1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያለክፍያ ነፃ አገልግሎት

ዓርብ፣ ግንቦት 24 2004

ያለምንም ክፍያ በነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይስጡ ቢባሉ ምላሽዎ ምን ይሆናል? «ያለክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በኢትዮጵያ» የዛሬው የወጣቶች መድረክ ቆይታችን የሚያተኩርበት ርዕስ ነው። ይመሻል ይነጋል። ሁላችንም ታዲያ እንደየፍላጎት፣ ምርጫችን መምሸትና መንጋቱን በየራሳችን ዘዬ ማስተናገዳችን አይቀርም።

https://p.dw.com/p/156dR

ያለምንም ክፍያ በነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይስጡ ቢባሉ ምላሽዎ ምን ይሆናል? «ያለክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በኢትዮጵያ» የዛሬው የወጣቶች መድረክ ቆይታችን የሚያተኩርበት ርዕስ ነው። ይመሻል ይነጋል። ሁላችንም ታዲያ እንደየፍላጎት፣ ምርጫችን መምሸትና መንጋቱን በየራሳችን ዘዬ ማስተናገዳችን አይቀርም። በእርግጥ ነገ ትርፍ አለያም ኪሳራ ተሽክሞ ቢጠብቀንም ማለት ነው። ለ24 ዓመት ወጣቷ የህክምና ዶክተር እና በአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ስራ አስኪያጅ ለሆነችው ሌላኛዋ ወጣት ግን ነገ ኪሳራ ተሸክሞ የሚጠብቃቸው አይመስልም። ቢያንስ ሁለቱም የህሊና ርካታ ለሚለግሳቸው ተግባር ጊዜያቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋልና። ሠላም ንጉሴ «ፍሬ ገነት ኪዳን ለህፃናት» በሚባለው በጎ አድራጊ ድርጅት ውስጥ ስራ አስኪያጅ ስትሆን በግሏም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች።

ወጣት ሠላም በግሏ ምን አይነት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን። ስራ አስኪያጅ በሆነችበት የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ እየመጡ የነፃ አገልግሎት ከሚሰጡ ግለሰቦች መካከል የ24 ዓመት ወጣቷ ዶክተር ቃልኪዳን አላቸው ትገኛለች። በአለርት ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ዳይሬክተር ስትሆን፤ በግሏ ደግሞ የነፃ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች።

ዶክተር ቃልኪዳን የነፃ አገልግሎት የምትሰጥበት ትምህርት ቤት የተካተተበት ፍሬገነት ኪዳን ለሕፃናት በራሱ የተቋቋመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን መሰረት አድርጎ ነው። ይህ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲጠነሰስ ነፃ አገልግሎት የመስጠት ራዕይ የነበራትን አንዲት ወጣት ህልም ከግብ ለማድረስ በማሰብ ነበር። በእርግጥ ወጣቷ ከዓመታት በፊት በድንገተኛ አደጋ ብታልፍም ህልሟ ግን ዛሬ ግቡን ሊመታ ችሏል።

በኢትዮጵያ እንደ ወጣት ፍሬገነት ሁሉ የነፃ አገልግሎት የመስጠት ህልም ያላቸው ወጣቶች ያን ያህል በርካታ ናቸው የሚባሉ አይደለም። በእርግጥ እንቅስቃሴው ቢኖርም ማለት ነው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በነፃ መስጠቴ የህሊና ርካታ እንዳገኝ ያስችለኛል ስትልም ገልፃለች ወጣቷ ሐኪም።

ወጣት ሠላም በበኩሏ በግል መፀሐፍትን በማሳተም በነፃ የማደል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች። ለዚያ ደግሞ ያነሳሳት በኢትዮጵያ ያለው የተረት መፀሐፍት እጥረት እንደሆነ ገልፃለች። የማንበብ ፍላጎትን ገና በለጋ እድሜ እንዲበለፅግ ማዳበር ወደፊት አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ያስችላል የሚል ጽኑ እምነትም አላት።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አንድን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቅም ይታወቃል። ለአብነት ያህል እዚህ ጀርመን ሀገር ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ነፃ የማኅብረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ሲረባረቡ ይስተዋላል። በሀገራችንም ወጣቶች መሰል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቢታይም፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን ጊዜ የለኝም በሚል የነፃ አገልግሎት ከመስጠት ሲገደቡ ይስተዋላል።

«ያለክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ ሁለት ወጣቶችን ያነጋገርንበት ጥንቅራችን በዚህ ይቋጫል። ወጣቷ ሐኪም ቃልኪዳን አላቸውን እና ወጣቷ ስራ አስኪያጅ ሠላም ንጉሴን በአድማጮች ስም ከልብ እናመሰግናለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ