1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን ተስፋና ችግርዋ

ሰኞ፣ ሐምሌ 4 2003

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዘገበዉ ካለፈዉ ጥር እስከ ሐምሌ በተቆጠረዉ ስድስት ወራት ዉስጥ ብቻ በጎሳና በፖለቲካ ግጭት ከሁለት ሺሕ ሰወስት መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ይሕን ለማስወገድ የጁባዎችን አርቆ አሳቢነት፥ የጎረቤቶቻቸዉን ቅንነት፥ የአለም አቀፉን ሐቀኛ ድጋፍ ይጠይቃል

https://p.dw.com/p/RZ74
ደቡብ ሱዳን ተስፋና ችግርምስል picture alliance/dpa

የአሮጌይቱ ክፍለ-ዓለም ትልቅ ልጅ ሁለት ሆነች።አዲስ ሐገር ተወለደች።የአዲሲቱን ሐገር ልደት አስታከን-ላፍታ ሱዳን-ደቡብ፥ ሱዳን ሰሜን፥ አፍሪቃ ዓለም እንላለን።አብራችሁኝ ቆዩ።

«እኛ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጥን፥ በደቡባዊ ሱዳን ሕዝብ ፍላጎት በሕዝብ የተወከልን የሕዝብ ተወካዮች የእራስን እድል በራስ ለመወሰን በተደረገዉ ሕዝበ-ዉሳኔ ዉጤት መሠረት፥ እነሆ ደቡባዊት ሱዳን ከዛሬ ጀምሮ ነፃና ሉዓላዊት ሐገር መሆንዋን አዉጀናል።»

ጀምስ ዋኒ ኢጋ።-የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ።እናት አፍሪቃ ከትልቅ ግማደ አካሏ ላይ እልቂት ፍጅት እንደለበቃት ሐምሳ ዘመን አርግዛ፣ በተስፋ-ቀቢፀ ተስፋ ምጥ አምስት አመት ተንቆራጥጣ፣ ሐምሳ-አራተኛ ልጇን ተገላገለች።እና ጁባ ፈነደቀች።

ካርቱም አረረች።ግን ፈገገች።-እንደማሽላ።እልቂት-ፍጅቱን፣ ተስፋ ቀቢፀ ተስፋዉን ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የዘወረዉ ዓለም ተደሰተ።እንኳን ደስ አላችሁ።ካንገትም-ይሁን ካንጀት በትልቅ ማሕበሩ ዋና ፀሐፊ በፓን ጊ ሙን አማካይነት ጁባን መረቀ።እንትፍ---እንትፍ።እደጊ-ተመንደጊ።አይነት።

«ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር፥ ፕሬዝዳንት ዑመር ዓል-በሽር እንኳን ለዚሕ አበቃችሁ።እዚሕ በመድረሳችሁ አድናቆቴን እገልፃለሁ።ሁለታችሁም ከባድ ዉሳኔና ማካካሻዎችን አሳልፋችኋል።ዛሬ ሁለታችሁም እዚሕ መገኘታችሁ ለሰላምና ለወዳጅነት ያላችሁን ቁርጠኝነት መስካሪ ነዉ።»

ከፒራሚድ እነፃቸዉ እስከ ፊደል ቀረፃቸዉ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ግራ ቀኝ ያኑሩት ቅርሥ ለጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤትነታቸዉ ግልፅ ምስክር ነዉ።ከሜድትራንያን ባሕር ደቡባዊ ጠረፍ-እስ ቀይ ባሕር ደቡባዊ ዳርቻ ዘርግተዉት የነበረዉ ጠንካራዉ የኩሽ ሥርወ-መንግሥት ሐይለኛ ተዋጊ፣ ብልሕ ገዢነታቸዉን መስካሪ ነዉ።ኑብያ-ወይም ሱዳኖች።የዚያኑ ያሕል ሱዳኖችን በቅርብ የሚያዉቁ፣ ባሕል፣ ታሪካቸዉን ያጠኑ እንደሚሉት ደግ፣ ገራገር የዋሕ ብጤዎችም ናቸዉ።

Südsudan Unabhängigkeitserklärung NO FLASH
ምስል dapd

በቅዳሜዉ የደቡብ ሱዳን የነፃነት ክብረ በዓል ላይ የተገኙ አንድ የምዕራብ ሐገር ባለሥልጣን ለቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደነገሩት ሱዳን በ1956 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጠጠር ነዉ) ከአንግሎ-ግብፅ ቅኝ አገዛዝ ነፃነትዋን ስታዉጅ ሱዳኖች ያዘጋጁ፣ የዘመሩትን ብሔራዊ መዝሙር እራሳቸዉ ሱዳኖች እንደ አዲስ ነፃ ሐገር ልዩ መለያ አልተቀበሉትም ነበር።

በደቡብ ሱዳን ነፃነት ሠበብ የብሪታንያዉ ማሠራጪያ ጣቢያ የጠቀሳቸዉ ባለሥልጣን ያሉትን ሳነብ ሥለ ሱዳኖች ያጠኑና ለረጅም ጊዜ ሱዳን የኖሩ ኢትዮጵያዊ በደቡብ ሱዳን ሰበብ ሥለ ሱዳኖች የነገሩኝን አስታወሰኝ።

«እንግሊዞች ሱዳኖችን IBM ነበር የሚሏቸዉ።»አሉኝ ሰዉዬዉ።IBM?-አልተናገርኩም።ግን ጠየቅሁ ራሴን።ኮፒዉተሩን።እና ኮፒዉተር አምራች ኩባንያዉን።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ለቅኝ ተገዢዎቻቸዉ----እያልኩ ላስብ ስቃጣ «International Business Machine ማለት አይደለም» ብለዉ ገላገሉኝ-እንዳልገባኝ የገባቸዉ እንግዳዬ።ሱዳኖች በየንግግራቸዉ መሐል «ኢንሻ አላሕ ቡክራ ማአሌሽ» ማለትን በጣም ይደጋግሙታል።» ቀጠሉ እንግዳዬ።ትርጉሙ አልከበደኝም።«ፈጣሪ ካለ፣ነገ፣ ችግር የለም» እንደማለት ነዉ።

መልዕክቱ «ማድረግ የሚገባቸዉን እራሳቸዉ በሰአቱ ከማድረግ ይልቅ ለፈጣሪ ይተዉታል፣ ለነገ ያሳድሩታል፣ ደሞ በዚያ ላይ ችግር የለም ይላሉ።በዚሕ ሰበብ ነዉ እንግሊዞች አረብኛዉን በእንግሊዝኛዉ ምሕፃረ ቃል ቀይረዉ IBMያሏቸዉ።» አሉ ሰዉዬዉ።

ስድብ-ምፀቱ የየደረሱበት ሐገር ሕዝብን በባርነት የሚገዙ-የሚሸጡት፣ የሚገድሉ፣ የሚያግዙ፣ የሚያሰድዱት ፥ እሁለት ሰወስት የከፋፈሉት የቅኝ ገዢዎች ባይሆን ኖሮ በርግጥ ከልብ ባሳቀ ነበር።ቢቢሲዉ የጠቀሳቸዉ ምዕራባዊ ባለሥልጣን እንደሚሉት ሱዳን ነፃነትዋን ስታዉጅ ካርቱም ላይ ከነረበዉ ድግሥ፥ ሥነ ሥርዓት ይልቅ የቅዳሜዉ የጁባዉ የተዋጣለት ነበር ይላሉ።በተለይ ይላሉ ባለሥልጣኑ «ደቡብ ሱዳኖች ብሔራዊ መዝሙር ባንዲራቸዉን ጠንቅቀዉ ማወቃቸዉ እራሳቸዉን ለማስተዳደር በቅጡ ለመዘጋጀታቸዉ ምስክር ነዉ።»


ብሔራዊ መዝሙሩም-ተዘመረ።ተጨበጨበለትም።

በርግጥ ደቡብ ሱዳኖች ለቅዳሜዉ ድግስ በቅጡ ተዘጋጅተዉ ነበር። ከቻይና የተገዛዉ ባለ ሥድስት ቀለም ባንዲራ ጁባ የደረሰዉ ከሳምንታት በፊት ነበር።ባንዲራዉ ግን የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድን፥ የሱዳን ነፃ አዉጪ ጦር ወይም ንቅናቄ ያሁኑ ገዢ ፓርቲ የ(SPLA/M) አርማ ነዉ።የቀድሞዉ ተዋጊ ቡድን አርማ፥ ተዋጊዉ ቡድን እንደ መስተዳድር እስካሁን ስድስት አመት በገዛት፥ እንደ ሐገር ወደፊትም በሚገዛት አዲስ ሐገር ብቻዉን ባደራጀዉ ድግስ መሐል ሲሰቀል ታዳሚዉ የማይጨፍ-የማይዘፍንበት ምክንያት የለም።

የምዕራባዊዉ ባለሥልጣንን አስተያየትን ማጣጣል በርግጥ ሥሕተት ሊሆን ይችላል።ግን ከመዝመሩ ጋር የአንድ ተዋጊ ሐይል ወይም ገዢ ፓርቲ አርማ አንደ ነፃ ሐገር መለያ መሠቀሉ አዲሲቱ ሐገር ከሷ በፊት አዲስ የነበሩ ሐገራትን ስሕተት የመደግሟ፥ የዛሬ አሮጌዎችን ገደዳ ፋና የመከተሏ ምልክት እንዳይሆን-ሊያሰጋ ይገባል።

የሰሜን ሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አል-በሽር እንዳሉት ሱዳኖች ለሳላም ሲሉ ሱዳንን ለሁለት ከፍለዋታል።ይሁንና ጁባ ላይ ሲደገስ፥ ሲዘመር፥ሲጨፈር፥ የሁለቱ ሱዳኖች አዋሳኝ ድንበር የአብዬ ግዛት ሠላም ግን በዉጪ ጦር መጠበቅ እንደተጠበቀ ነዉ።ኮርዶፋን የተፋላሚ ሐይላት ጦር ሐይላት ግራ-ቀኝ እንደተጋጩ-እንደተፋጠጡባት ነዉ።

እርግጥ ነዉ ካጭር ፋታ ባለፍ ግማሽ ምዕተ-አመት ያሕል ያስቆጠረዉ ጦርነትና የጦርነቱ መዘዝ የሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ሕይወት አጥፍቷል።ከሰወስት ሚሊዮን በላይ አፈናቅሏል።ወይም አሰድዷል። ሱዳንን ለሁለት መግመሱ አል-በሽር እንዳሉት፥ ብዙዎችም እንደሚያምኑት የእስካሁን የሕዝብ ስቃይ መከራ ማስቀረቱ አያጠያይቅም።መልክ ባሕሪዉን የቀየረ ግጭት-ጦርነት ላለመነሳቱ ግን ነፃነቱ በምንም መንገድ ዋስትና ሊሆን አይችልም።

የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ጉዳይ አጥኚ ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት ደግሞ መገንጠል ግጭት ጦርነትን ለማስወገድ የሚኖረዉ አስተምሕሮት ዳግም ሊጤን ይገባዋል።

«አንዱ መጤን ያለበት የመገንጠል ጉዳይ ነዉ።የአፍሪቃ ሕብረትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማሕበረሠብ በዚሕ ጉዳይ ላይ ሲበዛ ወግ አጥባቂዎች ናቸዉ።ከዚሕ በፊት ኤርትራ አሁን ደግሞ ደቡብ ሱዳን መገንጠላቸዉ ይሕ አደጋ ወይም የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስወገድ ጠቃሚ ሐብት መሆን አለመሆኑ ዳግም ሊነጋግር፥ ሊያጠያይቅም ይገባል።እኔ ለዚሕ መልስ የለኝም።ምክንያቱም ጉዳዩ በጣሙን አፍሪቃ ዉስጥ ባሉት የተለያዩ ግጭቶች ሁኔታ ጋር በጣም የተቆራኘ በመሆኑ።»

ከሆሊዉድ የፊልም አክተሮች፥ እስከ ዋይት ሐዉስ መሪዎች ለነፃነትዋ የታገለሉላት፥ከአረብ ሊግ እስከ አዉሮጳ ሕብረት፥ ከአፍሪቃ ሕብረት እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዲስ ሐገርነቷን ያፀደቁላት ደቡብ ሱዳን ከብዙ ጊዜ በላይ እንደተባለዉ የነዳጅ ዘይት ሐብት አላት።የእስከ ቅዳሜዋ አንዲት ሱዳን በቀን ከምታመርተዉ አራት-መቶ ሺሕ በርሚል ነዳጅ ሰማንያ በመቶ ያሕሉ የሚመረተዉ ከደቡብ ሱዳን ነዉ።

ይሕ ማለት ሰሜን ሱዳን አብዛኛ ሐብቷን አጣች ማለት አይደለም።ሱዳን ባጠቃላይ እስካሁን ያልተነካ ስድስት ቢሊዮን በርሚል ቅምጥ የነዳጅ ሐብት አላት።አብዛኛዉ ነዳጅ ሰሜን ምዕራብ፥ በአባይ ሰሜናዊ ተፋሰስ እና በቀይ ባሕር ጠረፍ አካባቢ ነዉ-ያለዉ።

ብቻ ደቡብ ሱዳን ሐብታም ናት።ግን ርዕሠ-ከተማዋ ጁባ እንኳን አንዲት ጥርጊያ መንገድ ነዉ ያላት።በቆዳ ስፋት ፈረንሳይ ልታክል ትንሽ ነዉ የሚቀራት።ነዳጅዋን ወደ ዉጪ የምትልክበት የራስዋ ወደብ የላትም።ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝቧ ዘጠና አራት ከመቶዉ የቀን ገቢዉ ካንድ ዶላር በታች ነዉ።በእርግዝና እና በወሊድ ችግር በሚኖቱ እናቶች ቁጥር የሚስተካከላት የለም።ሰማንያ አራት ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች መይም ናቸዉ።አንድ ዩኒቨርስቲ አላት።ጁባ ዩኒቨርስቲ።አብዛኞቹ ልጆች ግን ትምሕር ቤት አልገቡም።

እና ደሐ ናት የድሆች ደሐ።ድሕነቷን ለማቃለል ብቸኛ ገቢዋ የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ነዉ።ያን ለማድረግ ግን ነፃነት ማወጅ ብቻ በቂ አይደለም በሁለት እግሯ የቆመች ሐገርነቷ ነዉ-ወሳኙ።ደቡብ ሱዳን የሚገጥማትን ችግር ለማስወገድ ከጎኗ እንደሚቆሟ የዓለም ሐብታም ሐያል ሐገራት አረጋግጠዋል።ቀዳማዋ-ያዉ የዓለም ቀዳሚዋ ናት።ዩናይትድ ስቴትስ።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሐገሪቱ አምባሳደር ሱዛን ራይስ አረጋገጡ።

«የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሕዝብ ዘንድ እዉነተኛ ፥ ዘላቂና ተሻራኪ ወዳጅ እንዳላት የደቡብ ሱዳን ወዳጆችና ሕዝቧ ያዉቃሉ።»

የዓለም ገንዘብ ድርጅት፥ የአለም ባንክ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ የአፍሪቃ ሕብረት ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት በጋራና በተናጥል ቃል-እንደገቡት የጁባ መሪዎች ሐገራቸዉን ሐገር ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ይደግፋሉ፥ይረዳሉም።

ይሕ ሁሉ ባንድ ካበረ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክን በሁለት እግሯ የቆመች ሐገር ማድረግ አይገድም።ግን ብዙ ድካም፥ ያላሰለሰ ጥረት፥ እና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።ምክንያቱም ፕሮፌሰር ማርሻል እንደሚሉት ደቡብ ሱዳን ከመጀመሪያዉ ጀምሮ መገንባት አለባት።

«ደቡብ ሱዳን ዳግም የምትገነባ ሐገር አይደለችም።ከመጀመሪያዉ የምትገነባ እንጂ።ይሕ ደግሞ በራስዋ በሕዝቧ መካካል ወይም በሕዝቧና በመንግሥቷ መካከል መጥፎ ቅራኔ ሊያስከትል ይችላል።»

በፌስታ-ፈንጠዝያዉም መሐል በዉስጥ ቅራኔ መጠመዷ ነዉ-ጉዱ።በሁለት ሺሕ አምስት በተፈረመዉ አጠቃላይ ስምምነት መሠረት የቀድሞዉ አማፂ ቡድን ደቡብ ሱዳንን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አስተዳደሩን የሚቃወሙ ሰባት ቡድናት አመፅዉበታል።አብዛኛ ሕዝቧ የባሕላዊ እምነት ተከታይ ነዉ።

ባሕላዊ እምነት ተከታዩና በቁጥር የሁለተኛዉን ደረጃ በሚይዘዉ በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ተከታዩ መካካል ያለዉ የኑሮ ደረጃ፥የምጣኔ ሐብት፥ የትምሕርትና የሥልጣን ተባለጥ የሁለቱን ወገኖች ግንኙነት በቅሬታ የተሞላ አድርጎታል።ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ የዲንካ ጎሳ ነዉ።ኙዌሮች ሁለተኛዉን ደረጃ ይይዛሉ።የሁለቱ ጎሳ ልሒቃን የጠላቴ ጠላጥ---- ወዳጄ ነዉ-የሚል ፖለቲካ-ማሕበራዊ ፈሊጥ ቢያስተሳስራቸዉም ተራዉ ሰዉ በግጦሽ መሬት፥ በከብት ሐብት እና ሰበብ በየጊዜዉ እንደተጋጨ እንደተጋደለ ነዉ።


ዲንካዎች የሚበዙበት የቀድሞዉ አማፂ ቡድን የአስተዳዳሪነቱን ሥልጣን ከያዘ ወዲሕ ኙዌሮችን ገሸሸ ገለል ማድረጉ ወትሮም በቅጡ ያልጠገገዉን ደም አፋሳሽ ጠብ እንዳያንረዉ ያሰጋል።ዓለም በሰሜንና ደቡብ ሱዳኖች መካካል አቤዬ ላይ የተፈጠረዉን ግጭት ለማርገብ ሲጣደፍ፥ የእነ ጆርጅ ክሉኒ ሳይተላይት አብዬ የሚገባ የሚወጣዉን የሰሜን ሱዳን ጦር ምስል-ቁጥር ሲመዘግብ ደቡብ ሱዳኖች በጎና በፖለቲካ ግጭት ያልቁ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዘገበዉ ካለፈዉ ጥር እስከ ሐምሌ በተቆጠረዉ ስድስት ወራት ዉስጥ ብቻ በጎሳና በፖለቲካ ግጭት ከሁለት ሺሕ ሰወስት መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ይሕን ለማስወገድ የጁባዎችን አርቆ አሳቢነት፥ የጎረቤቶቻቸዉን ቅንነት፥ የአለም አቀፉን ሐቀኛ ድጋፍ ይጠይቃል።አዲስ መንግሥት ማለት ፕሮፌሰር ማርሻል እንደሚሉት አዲስ ድንበር፥ አዲስ ጎርብትና እና በጥንቃቄ ካልተያዘ አዲስ ችግርም ማለት ነዉ።

«የአዲስ መንግሥት መመሥረት ከቀድሞዉ ርዕሠ-ከተማዉ ጋር ካለዉ ችግር ሌላ ሌሎች ችግሮች ወይም ይፈጥራል።ችግር ወይም ዕድል።ደቡብ ሱዳን እንደ አዲስ መንግሥት ተመሠረተች ማለት ድንበር ትልቅ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነዉ።ይሕ ማለት ጦርነት ይኖራል ማለት አይደለም።ጥያቄ ግን ይኖራል። ከሰሜን ሱዳን ጋር ድንበር አካላይ ኮሚሽ ተመሥርቷል። ከዩጋንዳ ጋርም የቆየ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሥለነበረ ሌላ ኮሚሽ አለ።እርግጠኛ ነኝ ከኢትዮጵያ ጋርም እንዲሁ አንድ ሌላ ኮሚሽን ያስፈልጋል።ይሕ እንግዲሕ ቻይና ለነዳጅ ዘይት ሥትል ሱዳን ገብታለች።ደቡብ ሱዳን ነዳጅ ሐብት አላት በሚባልበት መሐል ያለ ነዉ።»

Südsudan Unabhängigkeitserklärung
ምስል ap

የአዲሲቱ ሐገር አጎራባችም የየራሳቸዉን ጥቅም ለማስከበር በጎሳ፥ በድንበር፥በምጣኔ ሐብት ግንኙነት ሰበብ አዲሱትን ሐገር ወደየራሳቸዉ ለመሳብ፥ አልሳብም ካለች ከተቃራኒዎችዋ ጎን ለመቆም መሞከራቸዉ አይቀርም።የደቡብ ሱዳን ተስፋ በርግጥ ትልቅ ነዉ።ከችግሮቿ ይልቃል ማለት ግን ያሳስታል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ