1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ መንግሥት ተስፋ የጣለበት ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻው ዘርፍ

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2009

ርካሽ የሰው ጉልበት፤ጥሬ እቃ እና ኃይል ፈላጊዎቹ የጨርቃ ጨርቅ እና የአልባሳት አምራቾች አይናቸውን በኢትዮጵያ ላይ ጥለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ባለሙያዎች "የተለጠጠ'' ያሉትን እቅድ አስተዋውቋል። እቅዱን በማስተዋወቁ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንግሥት የግንባር ሰው የሆኑት ዶ/ር አርከበ ተያዘውታል።

https://p.dw.com/p/2dX8o
Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻ የኢትዮጵያ ተስፋ?

በ100 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለው የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ ተመርቆ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ሰማያዊ ቲ-ሸርት የለበሱት የሒርዳራማኒ ሰራተኞች በዘመናዊ ማሽኖች ከአንድ ጥግ ለአሜሪካ እና ለአውሮጳ ገበያ የሚቀርቡ አልባሳት እየሰፉ ነበር። ኩባንያው ለዘጠኝ ወራት እያመረተ ነበር። ከመቶ አመታት በላይ ያስቆጠረው እና በአነስተኛ የልብስ መሸጫ የተጀመረው የስሪ ላንካው ሒርዳራማኒ  በ20 ፋብሪካዎቹ በወር አምስት ሚሊዮን አልባሳት የሚያመርት ሥመ-ጥር ኩባንያ ነው። የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ቪኖድ ሒርዳራማኒ እንደሚሉት ሌሎች የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮችን ቃኝተው በኢትዮጵያ ለመሥራት ከወሰኑባቸው ምክንያቶች መካከል አገሪቱ ያላት የሰራተኛ ኃይል እና መሰረተ-ልማት ይገኙበታል።

Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

«በአፍሪቃ እና ምሥራቅ አፍሪቃ በርካታ አገሮችን ተመልክተን ኢትዮጵያ ጥሩ የሰው ኃይል፤  ጥሩ መሰረተ-ልማት እና የተረጋጋ መንግሥት ሥላላት በዚህ ለመስራት ወስነናል። ይኸ ለወደፊቱ ፍንትው ያለ ርዕይ ይሰጠናል። የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻው ዘርፍ ረዥም አመታት ያስቆጠረ ነው። ስኬታ እንዲሆን ደግሞ እነዚህ ነገሮች ያስፈልጉታል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻ ዘርፍ ጠንካራ ትሆናለች የሚል እምነት አለን።»

ቪኖድ ሒርዳራማኒ ከሶስት አመታት ገደማ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ሲሉ ዛሬ ሐዋሳ ያረፈውን ፋብሪካ አዲስ አበባ ላይ የመክፈት እቅድ ነበራቸው። ኃሳባቸውን ያስቀየሯቸው ዶ/ር አርከበ እቁባይ ናቸው። ዶ/ር አርከበ በተለይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሥትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚያዊ እድገት እና የኢንዱስትሪያላይዜሽን ተስፋ በተለያዩ መድረኮች የሚያቀነቅኑ የመንግሥት የግንባር ሰው ሆነዋል።ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት መቀነቷን አጥብቃ የምትገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችም  የጠቅላይ ሚኒሥትሩ አማካሪ ውጥኖች ናቸው ሲባል ይደመጣል። ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከፍተኛ ሹማምንቶቻቸው በተገኙበት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርቆ ሲከፈት ጎልተው የታዩት እኚሁ ዶ/ር አርከበ ነበሩ።

30 ቢሊዮን ዶላሩ ርዕይ-2025

Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

በ100 ሔክታር የተጀመረው እና በመጪዎቹ አመታት ወደ 300 ሔክታር ይሰፋል የተባለለት የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራቾች የታቀደ ነው። የአሜሪካ፤ ስዊድን፤ቻይና፤ስሪ ላንካ፤ሕንድ፤ሖንግ ኮንግ እና ኢንዶኔዥያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራቾች ሐዋሳ ላይ ሊከትሙ አቅደዋል።

ዲያና ፋን ደር ፖልስ የኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻ ዘርፍ በቅርብ የሚያውቁ ባለሙያ ናቸው። ወ/ሮዋ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻ ዘርፍ ያሉትን የንግድ እድሎች የሚተነትን ሰነድ አዘጋጅተው አቅርበዋል። ሰነዱ የዘርፉን መልካም አጋጣሚዎች እና ማነቆዎች የአገር ውስጥ እና የውጭ የገበያ እድሎች እንዲሁም ያሉበትን የጉሙሩክ አሰራር እና የማጓጓዣ ችግሮች ይፈትሻል። የአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ ምርት እና የግብይት ትሥሥር ባለሙያዋ ዲያና ፋን ደር ፖልስ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጥረት ቢያደንቁም በርካታ ችግሮች ከፊቱ መደቀናቸውን አልሸሽጉም።

«የኢትዮጵያ የማምረቻ ዘርፍ ገና ጀማሪ ነው። የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እና ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠርን በመሳሰሉ አሳማኝ ምክንያቶች ዘርፉን ለማበረታታት መንግሥት የሚያደርገው በርካታ ጥረት መኖሩ የሚመሰገን ነው። ባንግላዴሽ እና ፓኪስታንን በመሰሉ ሌሎች አምራች አገሮች እንዲህ አይነት የመንግሥት ድጋፍ የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ሳቢ የመዋዕለ-ንዋይ እቅድ በማቅረቡ የውጭ ባለወረቶችን ትኩረት መሳብ ችሏል። ነገር ግን ወደ ማምረቻዎቹ ዝቅ ብለን ብንመለከት አሁን የሚመረተው ገና መሰረታዊ የሚባል ነው። ይኸ ደግሞ በግብዓቶች አቅርቦት ችግር የተፈጠረ ነው። ምክንያቱም አስፈላጊ ግብዓቶች እና ጥሬ እቃዎች የሉም። ሌላው ነገር ዘርፉን በማሳደግ ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደ አውሮጳ ኅብረት ገበያ መላክ ብትፈልግ የተቀመጠውን የሰራተኛ ሕግ መስፈርት ማክበር አለባት። ጉዳዩ በአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን እና በዓለም የንግድ ድርጅት ውይይት የተደረገበት ነው።»

ወትሮም እጅግ የተለጠጡ እቅዶች ይዞ ብቅ የሚለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. ከጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት የውጪ ንግድ 30 ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ሕልም አለው። የታሰበውን ለማሳካት አገሪቱ ወደ ውጭ የምትጭነውን የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርት አሁን ካለው በ300 እጅ ማሳደግ ይጠበቅባታል። አቶ አርከበ የአስር አመታቱን የመንግሥታቸው እቅድ 'ርዕይ 2025' ሲሉ አስተዋውቀውታል።

Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የጠቅላይ ሚኒሥትሩ አማካሪ ጀስት ስታይል ከተባለው የፋሽን መፅሔት ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ በአመት የ30 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጨርቃ ጨርቅ እና የአልባሳት ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መንግሥታቸው የወጠነው ውጥን 'ፈታኝ' ቢሆንም 'እናሳካዋለን' ሲሉ ተናግረዋል። "ቪየትናም እና ባንግላዴሽ ካሳኩት እኛ ከቶ እንዴት ይሳነናል?'' የሚል እምነት አላቸው ዶ/ር አርከበ። የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርት እና የግብይት ትሥሥር ባለሙያዋ ዲያና ፋን ደር ፖልስ ግን አሁን 100 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚያወጣ ምርት ለውጭ ገበያ የሚያቀርበውን ዘርፍ በ300 እጥፍ ለማሳደግ የተያዘው ውጥን አልተዋጠላቸውም። እቅዱንም "የተለጠጠ" ይሉታል።

«አይመስለኝም። እጅግ የተለጠጠ እና እውነታውን ያላገናዘበ እቅድ ነው። ምክንያቱም ለ2025 የቀረው ስድስት ወይም ሰባት አመት ብቻ ነው። አገሪቱ ስምንት በመቶ ብታድግ እንኳ እጅግ ብዙ ነው። ከሌሎች በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ጋር ብናነፃጽር ከ4-8 ከመቶ ኤኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ማምረቻ ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ከቪየትናም፤ቻይና ወይም ባንግላዴሽ የበለጠ እጥፍ መሆን አለበት ማለት ነው። በስድስት አመታት ውስጥ በአራት እጥፍ እንዲያድግ ወይም ከዘርፉ የውጭ ንግድ 500 ሚሊዮን ዶላር እንዲገኝ ቢታቀድ አሳማኝ ይሆናል። ለዚህ እቅድ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰቱ ከፍ ማለት ይጠበቅበታል። ከሕግ ማዕቀፍ አኳያም የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ ማሻሻያዎች ማድረግ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ በሥራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች አነስተኛ እድሜ ገደብ ማስቀመጥ ወይም አሁን የሌለውን የሰራተኛ ሕግ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ስለዚህ የሌሎች ኤኮኖሚዎች እድገትን ስንመለከት የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀደው ቁጥር የተለጠጠ እና ተዓማኒ አይደለም።»

በኢትዮጵያ ለሰራተኛ ፤የጥሬ እቃ እና ኃይል የሚከፈለው አነስተኛ ዋጋ አገሪቱ የውጭዎቹን ባለወረቶች ቀልብ ለመግዛት እንዳገዛት የዘርፉ ባለሙያዎች የፃፏቸው ትንተናዎች ይጠቁማሉ። ማቅለሚያ እና ኬሚካሎችን ጃፓን ፤ ቻይና ፤ ሕንድ ፤ ፓኪስታን ፤ ስዊትዘርላንድ ፤ ቱርክ እና ጀርመንን ከመሳሰሉ አገሮች ትሸምታለች። አገሪቱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ጥጥ የማምረት እምቅ አቅም እንዳላት ይነገራል። ይሁንና በጥራት ያለው ዘር እና በጸረ-ተባይ እጦት ወቅታዊው ምርት የሚታሰበውን ያክል አይደለም። የዩ.ኤስ ኤይድ መረጃ እንደሚጠቁመው በጎርጎሮሳዊው 2015/16 የበጀት አመት ኢትዮጵያ ያመረተችው 38,000 ሜትሪክ ቶን ብቻ ነበር። ኢትዮጵያ ከጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት  ማምረቻው ዘርፍ ከፍ ያለ ገቢ ለማግኘት የጥጥ ምርቷን ማሳደግን ጨምሮ በርካታ አሰራሮቿን በቅጡ ማደራጀት እንዳለባት ዲያና ፋን ደር ፖልስ ይመክራሉ።

Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

«በዚህ ደረጃ አገሪቱ ለምርት የምታበረክተው አስተዋፅዖ የሰራተኛ ጉልበት ብቻ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ብቸኛው መፍትሔ የጥሬ እቃ የሚገባበትን ሎጂስቲክስ (ማጓጓዣ) በማመቻቸት ወይም ደግሞ ለዘርፉ ግብዓት የሚያቀርብ የኢንዱስትሪ ሰንሰለት በማበጀት ነው። ኢትዮጵያ ለዘርፉ ግብዓት የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች ልታቋቁም ትችላለች። ነገር ግን ይኸ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው። በኢትዮጵያ ያለውን የጥጥ ምርት ብንመለከት አገሪቱ ካላት የማምረት አቅም 8 በመቶ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ይመስለኛል። መሬቱን ለጥጥ ምርት ዝግጁ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት በመጀመሪያ ከ9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልገዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዘርፉን በራሷ ጥሬ እቃ እስክታደራጅ ድረስ ላሉት አስር አመታት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ጥሬ እቃ ከውጭ  የምታስገባበትን እና ምርት ወደ ውጭ የምትልክበትን ማጓጓዣ ማቀላጠፍ ነው።»

እንደ ባለሙያዋ ገለጣ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት የምርት ሰንሰለት "ተሰብሯል" አሊያም የተሟላ አይደለም። የጥሬ እቃ እና ኬሚካሎች ግብዓት አለማሟላት፤ ብዙ መሻሻሎች የሚያሻው የጉምሩክ አሰራር እና የማጓጓዣ ጉዳይ ባለሙያዋ የጠቀሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው። ወ/ሮዋ "መንግሥት እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ቅድሚያ ሊሰጣቸው" ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የስሪ ላንካው ቪኖድ ሒርዳራማኒ ዘርፉ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት አላጡትም። ኢትዮጵያ ችግሮቿን ፈትታ ከዘርፉ ዳጎስ ያለ ገቢ ለማግኘቷ ግን ጥርጣሬ የላቸውም።

«ይህ የትልቅ ኢንዱስትሪ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ መናገር እንፈልጋለን። ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ከ30 እስከ 50 ባሉ አመታት አልባሳት ወደ ውጭ በመላክ ከአፍሪቃ ምን አልባትም በዓለም ቀዳሚ እንድትሆን መሰረቱን መጣል እንሻለን።»

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ