1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን 1ኛ ዓመት ነፃነት

ሰኞ፣ ሐምሌ 2 2004

ትንሺቱ ከተማ ለታላቁ በዓል እንድትመጥን ለማስጌጥ፣ ትላቁ አዳራሽ ለማስዋብ፣ በብዙ ሚሊዮን የተቆጠረ ዶላር ፈስሷል።ለአንድ ቀን ድግስ ሚሊዮናት ዶለር የተከሰከሰላት የጁባን የአዘቦት ፀጥታ ለማስከበር ግን እነ ሻምበል በእግራቸዉ መኳተን ግድ-አለባቸዉ።

https://p.dw.com/p/15ULC
A man waves the national flag of South Sudan during celebrations to mark the country's first anniversary of its independence in Juba, July 9, 2012. South Sudanese celebrating their nation's first birthday on Monday will bask in the pride of their hard-won political freedom, but many may ask when they will enjoy the material benefits promised by the government of former rebels. REUTERS/Adriane Ohanesian (SOUTH SUDAN - Tags: SOCIETY ANNIVERSARY POLITICS)
ጁባ-ፌስታምስል Reuters

ጁባ ካምናዉ በላይ ደምቃ፣ ካምናዉ የዛሬ ቀን እኩል ዛሬ ጨፈረች።የትንሺቱ ከተማ ትልቅ-ንፁሕ ዘመናይ አዳራሽ ካምናዉ በላይ አጊጦ ካምናዉ እኩል በመሪዎች፣ በሚንስትር ዲፕሎማቶች ተጨናንቆ፣ ካምናዉ በላይ የነፃነት ጥዑም ዜማ-ሲንቆረቆርበት፥ በጎ ቃል ተስፋ ሲሰበክበት ዋለ። የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ባንድ ዓመት አደገች።ጁባን ካምና በላይ አስዉቦ ካምና እኩል ያስፈጨረዉ፣ ትልቅ አዳራሿን ካምናዉ አኩል ሞልቶ፥ ካምናዉ በላይ ተስፋ ያስረጨዉ፣ ያመት እድገት ለአዲሲቱ ሐገር ሕዝብ የእድሜ ሒደት ብቻ ወይስ የሠላም፣ ብልፅግና ምልክት? ላፍታ እንጠይቅ።



የደቡብ ሱዳን ኢፐብሊክ ብሄራዊ መዝሙር።ላንድ ዓመት ባደባባይ ተዘመረ።ከጁባ-እስከ ሒጂሊጅ፥ ሠራዊት አሠለፈ።አስፎከረም።ከአዲስ አበባ እስከ ኒዮርክ፥ ከካይሮ እስከ ብራስልስ ዲፕሎማቶችን አስቆመ፥ ባንዲራ አሠቀለም።
«መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጠዉ በአምስት መቶ መያዶች ነዉ።ጦሩ ሙሉ በሙሉ አልተዋሐደም፥ ገና ብዙ ፈተና አለባቸዉ እንደመለት።»

አቶ ብሩክ መስፍን የአለም አቀፉ የፀጥታ ጥናንት ተቋም ተመራማሪ።የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳት ሳልቫኪር ግን ፈተናዎች አይበግሩንም አሉ።«የገጠመን ፈተና ይጥለናል? ወይስ እኛ እንደ ሐገር ቆመን መፃኤ እድላችንን እንበይናለን። እንደማምነዉ ይሕ ከአባት-አያቶቻችንና መስዋዕት ከሆኑ ወገኖቻችን አላማ ጋር በሚጣጣም ታሪክ ያሳርጋል።በጋራ ከሠራን የደቡብ ሱዳን ታሪክ መላዉን ዓለም ያነቃቃል።»


በቀድም።አርብ ነዉ።ለካርቱሞች ግን የፀሎት-ስግደት፣ የበዓል-ዕረፍት ዕለት አልነበረም።እንደ ቀዳሚዎቹ ሰወስት አርቦች ሁሉ ገሚስ ካርቱሞች የፕሬዝዳንት ዑመር ሐሰን አልበሽርን አገዛዝ ለማስወገድ ለአመፅ የታደሙበት፣ አልበሽር በአንፃሩ አመፀኞቹን ለማፈን የሚባትሉበት የዉጥረት ዕለት ነበር። የቀድሞዉ እዉቅ ጄኔራል የካርቱሙን አመፅ-ተቃዉሞ ለማክሸፍ ከመጣደፍ መባተላቸዉ እኩል የሥርዓታቸዉን ሕልቅት ምዕራብና ደቡብ ላይ ፈጥርቆ የያዘዉን ግጭት-ጦርነት ከመከታተል አልቦዘኑም።

ከአል ፈሽር-ዳርፉር ብዙም አዲስ ነገር የለም።ለዳርፉር ያ-አርብ እንዳለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ ሠላም ከጦርነት፣ ስግደት-ፀሎት፣ በዓል-እረፍት ከግጭት፣ ግድያ የሚፈራረቁበት ዕለት ነዉ።ለጁባ የሥራ ቀን ነዉ።ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ዛሬ በተከበረዉ የደቡብ ሱዳን አንደኛ ዓመት የነፃነት በአል ላይ የሰሜኑ አቻቸዉ እንዲገኙ የግብዣ ደብዳቤ የፃፉት፥አልበሽር መጋበዛቸዉን የሰሙትም የዚያን ቀን ነዉ።አርብ።


አል-በሽር በካርቱሙ ዉጥረት ጥድፊያ መሐል፣ እንደ ሰላማዊ ሰዉ እየተደራደሩ፣ እንደ ተግባቢ ጎረቤት እተስማሙ፣ እየተፈራረሟቸዉ፣ እንደ ክፉ አንጣ የሚያወግዟቸዉ ሰዉዬ፣ እንደ ደመኛ ጠላት እየወጉ እንደ ጥሩ ወዳጅ የመጋበዛቸዉን ሰበብ ምክንያት፣ የሚሰጡትን መልስ ይዘት፣ የግብዣ-መልሱን ዲፕሎማሲያዊ እንድምታ እያነሱ ሲጥሉ የካዱቅሊዉ መልዕክት አናጠባቸዉ።

ካዱቅሊ-ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች በሕዋላ የሰሜን ሱዳንን የደቡብ ድንበርነት የተረከበች፣ ደቡብ ሱዳን አንፃራዊ ሠላም ሲሰፍንባት ለሱዳኖች የጦርነት-ዛር መደለቂያነት የተፈረደባት የደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ ናት።አርብ።የግዛቲቱ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኢብራሒም ብሌንዲያሕ፣ የቀድሞዉ የሻኪያን ከተማ አስተዳዳሪ አሊ ማተርና ሌሎች ስድስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ።

ገዳዮች፣-ካርቱሞች በደቡብ ሱዳን የሚደገፈዉ የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N) ነዉ ይላሉ።ጁባዎች ደግሞ የለንበትም።ፌስታ ግድያ፣ ግብዣና መርዶ።ሱዳኖች።የተቃርኖ-ሁነት ድምቀት አብነቶች።ካዱቅሊ ስታለቅስ፣ ካርቱም ስታነባ፣ ጁባ ፈነደቀች።ዛሬ።


የአዲሲቱ ሐገር አዲስ ርዕሠ ከተማ ለዛሬዉ በዓል ተጠርጋ-ተወልዉሏ ተዉባለች።በልዩ ትዕዛዝ ከዉጪ በተገዙ ልዩ አምፑሎች ደምቃለች።በእዉቅ በተሰፉ ባንዲራና አርማዎች፣ በጥንቃቄ በተፃፉ-ቅስት መፈክሮች ተንቆጥቁጣለች። የነፃነት ትልቅ አርበኛዋ የኮሎኔል ዶክተር ጆን ጋራግ አስከሬን ያረፈበት ዉብ ግዙፍ አዳራሽ በደሳሳ ጎጆ ቤቶች ለተሞላችዉ ትንሽ አቧራማ ከተማ በርግጥ ገዝፎባታል።

ግን የዉጪ ሐገር መሪዎችን፣ ሚንስር-ዲፕሎማቶች ከማስተናገድ ሌላ የክብር ሽልማት ተሽላሚ ሸላሚዎች፣ የቁንጅና ዉድድር ተፎካካሪ ቆነጃጂቶች፣ ታጭቀዉበታል።እና አዳራሹ ለጁባ ደሳሳ ጎጆዎች ይግዘፍ እንጂ ለሚስተናገዱበት ክቡራትና ክቡራን ክብር፣ ለነፃነት በዓሉ ታላቅ ድል ሲባል ግዙፍ አርማ ተተክሎለት እንደገና ገዝፏል።

ትንሺቱ ከተማ ለታላቁ በዓል እንድትመጥን ለማስጌጥ፣ ትላቁ አዳራሽ ለታላላቆቹ ሹማምንት እንዲመች ለማስዋብ፣ ትልቁን ድግስ፥ ለማሳመር በብዙ ሚሊዮን የተቆጠረ ዶላር ፈስሷል።ሻምበል ዩአንግ ማኬቴ ዩአንግ ሙኒኪ የተሰኘዉ የጁባ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ እንደመሆናቸዉ መጠን ታላቁ ድግስ እንዳይታጎል ነቅቶ ከሚጠብቀዉ የፖሊስ ሠራዊት አንዱን ብርጌድ ማዘዛቸዉን መገመት አያዳግትም።

ለአንድ ቀን ድግስ ሚሊዮናት ዶለር የተከሰከሰላት የጁባን የአዘቦት ፀጥታ ለማስከበር ግን እነ ሻምበል በእግራቸዉ መኳተን ግድ-አለባቸዉ።«እስረኞቻችንን ወደ ዋናዉ ወሕኒ ቤት ለማጓጓዝ መኪና ያስፈልገኛል።ለባለ መኪናዉ የምከፍለዉ ገንዘብ ካገኘሁ መኪና ተኮናትሬ እስረኞቹን ወሕኒ ቤት አደርሳቸዋለሁ።»

የቀድሞዋ ሱዳን ማዕከላዊ መንግሥትና የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድን የሱዳን ነፃ አዉጪ ጦር ወይም ንቅናቄ (SPLA/M) በሁለት ሺሕ አምስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የሠላም ዉል ከተፈራረሙ ወዲሕ ደቡብ ሱዳን ለስድስት ዓመት ነፃ አከል-ራስ ገዝ መስተዳድር ነበረች።

ዉሉ ከተፈረመ በሕዋላ በነበረዉ ስድስት አመት የራስ-ገዝ አስተዳዳሪ የነበረዉ የቀድሞዉ አማፂ ቡድን SPLA/M ባለፈዉ አመት የመግሥትነቱን ሥልጣን እስከተረከበበት ጊዜ ድረስ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ብቻ አስር ቢሊዮን ዶላር ወስዷል።

ዓለም አቀፉ የሠብአዊ መብት ተሟጓች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ ከሁለት ሺሕ ሰባት እስከ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ በነበረዉ ሁለት ዓመት ደቡብ ሱዳን በኬንያ በኩል ከዩክሬንና ከቻይና ብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ታንኮች፥ ሌሎች የነብስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎች፥ ቦምቦችና ጥይቶች ገዝታለች።

ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ተጥሶ ገና ሐገር ወዳልነበረችዉ ግዛት ለጎረፈዉ ጦር መሳሪያ የተከፈለዉ ገንዘብ ከአስር ቢሊዩኑ ዶላር የነዳጅ ገቢ ተቆንጥሮ መሆኑን ለማወቅ አስተንታኝ አያሻም።ርዕሥ-ከተማ ጁባን ጨምሮ የድፍን ደቡብ ሱዳን ሕዝብ ግን መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት አቶ ብሩክ እንዳሉት የመያዶችን እርጥባን መጠበቅ አለበት።

ሐገርን ነፃ ማዉጣት በርግጥ ከባድ ነዉ።ነፃ ሐገርን ተገቢ ሐገር ማድረግ ደግሞ ነፃ ከማዉጣት በላይ ከባድ ነዉ።በአንድ ዓመት ጊዜ ብዙ እንዲሰራ የሚጠብቅ በርግጥ የለም።ጅምሩ ካልታየ ግን ተስፋዉም አይኖርም።በተለይ አቶ ብሩክ እንደሚሉት ለረዥም ጊዜ የማሰብ ራዕይ ከጎደለ።


ሻምበል ዩአንግና ባልደረቦቻቸዉ ከደረሱበት ለመድረስ ከሠላሳ አመታት በላይ መዋጋት፥ ብዙ ጓዶቻቸዉን መሰዋት ነበረባቸዉ። ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ሕይወቱን፥ ከሰወስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ቤት፣ ሐብት ንብረቱን ጥሎ መፈናቀል ወይም መሰደድ ነበረበት።

አሁን የሐገርን ፀጥታና ደሕንነት ማስከበር ደግሞ ሻምበል ዩአንግ እንደሚሉት ለነፃነት ከመፋለም በላይ ከባድ፥ አስፈላጊም ነዉ።

«ለረጅም ጊዜ የተዋጋነዉ የሱዳንን ሥርዓት ለማስተካከል ነዉ።አሁን ደግሞ ፖሊስነት ለኔ ጥሩ ነዉ።በጣም አስፈላጊ ነዉ።ምክንያቱም የዜጎችንና የሐገሪቱን ደሕንነትና ፀጥታ የማስከበር ሥራ ሥለሆነ።»

ደቡብ ሱዳን ዓመት የተጓዘችዉ ግን በሻምበል ዩአንግና በብጤዎቻቸዉ እምነት፥ ምኞትና ፍላጎት ተቃሮኖ ነዉ።ነፃነትዋ ባከበረች በወሩ ነሐሴ ላይ ኑዌር እና በሙርል ጎሳ ታጣቂዎች መካካል በተፈጠረዉ ግጭት ከስድስት መቶ በላይ ሰዎች ተገደሉ።የጎሳ ግጭት፥ ዘረፋ መበቃቀሉ ቀጥሎ ጥር ላይ ብቻ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎች ተገደሉ።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቀሉ።

ከSPLA/M ያፈነገጡ የቀድሞ ተዋጊዎች፥ አዳዲስ የተመሠረቱ ተቃዋሚ ሐይላት የአዲሲቱን ሐገር መንደሮች ባዳዲስ ዉጊያዎች እያዋካቡዋቸዉ ነዉ።ደቡብ ሱዳን ከሜን ሱዳን ጋር ሒጂሊጅ በቀጥታ፥ ኮርዶፋን፥ ብሉ ናይልና ዳርፉር በተዘዋዋሪ የገጠመችዉ ጦርነትና ዉዝግብ ብዙ ሺዎችን እየፈጀ፥ መቶ ሺዎችን እያሰደደ ነዉ።

የአመታቱ ጦርነት ቁስሏ ሳሽር በቀጥታም በተዘዋዋሪም የተዘፈቀችበት ቅሪት ዉዝግብ-አዳዲስ ግጭት ዉጊያ ሕዝቧ በሠለም-ነፃነት የመንቀሳቀስ፥ የመበልፀጉን ተስፋ ቢያንስ እስካሁን ብሔራዊ መዝሙሩ ላይ ብቻ አስቀርቶበታል።

ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ዘይት፥በብረት፥ በመዳብ፥ በብር፥በወርቅና በሌሎች ዉድ ማዕድናት የበለፀገች ነች።አብዛኛ ሕዝቧ ግን ከድሕነት ጠገገ በታች ነዉ-የሚኖረዉ።በወሊድ በሚሞቱ እናቶች ፥ በክትባት እጦት በሚቀጩ ሕፃናት ቁጥር ከዓለም የመጀመሪያዉን ደረጃ ይዛለች።ወይዘሮ ኮሌታ አኩስታሮ እና ብጤዎቻቸዉ የሐገራቸዉን አስከፊ ገፅታ በተለይም የሴቶችን ችግር ለመለወጥ ደፋ ቀና ማለታቸዉ አልቀረም።

«ሰወስት አራተኛ ያሕሉ ሴቶች ማይምን ናቸዉ።እነሱ እራሳቸዉን እንዲችሉ መሠረተ-ትምሕርት ማስተማር አለብን።»

አምና ከዜሮ ለጀመረችዉ ሐገር ለመሠረተ-ትምሕርት፥ ለመሠረተ-ልማት፥ ለመሠረታዊ-ፍጆታ፥ ለመሠረታዊ የመንግሥት ሥራ ገንዘብ ያሻታል።ገንዘቡን በቀን ወደ አራት መቶ ሺሕ በርሚል ከሚዛቅበት የነዳጅ ዘይት ማግኘቱ በርግጥ አልገደደም ነበር።ገንዘቡን በተገቢዉ ጊዜ የማግኘት፥ ለተገቢዉ ጉዳይ የማዋሉን ብልጠት-ብልሐት ሠላሳ አመት የተዋጉላት መሪዎቿ ማጣታቸዉ እንጂ ድቀቱ።

ዘጠና ስምንት በመቶዉ የደቡብ ሱዳን ገቢ ከነዳጅ የሚገኝ ነዉ።የጁባ መሪዎች ባለፈዉ ጥር የሐገሪቱን የነዳጅ ጉርጓዶች ሲዘጉ፥የካርቱም ጠላቶቻቸዉን ለመበቀል አልመዉ ነበር።እርምጃዉ ካርቱሞችን መጉዳቱ አልቀረም።የወለፊንድ ባርቆ አዲሲን ሐገር የጎዳዉ ይብሳል። በትንሽ ግምት በወር ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር አሳጣት።ጨቅላ ምጣኔ ሐብቷን አሸመደመደዉ።ተቀማጭ የዉጪ ምንዛሪዋን ባዶ አስቀረዉ።የገንዘቧን (የፓዉንድ) ዋጋ አዘቅት ወረወረዉ።አቶ ብሩክ፥-


የሁለቱ ሱዳኖች ተወካዮች ባለፈዉ አርብ አዲስ አበባ ላይ የደረሱበት ስምምነት በርግጥ ሥለ ድርድር ከመስማማት ባለፍ ሁነኛ ትርጉም የለዉም።ዛሬ ጁባ ላይ ለተከበረዉ በዓል ልዩ ድምቀት መስጠቱ ግን አልቀም።ስምምነቱ አል-በሽር የኪርን ግብዣ ተቀብለዉ እንዳምናዉ ጁባ የሚወስዳቸዉ አይነት ግን አልሆነም።አልሔዱም።ሁለቱን ሱዳኖች የሚሸመግለዉ ቡድን መሪ የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳት ታቦ ኢምቤኪ እንዳሉት ደግሞ ስምምነቱ ለወደፊቱ ድርድር መሠረት የሚጥል ነዉ።ተስፋ-ቀቢፀ ተስፋ ለማይለየዉ ምድር ደግሞ ሌላ ተስፋ-ወይም ቀቢፀ-ተስፋ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Schlagworte: Unabhängigkeitsreferendum Südsudan Wer hat das Bild gemacht/Fotograf?: Simone Schlindwein Wann wurde das Bild gemacht?: 9.1.2011 Wo wurde das Bild aufgenommen?: Juba Südsudan Bildbeschreibung: Bei welcher Gelegenheit / in welcher Situation wurde das Bild aufgenommen? Wer oder was ist auf dem Bild zu sehen? erster Wahltag Referendum Wahlstation
የድሕነቱ ቅንጣት ገፅታምስል Simone Schlindwein
South Sudan's President Salva Kiir attends celebrations to mark the first anniversary of the country's independence at the John Garang memorial mausoleum in Juba, July 9, 2012. South Sudanese celebrating their nation's first birthday on Monday will bask in the pride of their hard-won political freedom, but many may ask when they will enjoy the material benefits promised by the government of former rebels. REUTERS/Adriane Ohanesian (SOUTH SUDAN - Tags: SOCIETY ANNIVERSARY POLITICS)
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ




ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ