1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የIS እርምጃ፤የዮርዳኖስ ብቀላ እና መዘዙ

ረቡዕ፣ ጥር 27 2007

ከአማን ዉሎዉን የተሰማዉ ግን የዚያች ሐገር ሕዝብ ለሁለት መከፈሉን ጠቋሚ ነዉ።ገሚሱ እንደ ገዢዎቹ ሁሉ ሶሪያና ኢራቅ የመሸጉትን አማፂያን መዉጋት አለብን ይላል።ሌላዉ ደግሞ ምን አግብቶን

https://p.dw.com/p/1EVc4
ምስል Reuters/M. Hamed

እራሱን «የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS)» ብሎ የሚጠራዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ከዚሕ ቀደም የማረከዉን ዮርዳኖሳዊ የጦር ጄት አብራሪ መግደሉ ትንሺቱን አረባዊት ሐገር አጣብቂኝ ዉስጥ ከትቷል።የንጉስ አብደላ መንግሥት የፓይለቱን ደም ለመበቀል ከዚሕ ቀደም ሞት ተፈርዶባቸዋል ያላቸዉን ሁለት የአል-ቃኢዳ አባላትን ገድሏል።ይሁንና የብቀላዉ ግድያ ዮርዳኖስ በአሜሪካ መራሹ ዘመቻ መሳተፏን በመደገፍና በመቃወም የተከፈለዉን ዮርዳኖሳዊ የሚያግባባ አልመሰለም።ጉዳዩ ያሰጋቸዉ ንጉስ አብደላሕ በዩናይትድ ስቴትስ የሚያደርጉትን ጉብኝት አቋርጠዉ ለመመለስ ተገደዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

መቶ አለቃ ሙዓት አል-ካሴአስበሕ አሜሪካኖች በሚመሩት ዉጊያ፤ የዚያን ፅንፈኛ ቡድን ይዞታ ለመደብደብ ቦምብ ያጨቀበትን አሜሪካ ሠራሽ F-16 ጄቱን እያበረረ ራቃ-ሶሪያ ሰማይ እንደደረሰ አዉሮፕላኑ ተመቶ ወይም ተበላሽቶ ወደቀ።እሱም ተማረከ።

ኢራቃዊቷ ሳጂዳ አል ሪሻዊ እና ዚያድ አል-ካርቡልይ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2005 አማን ዮርዳኖስ ዉስጥ ሥልሳ ሰዎችን በቦምብ አጥፍተዉ ከጠፉ አሸባሪዎች ጋር በአባሪ-ተባባሪነት ነበር የተወነጀሉት።

ይሕ ነዉ የሁለቱ ተቃራኒዎች ገድል።

አክራሪዉ አማፂ ቡድን (ISIS) እና የዮርዳንስ መንግሥት እነዚሕን ምርኮኞች ለመለዋወጥ መደራደር፤ መስማማታቸዉ ሲወራ፤ሲዘገብ ሲተነተን-ነበር።የተባለ፤የማይሆንበት፤የሆነ የማይባልበት የተቃርኖ ምድር ዘመናት እንደተመሰከረለት አይን-ላጣፋ-አይን አጥፋ ዓይነት ብይን ዛሬም እንደገና ፀናበት።

Jordanien - Pilot
ምስል Reuters

ፅንፈኛዉ ቡድን ዛሬ ባሰራጨዉ ቪዲዮ እንዳሳየዉ የንጉሳዊዉ አየር ሐይል ፓይለት እሳት ተለቆበት ተገድሏል።ለወላጅ፤ዘመድ፤ ወዳጆቹ ታላቅ ሐዘን።ሳፊ አል-ካሴአስበሕ-አባት ናቸዉ።«የዮርዳኖስ መንግሥት የልጄን ደም ለመበቀል በአሸባሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ አጠይቃለሁ።»

ለሐሺማይቱ ንጉሳዊ አገዛዝ በርግጥ ከፍተኛ ቁጭት ነዉ።ንጉሳዊዉ አገዛዝ የመጀመሪያ የብቀላ ዱላ ያረፈዉ ግን በሁለቱ ኢራቃዉያን ላይ ነዉ።ወይዘሮ ሪሻዊ እና አቶ ካርቦልይ።ሁለቱም በሥቅላት ተገደሉ።የሁለቱ ሰዎች ወላጅ፤ ዉላጅ፤ ዘመድ ወዳጆች ወይም የኢራቅ መንግሥት ያሉት ካለ-በይፋ አልተነገረም።

የግድያ-ብቀላ ግድያዉን ዜና ዋሽግተን ሆነዉ የተከታተሉት ወይም የብቀላ ግድያዉን ያፀደቁት ንጉስ አብደላሕ ግን ፓይለታቸዉ «መስዋዕት» የሆነለት ዓላማ ግብ እንዲመታ ሕዝባቸዉ በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል።

«የተሰዋዉ (ፓይለት)ን ቤተ-ሰብ ሐዘን እንጋራለን።ሐዘናቸዉ የሁሉም ዮርዳኖሳዊ ሐዘን ነዉ።እንደ አንድ ሐገር በጋራ መቆም የሁላችንም ግዴታ ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ንጉሱን ወደ አማን የሸኙት ሙሉ ድጋፋቸዉን ሰጥተዉ ነዉ።ከአማን ዉሎዉን የተሰማዉ ግን የዚያች ሐገር ሕዝብ ለሁለት መከፈሉን ጠቋሚ ነዉ።ገሚሱ እንደ ገዢዎቹ ሁሉ ሶሪያና ኢራቅ የመሸጉትን አማፂያን መዉጋት አለብን ይላል።ሌላዉ ደግሞ ምን አግብቶን።-እሳቸዉ አንዱ ናቸዉ።

Sajida al-Rashawi Al-Qaida-Mitglied 2006
ምስል Reuters/M. Jaber

«(እንዲያዉ) ሁሉም ምንም አልጣመኝም።የኛ ፍላጎት አይደለም።ከሶሪያ ምንድነዉ የምንፈልገዉ? ልጆቻችንን ወደዚያ ያዘምታሉ---እዚያ ምን የጠፋብን ነገር አለ?»ዮርዳኖስ በአሜሪካ መሪና አስተባባሪነት ኢራቅና ሶሪያ የሸመቀዉን ቡድን ከሚወጉት አምስት የአረብ መንግሥታት አንዷ ናት።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ