1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያመፁ ወታደሮችና የኤርትራ መንግሥት

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2005

ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/17PVO
Straßenszene in der Independence Avenue in Asmara, der Hauptstadt von Eritrea, aufgenommen 1997.
ምስል picture-alliance/ dpa

ትናንት ባመጹ ወታደሮች ተቋርጦ ነበር የተባለው የኤርትራ መንግሥት ቴሌቪዥን ስርጭት መቀጠሉ ተዘገበ ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሰረት የኤርትራ መንግሥትም በዋና ከተማይቱ አስመራ ሁሉም ነገር ሠላማዊ መሆኑን አስታውቋል ። ይሁንና በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል ።

የኤርትራ ፕሬዝዳንት የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረ መስቀል እንደ ትናንት ሁሉ ዛሬም አስመራ ሰላማዊ ናት ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። አንድ የተቃዋሚ ድረ ገፅን የጠቀሰው  AFP  ወደ 100 ይጠጋሉ ያላቸው ትናንት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን የተቆጣጠሩ ያመፁ ወታደሮች አዛዥ እጃቸውን ለመስጠት መስማማታቸውን ዘግቧል ።

Blick über Asmara.jpg Blick über die Häuser von Asmara vom Turm der Kathedrale aus gesehen. Im Vordergrund die Independence Avenue, aufgenommen 1997.
ምስል picture-alliance/ dpa

የዘገባው እውነትነት ግን በሌላ ምንጭ አልተረጋገጠም ።  አንዳንድ ምንጮችም የወታደሮቹን እርምጃ ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር አስተካክለውታል ። በብሪታኒያው የጥናት ተቋም ቻተምሃውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች አጥኚ አህመድ ሶልሜን ግን ከኤርትራ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ የተፈፀመውን ለማወቅ አዳጋች መሆኑን ነው ለዶቼቬለ የተናገሩት ።         

« መፈንቅለ መንግሥት ወይም በወታደሩ ውስጥ አመፅ ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነው ። በአሁኑ ጊዜ የትናንቱ እርምጃ ውጤት ምን እንደሆነ ለማወቅ መጠበቅ አለብን ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ምን እንደሆነ አናውቅም ። ሆኖም የሆነ አይነት አመፅ እየተካሄደ ነው ። »

በአንዳንድ ዘገባዎች እንደተጠቆመው ወታደሮቹ ህገ መንግሥቱ እንዲከበርና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቀው መግለጫቸው ትናንት በኤርትራ ቴሌቪዥን እንዲነበብ አድርገዋል ። የአፍሪቃ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ማሃሪ ታደለ ማሩ የወታደሮቹ እርምጃ ለመንግሥት የማስጠንቀቂያ ደውል ነው ይላሉ ።

President of Eritrea Isaias Afewerki attends a news conference with European Commissioner for Development and Humanitarian Aid Louis Michel (not pictured) after their meeting at the European Commission headquarter in Brussels, Belgium, 04 May 2007. EPA/OLIVIER HOSLET +++(c) dpa - Report+++
Eritrea Präsident Isayas Afewerkiምስል picture-alliance/dpa

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ይህን መሰሉ የአመፅ እንቅስቃሴ መካሄዱ ሲነገር የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ። ይህ ወዴት ሊያመራ ይችላል ? ምንስ ያመለክታል ተብለው የተጠየቁት  የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ሶልመን ሲመልሱ

 « ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት አለማምጣቱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ። እኔ ግን ለውጥ ማምጣቱን እጠራጠራለሁ ። ኢሳያስ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችሉ ይመስለኛል ። ሆኖም በርግጥ ይህ እርምጃ በቅርቡ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ከድተው መኮብለላቸው ከተዘገበ በኋላ የተወሰደ  2 ተኛ  እርምጃ ነው ። ስለዚህ በራሱ በአስመራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ እየተጠናከረ የመምጣቱ ምልክቶች አሉ ። »

የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር መሃሪም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው ።

ትናንት በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ያመፁ ወታደሮች ወሰዱ የተባለው እርምጃ የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ስልሜን እንዳሉት የህዝቡ ብሶት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።

« የተደማመረ ነገር እንዳለ ይታያል የሰብአዊ መብት ይዞታው ወጣት ኤርትራውያን በግዳጅ ለውትድርና መመልመላቸውና  በአነስተኛ ክፍያም ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ በመደረጉ በርካታ ወጣት ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሌሎች የአካባቢው ሃገራት እየተሰደዱ ነው ። ስለዚህ ባለፉት 24 ሰአታት የተከናወኑት ድርጊቶች ለተፈፀሙት ሁኔታዎች እንደ ምሬት መግለጫ ሆነው ነው የሚታዩ ይመስለኛል ። ይህ እንደሚሆንም የሚጠበቅ ነው ። ሆኖም በኛ ግምት ይህ የአገዛዙ መዳከም ምልክት ነው ። »

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ