1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን፤ ጦርነት፤ ረሐብና ስደት

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ የካቲት 23 2009

«ዘግናኝ ግፎች ተፈፅመዋል።ሰዎች ተደፍረዋል።ልጆች ተሰቃይተዋል።የሰዎች ቤቶች፤ ሰብሎች፤ ከብቶች ወድሞባቸዋል።ወይም ተዘርፈዋል።ምግብ ተነፍገዋል።የሁሉም ምክንያት ዉጊያ ነዉ።ዉጊያ ባይኖር ረሐብ አይኖርም ነበር።»

https://p.dw.com/p/2YTsF
Süd-Sudan Mütter und Kinder beim UNICEF-Gesundheitszentrum in Nimini village
ምስል Reuters/S. Modola

Südsudan Flüchtlinge-UNHCR - MP3-Stereo

ዩኒቲ ስቴት በተባለችዉ የደቡብ ሱዳን ግዛት በረሐብ ለተጎዳዉ ሕዝብ ርዳታ ያከፋፍሉ የነበሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞች አካባቢዉን ለቀዉ ለመዉጣት መገደዳቸዉን ድርጅቱ አስታዉቋል።በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ እንደሚለዉ ማዬንዲት በተባለችዉ ወረዳ የነበሩ ሠራተኞቹ ለደሕንነታቸዉ አስጊ በመሆኑ አካባቢዉን ለቀዉ ወጥተዋል።የደቡብ ሱዳንን ጦርነት እና ረሐብ ሸሽቶ ወደ ጎረቤት ሐገራት የሚሰደደዉ ሕዝብ ቁጥርም እየጨመረ ነዉ።የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት እዚያዉ ደቡብ ሱዳን ከሚገኙት ይልቅ ወደ ጎረቤት ሐገራት ለተሰደዱት ርዳታ ማቅረብ ይቀላል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ባልደረባ ሊዮ ዶብስ እንደሚሉት የደቡብ ሱዳን ረሐብ-ሰዉ ሠራሽ ነዉ።የጦርነት ዉጤት።«በመሠረቱ ሰዉ ሰራሽ ረሐብ ነዉ።ሥለ ደቡብ ሱዳን ረሐብ ስናወራ የፖለቲካ ቀዉስ ዉጤት ነዉ።መፍትሔዉም፤ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ርዳታ ፖለቲካዊ መሆን አለበት።»
ረሐቡ፤ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ባለፉት ሰሰወስት ዓመታት ካየና ከሚያዉ መከራ አንዱ ምናልባትም ይፋ እዉቅና የተሰጠዉ ነዉ።ሌሎቹ ብዙ ናቸዉ።ሴቶች ተደፍረዋል።ሕፃናት ግፍ ተዉሎባቸዋል።የደካሞች ቤት ጋይቷል። ሐብት ንብረታቸዉ ተመዝብሯል።
                                         
«ዘግናኝ ግፎች ተፈፅመዋል።ሰዎች ተደፍረዋል።ልጆች ተሰቃይተዋል።የሰዎች ቤቶች፤ ሰብሎች፤ ከብቶች ወድሞባቸዋል።ወይም ተዘርፈዋል።ምግብ ተነፍገዋል።የሁሉም ምክንያት ዉጊያ ነዉ።ዉጊያ ባይኖር ረሐብ አይኖርም ነበር።»አንድ መቶ ሺሕ ተርቧል።ሁለት ሚሊዮን ተፈናቅሏል።ከ1,5 ሚሊዮን የሚበልጠዉ ተሰድዷል።እየተሰደደም ነዉ።«አሳሳቢ» ይሉታል ዶብስ።
                                      
«ሁኔታዉ በጣም አሳዛኝ ነዉ።እኛን በጣም እያሳሰበን ነዉ።እንዳልከዉ ድንበር አቋርጠዉ ጎረቤት ሐገራት የደረሱት ስደተኞች ቁጥር በቅርቡ ከ1,5 ሚሊዮን በልጧል።ከዚሕ በተጨማሪ ከ1,9 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እዚያዉ ሐገር ዉስጥ ተፈናቅሏል።ወደ ዉጪ መሰደዱም እንደቀጠለ ነዉ።»
UNHCR እንዳስታወቀዉ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ሰሜን ሱዳን የገባዉ ደቡብ ሱዳናዊ ከ31 ሺሕ በልጧል። ሱዳን ባጠቃላይ ከ328 ሺሕ፤ ኢትዮጵያ ከ3 መቶ ሺሕ በላይ፤ ዩጋንዳ ከ7 መቶ ሺሕ በላይ፤ ኬንያ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ያስተናግዳሉ።«ደጎች» ይሏቸዋል ዶብስ።
                              
«የነዚሕ ሐገራት መንግሥታት በጣም ደግ ናቸዉ።ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ተባባሪ ናቸዉ። ላሳዩት ትብብርና ርሕራሔ እናመሰግናቸዋለን።»
ፈተናዉ እዚያዉ ሐገር ዉስጥ ያሉትን መርዳቱ ነዉ።ዉጊያዉ ትልቁ እንቅፋት ነዉ።የተፋላሚ ኃይላት ታጣቂዎች ዛቻ፤ ቁጥጥርና አንዳዴ ዘረፋ ከባዱ መሰናክል።ዛሬ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት 28 ሰራተኞች ከማዬንዲት ለማዉጣት መገደዱን አስታወቀ።ምክንያት፤- ሠራተኞቹ ላይ አደጋ ሊጣል ይችላልና።ይንና መሠል እንቅፋቶች በመኖራቸዉ የርዳታ ድርጅቶች መርዳታ የሚገባቸዉን ሕዝብ እየረዱ አይደለም።
                              
«ርዳታ እሚፈልጉት ሰዎች ጋ መድረስ በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል።የሎጂስቲክስ ችግርም አለ።ባሁኑ ወቅት የምንረዳዉ ሕዝብ የኛን ርዳታ ከሚፈልገዉ አንድ አራተኛዉን ያሕል ነዉ።ይሕ ለኛ ትልቅ ችግር ነዉ።»የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር፤ የርዳታ ሠራተኞች በረሐብ በተመታዉ አካባቢ ያለገደብ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ከሳምንት በፊት አስታዉቀዉ ነበር።ዛሬ በሳምንቱ ዓለም አቀፉ ድርጅት ሰራተኞች ለማሸሽ ተገደደ።

Südsudan Kindersoldaten
ምስል picture alliance/AA/UNICEF/S. Rich
UN Blauhelme Süd Sudan Südsudan
ምስል Getty Images/A.G.Farran

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ