1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳንና የተመድ ማዕቀብ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2007

ዠኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ የሚገኘው የተመ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ተፈፀመ የተባለውን አስከፊ የመብት ጥሰት የሚያጣራ አንድ ቡድን ለመላክ ወሰነ።

https://p.dw.com/p/1FsfA
Afrika Bildergalerie Kindersoldaten im Süd-Sudan
ምስል DW/A. Stahl

47 አባል ሀገራት የተጠቃለሉበት የምክር ቤቱ ባለፈው ሀሙስ ያስተላለፈው ውሳኔ በርካታ የመብት ጥሰቶችን የሚያሳይ፣ ማለትም ሲቭሎችን ሆን ብሎ የመግደል፣ ከመኖሪያ አካባቢቸው በጅምላ ማፈናቀል፣ የወሲብ ጥቃት እና ሕፃናትን በግዳጅ ለውጊያ መመልመልን ጭምር የሚያሳይ ረጅም ዝርዝር አውጥቷል። ዩኤስ አሜሪካ እና ብሪታንያ ያረቀቁትየውሳኔ ይዘት የአፍሪቃውያት ሀገራትን ድጋፍ ያገኝ ዘንድ ብዙ ለውጦች ተደርገውበታል። ረቂቁን ውሳኔ ለምክር ቤት ያቀረቡት በምክር ቤቱ የዩኤስ አሜሪካ አምባሳደር ኪት ሀፐር በደቡብ ሱዳን የሚታየውን ጊዚያዊ ሁኔታ በዓለም እጅግ አስከፊ መሆኑን በመግለጽ፣ ምክር ቤቱ ይህን ግዙፍ የመብት ጥሰት በቸልታ ሊያልፈው እንደማይገባ አሳስበዋል።

Symbolbild Frauen Opfer Konflikt Südsudan
ምስል GetttyImages/AFP/C. Lomodon

በሲቭሉ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ላይ የመብት ጥሰት፣ የጦር ወንጀል እና በስብዕና አንፃር ወንጀል የፈፀሙ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጀመረው ጥረት ላይ የደቡብ ሱዳን መንግሥትም እንዲተባበር የምክር ቤቱ ውሳኔ ጠይቋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይህንን ውሳኔ የደረሰው ያለሙ መንግሥታት ከፍተኛ ወሳኝ አካል የሆነው የተመ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ብሔራዊውን መረጋጋት ስጋት ላይ ጥለዋል ባላቸው በሶስት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጦር ጀነራሎች እና በሶስት ከፍተኛ የተቀናቃኙ ያማፅያን ጦር አዛዦች ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ካስተላለፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው። በስድስቱ የጦር ኃላፊዎች ላይ የተጣለው የዝውውር እና ንብረታቸው የማይንቀሳቀስበት እገዳ የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እስከቀጠለ ድረስ እንደፀና ይቆያል። ስድስቱ ከፍተኛ የጦር ኃላፊዎች ከሱዳን ተገንጥላ ነፃ መንግሥት ካቋቋመች ሰሞኑን አራተኛ ዓመት በሚሆናት ደቡብ ሱዳን ውስጥ በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በተቀናቃኛቸው የቀድሞ ምክትላቸው ሪየክ ማቸር ደጋፊዎች መካከል እአአ ከታህሳስ 2013 ዓም ወዲህ በቀጠለው የርስበርስ ጦርነት ላይ በሲቭሉ ላይ ተፈፀመ በተባለው የመብት ጥሰት ሰበብ ማዕቀብ የተጣለባቸው የመጀመሪያዎቹ ናቸው። የውሳኔው ትክክለኛነትን ያመለከቱት በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የዩኤስ አምባሳደር ሳማንታፓወር ሰላምን የሚያደፈርሱ በኃላፊነት በሕግ ከመጠየቅ እንደማያመልጡ አስረድተዋል።

Kindersoldaten in Südsudan
ምስል AFP/Getty Images/Ch. Lomodong

የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ፖሊሲ ጥናት ተቋም «ኢናፍ» የተሰኘው ፕሮዤ ተንታኝ አቻያ ኩማር ይህንኑ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የማዕቀብ ውሳኔ በደቡብ ሱዳን ለሚፈፀመው ግዙፍ የመብት ጥሰት ተጠያቂዎችን በኃላፊነት ወደ መጠየቁ የሚያመራ የመጀመሪያ ዋነኛ ርምጃ ነው በሚል አሞግሰዋል። ይሁንና፣ አሁን የተጣለው ማዕቀብ በደቡብ ሱዳን የቀጠለውን የርስበርስ ጦርነት በማብቃቱ ረገድ አንዳችም ሚና እንደማይኖረው ነው ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው በዚችው ሀገር የተሠማራው የተመድ ሰላም አስካባሪ ጓድ የቀድሞ ኃላፊ ፒተር ሹማን ያስታወቁት።

«በኔ አስተያየት፣ ማዕቀቡ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱን ደካማነት ነው ያጎላው። ምክር ቤቱ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ፖለቲካዊ ርምጃ ለመውሰድ፣ ብሎም፣ በአመራሩ ላይ ግፊት ለማሳረፍ አይፈልግም። በዚህም የተነሳ ነው አሁን በተባሉት የጦር ኃይሉ መሪዎች ላይ ማዕቀብ የጣሉት። የማዕቀቡ ውሳኔ ለምን ሶስቱን የጦር ኃይል መሪዎች እንደነካም ሆነ፣ ማዕቀቡ ይነሳላቸው ዘንድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ቤቱ አንዳችም መግለጫ አልሰጠም። ውሳኔው ግልጽነት የጎደለው ነው።ምክር ቤቱ በመንግሥቱ እና በተቃዋሚዎቹ መካከል ድርድሩ እንዴት መቀጠል እንደሚፈልግ ግልጽ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። »

አንዳንድ ያካባቢውን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚናገሩት፣ ከፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ማዕቀብ ጎን፣ የዚችው ሀገር መንግሥት የተቋቋመበትን ሁኔታ ባስገኘው በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ፣ በ«ኤስ ፒኤል ኤም» መካከል እአአ በ2005 ዓም በተደረሰው የሰላም ስምምነት ላይ ቁልፍ ሚና የተጫወተችው ዩኤስ አሜሪካ የደቡብ ሱዳን ውዝግብ ያበቃ ዘንድ ልዩ ኃላፊነት እንዳለባት አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ። እንደ ተንታኞቹ አስተያየት፣ ዩኤስ አሜሪካ ለዚችው ሀገር ከምትሰጠው ሰብዓዊ ርዳታ ጎን ፣ ተቀናቃኞቹ ወገኖች ለማስታረቅ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ «ኢጋድ» ሸምጋይነት የተጀመረውን ድርድር በቀጥታ ዲፕሎማሲ በመደገፍ ወይም በፖለቲካው ዘርፍ ከፍተኛ ተሰሚነት ባላቸው የአመራሩ አባላት ላይ ጠንካራ ማዕቀብ በመጣል ሀገሪቱ የምትረጋጋበትን ሂደት ማፋጠን ይጠበቅባታል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ