1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልተሳካው የዩክሬን ተኩስ አቁም

ሰኞ፣ የካቲት 9 2007

የዩክሬን መንግስት እና አማጽያን በሳምንቱ መጨረሻ የተፈራረሙት ስምምነት በአንድ ቀን ተጣሰ። የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄኔፈር ፓሳኪ ሩሲያ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በምስራቅ ዩክሬን አሰማርታለች ሲሉ ከስሰዋል።

https://p.dw.com/p/1EcWz
Ukraine Unruhe in Debaltseve
ምስል Getty Images/B. Hoffman

የዩክሬን መንግስት ጦር እና አማፅያኑ በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል የሚያደርጉት የተኩስ ልውውጥ በሳምንቱ መጨረሻ የተፈረመውን ስምምነት ዋጋ ቢስ ያደርገዋል የሚል ስጋት አይሏል። የዩክሬን፣የሩሲያ እንዲሁም የጀርመን ናፈረንሳይ መሪዎች የተሳተፉበት ስምምነት ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ሊያቆሙ የጦር አውድማ የሆኑትን አካባቢዎችም ከከባድ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲያደርጉ የታቀደ ነበር። በሚኒስክ ቤላሩስ የተፈረመው ስምምነት ካሁን ቀደም ሁለቱ ወገኖች በወርሃ መስከረም ካደረጉት የተለየ ባይሆንም በሉሃንስክ ግዛት ነዋሪዎች ዘንድ ግን የተስፋ ጭላንጭል አሳይቶ ነበር።

የአካባቢው ነዋሪ ስምምነቱ እንደተፈረመ «እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ድረስ አልተኛንም ነበር። ከዚያም ፀጥታ ሆነ እና ተኛን። አሁን ፀጥታ የሰፈነ ስለሚመስል ወደገበያ እየሄድን ነዉ። እንደእግዚአብሔር ፈቃድ የተሻለ ይሆናልም ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረው ነበር።

እሁድ ለሊት ተግባራዊ እንዲሆን የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ግን የተጣለበት ተስፋ ሳይበዛበት አልቀረም። በምስራቅ ዩክሬን በሉሃንስክ ግዛት የዴባልትስቭ ከተማ የከባድ መሳሪያ ልውውጦች መሰማታቸውን አሶሼየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የአሶሼትድ ፕሬስ ባልደረቦች ከባድ መሳሪያውን የዩክሬን መንግስት ጦር ሳይተኩስ እንዳልቀረ ተናግረዋል። በኬየቭ መንግስት ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር የምትገኘው የዴባልትስቭ ከተማ ከውጭ በአማጽያኑ ተከባለች። አማጽያኑ ከተማዋን የኬየቭ መንግስት ደጋፊዎች እንዲያስረክቧቸው ይፈልጋሉ። የዩክሬን ፕሬዝደንት ፔትሮ ፕሮሼንኮ ለስምምነቱ መጣስ አማጽያኑን ትረዳለች ተብላ የምትከሰሰውን ሩሲያ ተጠያቂ አድርገዋል።

Ukraine Panzer der ukrainischen Armee
ምስል Reuters/A. Chernyshev

«በሚኒስክ ስምምነት ላይ ከደረስን በኋላ የተፈጸመው ጥቃት በዩክሬን ንጹሃን ላይ ብቻ የተፈጸመ አይደለም። ይህ በሚኒስክ የሰላም ስምምነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው። የሚኒስክ ስምምነት እንደተፈረመ ያለ አንዳች ማብራሪያ የሩሲያ የጥቃት ዘመቻ ተጠናክሯል።»

በሌሎች የዩክሬን አካባቢዎች ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን የዜና አውታሮች ዘግበዋል። የግዛቲቱ ቁልፍ የመጓጓዣ ማዕከል እንደሆነች በሚነገርላት የዴባልትስቭ ከተማ በዩክሬን መንግስት ሃይሎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ቢሰነዘርም ወደ ከፋ ጦርነት የደረሰ ግን አይመስልም። አማጽያኑ የሰላም ስምምነቱን እየጣሱ በመሆኑ የኬየቭ መንግስት ሃይሎች አካባቢውን ለቀው እንደማይወጡ ማስታወቃቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ከስምምነቱ በኋላ አማጽያኑ በፈጸሙት ጥቃት አምስት የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን እና 25 መቁሰላቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

Ukraine Unruhe in Debaltseve
ምስል Reuters/G. Garanich

የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄኔፈር ፓሳኪ በአካባቢው ለተፈጠረው ትርምስ ሩሲያን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

«የሩሲያ ጦር በርካታ የጦር መሳሪያ እና ተተኳሾችን የዩክሬናውያኑን ቦታ ወደሚያጠቃበት የዴባልትስቭ ከተማ አካባቢ አሰማርቷል። የሩሲያ ጦር የአየር መቃወሚያ ወደ አካባቢው አሰማርቷል። እነዚህ የሩሲያ ጦር እንጂ የአማጽያኑ አለመሆናቸውን እርግጠኞች ነን። ይህ በሙሉ በዚህ ሳምንት ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በተጻራሪ የተደረገ ነው።»

ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ለአስር ወራት የዘለቀውን እና 5,300 ሰዎች ያለቁበትን የዩክሬን ቀውስ መቋጫ ያበጃል የሚል ተስፋ ተጥሎ ነበር። የዩክሬን ባለስልጣናትም ይሁኑ የአማጽያኑ መሪዎች ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት አበክረው እንደሚሰሩ ቢናገሩም እርስ በርስ ከመወነጃጀል ያለፈ የፈየዱት ነገር የለም። በግጭቱ የምትወቀሰው ሩሲያ ሁለት ምክትል መከላከያ ሚኒስትሮች ከሌሎች 19 ግለሰቦች እና ተቋማት ጋር የአውሮጳ ህብረት ማዕቀብ እንደጣለባቸው አሶሼየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ