሰብ ዞን እንጅባራ ከተማ ሰሞኑን በድምቀት ተከብሯል። የሰባት ቤት አገው  የፈረሰኞች ማህበር የተመሰረተው አባት አርበኞች ጣሊያንን በአድዋ ድል ከነሱ በኋላ የፈረሶችን ውለታ ለማስታወስ ተብሎ እንደሆነ የማህበሩ ፕረዚደንት አለቃ ጥላዬ አየነው ተናግረዋል። ማህበሩ በመጀመሪያ እንዴት አንደተመሰረተና  ስያሜውንም እንዴት እንዳገኜ አለቃ ጥላዬ አስረድተዋል። በሂደት የማህበሩ አባላት እየተበራከቱ መምጣታቸውን የሚናሩት አለቃ ጥላዬ በኋላም ሰባት ወረዳ በነበረው የወቅቱ የአገው ምድር አደረጃጀትና በሰባቱ ወንድማማቾች በሚጠሩት ወረዳዎች ስሜው አንደተቀየረ ጠቁመው አሁን የአባላቱ ቁጥር የደረሰበትን ደረጃ ይናገራሉ። የአዊ ብሔረሰብ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መለሰ አዳል ባህሉን ለቱሪስት መስህብነት ለመጠቀም ከአለፈው ዓመት ጀምሮ የማህበሩን ዓመታዊ ክብረ በዓል በዞኑ ዋና ከተማ እንጅባራ መክበር መጀመሩን ገልፀዋል። በቀጣይ የዞኑን ህብረተሰብ አለባበስና ሌሎቹንም እሴቶች በማስተዋወቅ የፈረስ ማህበሩን ዓመታዊ ፌስቲቫል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ይሰራልም ብለዋል።

Kultureller Pferdeverband in der Region Amhara
ምስል DW/A. Mekonnen

በዓሉ ከሌሎች በዓላት ልዩ የሚያደርገው ለእንስሳት ክብር ተሰጥቶት መከበሩ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን ናቸው። በዓሉ የበለጠ እውቅና እንዲኖረው ምሁራን እንዲያጠኑት እየተደረገ መሆኑንና ይህን የሚዘክር ሙዚየም ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነ ለ”DW” ተናግራል። ማህበሩ ለዞኑ ህብረተሰብ ያለው ማህበራዊ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ይህን ቱባ ባህል ለትውልድ ለማስተላለፍ ይሰራል ነው ያሉት።

Äthiopien Injibara - Agau "Horse Riding Association"
ምስል DW/A. Mekonnen

በበዓሉ ወቅት የሚከናወኑ ተግባራትም አቶ ባይነሳኝ አመልክተዋል። የፈረስ ማህበር አባል የሆኑትና ከዚገም ወረዳ  እንደመጡ የሚናገሩት አቶ ወረቁ ኃይሌ የፈረስ ማህበር አባል መሆን የሚያስገኘውን ጥቅም ዘርዝረዋል። ወ/ሪት ማህሌት የኔው በእለቱ ፈረስ ስትጋልብ ነው ያገኘኋት። የምትጋልበውን ፈረስ ለጥቂት ደቂቃዎች ገታ አድርጋ ለምን የፈረስ ማህበር አባል መሆን እንደፈለገች አጫውታኛለች።  የእለቱ የክብር እንግዳና በባህል ተጫዋችነቱ የሚታወቀው ይሁኔ በላይ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር አምባሳደር ተብሎ በማህበሩ አባላት ተሹሟል። ስሜቱን አካፍሎኛል። የካቲት 3/2011 ዓ ም በተካሄደው በዚሁ በዓል ላይ  የፌደራል፣ የክልልና የዞን ባለስልጣናት፣ ታዋቂ አርቲስቶችና እጅግ ቁጥሩ የበዛ የፈረሰኞች ማህበር አባላት ከነፈረሶቻቸው ጋር ተገኝተዋል።

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ