1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የወዲያነሽ» እና የ«ጉንጉን» ደራሲ

እሑድ፣ መጋቢት 9 2010

አንጋፋ ደራሲ እና አርታኢ ናቸው። መምህር መባሉን ነው የሚመርጡት፣ከእድሚያቸው አብዛኛውን በመምህርነት በማሳለፋቸው። ኃይለ መለኮት መዋዕል ይባላሉ። በአንባብያን ዘንድ ተወዳጅነትን ባተረፉት ሁለት ረዣዣም ልብወለዶቻቸው ይበልጡን ይታወቃሉ። ከአንባብያን ጋር ያስተዋወቃቸው በ1978 ዓም የታተመው «የወዲያነሽ» ረዥም ልቦለድ መጽሐፋቸው ነው።

https://p.dw.com/p/2uUAM
Symbolbild Buch Bücher Lesen
ምስል Colourbox

«የወዲያነሽ» እና የ«ጉንጉን»ደራሲ

«የወዲያነሽ» ረዥም ልቦለድ ከታታመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በኢትዮጵያ ራድዮ ተተርኳል። «የወዲያነሽ» ደራሲ ኃይለ መለኮት ከዚያ በፊትም ግጥም እና ተውኔቶችን ይጽፉ ነበር። የሚጽፉትም ከትውልድ አካባቢያቸው ከሰሜን ሸዋ ወደ  አስመራ ከሄዱ በኋላ መናገር በጀመሩት በትግርኛ ቋንቋ ነበር።

ሰሜን ሸዋ ይፋት የተወለዱት አቶ ኃይለ መለኮት መዋዕል እስከ አራተኛ ክፍል ኮምቦልቻ ከተማሩ በኋላ ቀሪውን የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አስመራ ነው የተከታተሉት። ወደ ስነ ጽሁፍ ዓለም የተሳቡትም የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ አንስቶ ነበር። ለዚህም ባለውለታዎቻቸው የያኔዎቹ አስተማሪዎቻቸው እና አባታቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በመምህርነት የተሰማሩት አቶ ኃይለ መለኮት እንደሚሉት ደራሲ እሆናለሁ ብለው አስበውም አያውቁም። ሆኖም በ1960ዎቹ አጋማሽ የሠራተኛ ማህበር እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ መሆን ከጀመሩ በኋላ የሚያቀርቧቸው ጽሁፎች ተቀባይነት ሲያገኙ መጻፍ እንደምችል ተረዳሁ ይላሉ ። ከዚያም የመጀመሪያውን ረዥም ልብወለድ ድርሰታቸውን የወዲያነሽን ጻፉ። በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተውን «የወዲያነሽ»ን መጻፍ ጀመሩት ግን ረዥም ልብወለድ ይሆናል ብለው አልነበረም። ወደ ረዥም ልቦለድ ያደገው «የወዲያነሽ» ለህትመት መብቃቱ የአቶ ኃይለ መለኮት ትልቁ ደስታቸው ነበር። መፀሐፉ መታተሙ ብቻ ሳይሆን ሳያስቡት ተፈላጊ እና ተነባቢ መሆኑም ያልጠበቁት ነበር።

ከ«የወዲያነሽ» ቀጥሎ «ጉንጉን» የተባለ ረዥም ልብ ወለድ ደረሱ ። ለዚህ ድርሰት ምክንያት የሆናቸው ደግሞ የተወሰኑ ደራሲዎች በሚገናኙበት የንባብ ክበብ ለማቅረብ በአጭሩ የደረሱት ጽሁፍ ነበር ።ጉንጉንም እንደ የወዲያነሽ በራድዮ ተተርኳል። «ጉንጉን» በ1982 ዓም ነበር የታተመው።

ከ23 ዓመት በኋላ ደግሞ «እንኪያ ሰላንትያ» የተሰኘውን መፀሐፍ አሳተሙ። ከዚያ በፊት እርሳቸውና ሌሎች የስነ ጽሁፍ ባለሞያዎች ያዘጋጇቸው የግብረ ገብ ማስተማሪያ መጻህፍት ከባድ መሆናቸውን ከተገነዘቡ በኋላ ተማሪዎች በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ ብለው ባሰቡት በእንኪያ ሰላንትያ ማዘጋጀታቸውን ይናገራሉ። በአስተማሪነት ዘመናቸው መደምደሚያ ላይ ያሳተሙትን ይህን መጸሀፍ ለተማሪዎች የሰጠሁት ገጸበረከት ይሉታል።  

ኂሩት መለሰ

ልደት አበበ