1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያላባራው የስደት ፍሰት

ሰኞ፣ ሰኔ 10 2011

ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገራትም ሆነ እዚያው በሀገር ውስጥ ከቦታ ወደ ቦታ የሚደረገው ፍልሰት መቀጠሉን አንድ ጥናት አመለከተ። ድንበር ተሻግሮ ከሀገር ለመውጫነት ሰዎች የሚጠቀሟቸው የተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ላይ ቁጥጥር የሚደረግ ቢሆንም ስደት ግን አሁንም እንዳላቋረጠ ጥናቱን ካካሄዱት ምሁራን አንዱ ለዶይቼ ቬለ DW ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/3Ka83
Serbien Migranten
ምስል picture-alliance/AP Photo/D. Vojinovic

«ስደቱ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ቀጥሏል»

 ከሀገር የሚደረገውን ፍልሰት ለማስቆም የመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርቲሲ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የስነሰብ መምህር ዶክተር ፈቃዱ አዱኛ፤ ጥረቱ ግን ያን ያህል የተሰዳጁን ቁጥር እንዳልቀነሰው በጥናቱ መታየቱን ይናገራሉ። ጥናቱን ያካሄደው የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ የማኅበራዊ ሳይንስ ተቋም ሲሆን ዶክተር ፈቃዱ ወደዚህ ጥናት ከገቡ ከአንድ ዓመት ጥቂት አለፍ እንደሚል አመልክተዋል። የፍልሰቱ ሁኔታ ከሀገር መውጣት ብቻ ሳይሆን እዚያው ሀገር ውስጥ ወቅትን ተከትሎ ወይም የእርሻ ቦታም ሆነ የጉልበት ሥራ ፍለጋ የሚደረግ መሆኑን ዶክተር ፍቃዱ ያስረዳሉ።

በተለይ ድንበር ተሻግሮ ወደሌሎች ልዩ ልዩ ሃገራት የሚደረገው ፍልሰት መንገዱ እጅግ አደገኛ እና የሞት ስጋት ያጠላበት መሆኑ በየጊዜው ይነገራል። ብዙዎችም ሕይወታቸውን ማጣታቸው የየጊዜው ዜና ነው። እንዲህም ሆኖ ስደቱ ሊቆም ያልቻለበትን ምክንያት ጥናቱን ተመርኩዘው ዶክተር ፍቃዱ ከተማ ላይ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሥራ አጥነት፤ በገጠር ደግሞ የመሬት እጥረት መኖርን ከውስጥ ገፊ ምክንያቶች ከውጭ ደግሞ የሚያሳስቱ እና ሳቢ ምክንያቶች መኖራቸውን ይዘረዝራሉ።

Symbolbild Folter Afrika
ምስል Getty Images/AFP/F. Buccialrelli

በዚህም ላይ በየማኅበራዊ መገናኛው የሚዳረሰው አማላይ እና የተዛባ መረጃ፣  በዚያም ላይ ወደ ውጪ ሰው ከሄደ ቶሎ ይለወጣል የሚለው አስተሳሰብም ስደት እንዳይቆም የራሱን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል። የአውሮጳ ሃገራት በተለይ ከአፍሪቃ ሃገራት አላባራ ያለውን የተሰዳጆች ፍሰት ለመግታት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ጋር የተለያዩ ድርድር እና ስምምነቶች ሲያደርጉ ታይቷል። የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እና ፕሮጀክቶችም እንዳሉ በየጊዜው ይነገራል። ይህ ምን ያህል ውጤት አምቶ ይሆን? ዶክተር ፈቃዱ እንደሚሉት ብዙዎቹ ጥረቶች እስካሁን መሬት አልረገጡም።

Mittelmeer Flüchtlinge aus Seenot gerettet
ምስል picture-alliance/AP Photo/O. Calvo

እርግጥ ከስደት የተመለሱትን ለማቋቋም የሚደረገው ድጎማ መልካም እና አንድ ነገር ሊባል ይችላል። ሆኖም ግን ሰዎች በብዛት የሚሰደዱባቸውን አካባቢዎች በመለየት አስቀድመው ከሚኖሩበት ስፍራ ሳይለቅቁ ለፍልሰቱ ምክንያት የሚሆኑትን በማጣራት በመለየት ገና ሳይሰደዱ ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል ሥራ መሠራት እንደሚኖበት ነው ያመለከቱት። ከዚህም ሌላ የተለመዱ የስደት መስመሮች ላይ ቁጥጥሩ ቢጠብቅ፤ ሰዎችንም በሕገወጥ የሚያሸጋግሩት ላይ ክትትሉ ቢጠናከር ስደትን ፈፅሞ ማስቀረት ባይቻል እንኳ የተሰዳጆችን ቁጥር ለመቀነስ አንዱ መንገድ እንደሆነም  በአዲስ አበባ ዩኒቨርቲሲ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የስነሰብ መምህር ዶክተር ፈቃዱ አዱኛ ከዶይቼ ቬለ ጋር በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ