1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃና የእሕጉሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት

ሐሙስ፣ ግንቦት 4 1997
https://p.dw.com/p/E0ej

በዓለም ላይ በልማት እጦትና፤ የኤኮኖሚ ችግር ብርቱ ስቃይ የሚደርስበትን በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘውን የአፍሪቃ ሕዝብ ያህል የትም ተፈልጎ አይገኝም። የዕለት ኑሮውን ከአንዲት ዶላር ባነሰች ገቢ ከሚገፋው ከሚሊያርድ የሚበልጥ የዓለም ሕዝብ አብዛኛው የሚኖረውም በዚያው አካባቢ ነው። ድህነት፣ በሽታ፣ የፍትሃዊ አስተዳደርና የመብት እጦት፤ እንዲሁም ኋላ ቀርነት የወደፊት ዕድሉን አንቀው፤ መንገዱን አጨልመውት ነው የሚገኙት።

የአፍሪቃ ሕዝብ ዛሬ በየቦታው በሙስና ወግ በተዘፈቁና ለበጎ የአስተዳደር ዘይቤ ባዕድ በሆኑ ገዢዎች ከመረገጡ ባሻገር አቅሙ የማይችለውና ትውልድ ከፍሎ የማይወጣው የውጭ ዕዳ ተሸካሚም ሆኖ ነው የሚገኘው። የዕዳ ምሕረት ወዲህ የዕዳ ምሕረት ወዲያ ብዙ ይባል ይዘከር እንጂ በተጨባጭ እስካሁን ያገኘው አንድም ጥቅም የለም። ሁኔታው የልማት ተሥፋውን ያን ያህል የሚያዳብር ሆኖ አይገኝም።

ከፋም ለማም ጭብጥ በሆነ የዕድገት አቅጣጫ ስታመራ የምትታየው ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ናት። ለመሆኑ የዚህች አገር ዕርም’ጃ አርአያነቱ እስከምን ነው? ዕድገቱ በአሕጉሪቱ ልማት ላይ ያለውና የሚኖረውስ ተጽዕኖ? ይህን ጉዳይ ለመከታተልና ለመመርመር በየጊዜው የሞከሩ የምጣኔ-ሃብት ጠበብት እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተቋማት አልታጡም። ከነዚሁ መካከልም አንዱ በአሕጽሮት IMF በመባል የሚጠራው ዓለምአቀፍ የተባበሩት መንግሥታት የገንዘብ ተቋም ነው።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በቅርቡ ያወጣው አንድ መረጃ የፕሬቶሪያ ልማት በተቀሩት የአፍሪቃ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ክብደት የሚሰጠው ተጽዕኖ እንዳለው አመልክቷል። እርግጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ እንደተለመደው ዓቢይ የዕድገት መንኮራኩር የሆነው የንግድ ግንኙነት በክፍለ-ዓለሚቱ ያለው ሚና ያነሰ በመሆኑ የጥናቱ ውጤት ከተጨባጭነት ይልቅ በግምት ላይ ነው የሚያመዝነው።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ያካሄደው ጥናት ጉዳዩን ደቡብ አፍሪቃ ከዓለም ሕብረተሰብ የተገለለች የአፓርታይድ ግዛት እስከነበረችበት ጊዜ እስከ 60ኛዎቹ ዓመታት መለስ ብሎ ይዳስሳል። የደረሰበት ድምዳሜም ያለፉት አራት አሠርተ-ዓመታት የፕሬቶሪያ የልማት ዕርምጃ ለ 47 የአፍሪቃ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ ድርሻ ነበረው የሚል ነው።

ከ 1960 እስከ 1999 ዓ.ም. በተጠናቀሩ ዳታዎች ተመሥርቶ የቀረበው የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው የደቡብ አፍሪቃ 1 በመቶ የኤኮኖሚ ዕርምጃ በተቀሩት የክፍለ-ዓለሚቱ አገሮች እስከ 0.7 በመቶ ለሚደርስ ዕድገት ድርሻ ነበረው። በተፋጠነ የዕድገት አቅጣጫ እያመራች የምትገኘው ደቡብ አፍሪቃ ከጎረቤቶቿ ጋር ይበልጥ እየተሳሰረች በመሄድ ላይ በመሆኗ ወደፊት የክፍለ-ዓለሚቱ የንግድ ልውውጥ እንዲያውም ይበልጥ መጨመሩ አይቀርም ነው የተባለው።

ሆኖም የምንዛሪው ተቋም ጥናት በኤኮኖሚው ዕድገት ግንኙነት ላይ ከማተኮር አላለፈም። ከንግድ እስከ ካፒታል ያሉትን ሌሎች ምክንያቶች ለወደፊት ምርምር ትቷቸዋል። በደቡብ አፍሪቃ የተቋሙ ወኪል ቪቫክ አሮራ እንደሚሉት የጥናቱ መሠረታዊ ዓላማም የፕሬቶሪያ ዕድገት በክፍለ-ዓለሚቱ ልማት ላይ ያለውን ተጽዕኖ መመርመር እንጂ እንዴትና ሰምን ለሚሉ ዝርዝር ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት መሞከር አልነበረም።

በሌላ አነጋገር የአካባቢው የንግድ ልውውጥ በመጠኑ ገና ዝቅተኛ በመሆኑ ወሣኝ ጉዳይ ሆኖ አልተገኘም፤ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም። መረጃዎችን ለመጠቃቀስ ያህል እርግጥ ከ 1994 እስከ 2002 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪቃ በክፍለ-ዓለሚቱ የነበራት የውጭ ንግድ ድርሻ ከዚያ ቀደም ካሉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት ሲነጻጸር በአማካይ በሶሥት ዕጅ ዕድገት አሣይቷል። ግን ይህ ከጠቅላላው የእሪቃ ንግድ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑ ነው።

በሌላ በኩል በተመሳሳይ ጊዜ የተቀረው አፍሪቃ ከፕሬቶሪያ ጋር ያካሄደው የንግድ ልውውጥ በአራት ዕጅ ከፍ ብሏል። ግን ይህም ከጠቅላላው የክፍለ-ዓለሚቱ ዓመታዊ ብሄራዊ ምርት መጠን ሲነጻጸር በአማካይ በ 1.5 በመቶ ዕድገት የተወሰነ መሆኑ ነው። የደቡብ አፍሪቃ የውጭ ንግድ ገቢ ዳታ እንደሚያመለክተው አገሪቱ ባለፈው 2004 ዓ.ም. ከተቀሩት የክፍለ-ዓለሚቱ መንግሥታት ጋር ያካሄደችው ንግድ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር ያለፈ አልነበረም።
እንግዲህ ድርሻው ደቡብ አፍሪቃ በዓለምአቀፍ ደረጃ ካካሄደችው ንግድ 7.5 በመቶ ገደማ ቢጠጋ ነው። ለማነጻጸር ያህል በአሜሪካና በደቡብ አፍሪቃ መካከል በዚሁ ጊዜ የተካሄደው የንግድ ልውውጥ በዋሺንግተን መንግሥት መረጃ መሠረት ከ 44 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል። ውስጣዊው የአፍሪቃ ንግድ በሚገባ ለመስፋፋት ገና ብዙ ይቀረዋል ማለት ነው።

ሁኔታውን ለመለወጥ ከምንዛሪው ተቋም በኩል የተሰጠው አስተያየት የመዋዕለ ነዋይንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ቁልፍ ጉዳይ ያደርጋል። ይህም ደቡብ አፍሪቃ ከአፓርታይድ ተላቃ በዴሞክራሲ አቅጣጫ ማምራት ከጀመረች ወዲህና እንደገና ከአፍሪቃ በሰፊው ከተቀራረበች ወዲህ ባሉት ዓመታት ቀስ በቀስ ሥር መስደድ መያዙን ነው ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የሚናገረው።

እርግጥ የዚሁ ጊዜ ጥናት ተጠናቆ ባይቀርብም ከደቡብ አፍሪቃ ወደ ሰሜን የሚንቀሳቀሰው የጆሃንስበርግ ባንኮች፣ ነጋዴዎችና የማዕድን ኩባንያዎች ገንዘብ ባለፉት ዓመታት በጣሙን ከፍ ብሏል። ይሄው የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ባለፈው ዓመት ብቻ በእጥፍ መጨመሩ ነው የሚገመተው። የመስኩ አዋቂዎች እንደሚናገሩት የደቡብ አፍሪቃ ኩባንያዎች ከ 1994 እስከ 2003 ዓ.ም. በደቡባዊው አፍሪቃ የኤኮኖሚ ሕብረት አገሮች በያመቱ በሥራ ላይ ያዋሉት ካፒታል ብቻ በአማካይ 435 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋል።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የደቡብ አፍሪቃ ቀጥተኛ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት የአንዳንድ የአፍሪቃ አገሮችን የካፒታል እንቅስቃሴ እንደሚያዳብርና የፕሬቶሪያ ዕድገትም ባለው የገንዘብ ትስስር የተነሣ በዚያው ሊንጸባረቅ እንደሚችልም አመልክቷል። ደቡብ አፍሪቃ በአሕጉሪቱ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ጥረት ላይ ባላት ቀደምት ሚናም በውስጧ የምታደርገው የልማት ዕርምጃ በሌሎቹ አገሮች የነጋዴውንና የተጠቃሚውን በራስ መተማመን የሚያዳብር እንደሚሆን ነው በጥናቱ የተጠቀሰው።

ደቡብ አፍሪቃ ዛሬ የክፍለ-ዓለሙ የልማት ቁንጮ ናት። በ IMF መረጃ መሠረት የ 2003 ዓ.ም. አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ ከአፍሪቃ የመግዛት አቅም ከሲሶውና 38 በመቶ ከሚሆነው የገበያ ልውውጥ መጠን የተስተካከለ ነበር። እርግጥ የስድሣኛና ሰባኛዎቹን ዓመታት ሁኔታ አገሪቱ በአፓርታይድ ሳቢያ የተገለለች ስለነበረች ጭብጥ በሆነ መልክ ለመናገር ያዳግታል። ሆኖም የምንዛሪው ተቋም ወኪል ቪቫክ አሮራ እንደሚሉት የያኔዋም ፕሬቶሪያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የቀረበ የኤኮኖሚ ትስስር ስለነበራት ይሄው በተቀረው አፍሪቃ ዕድገት ላይ ጥቂትም ቢሆን ተጽዕኖ ወይም ድርሻ ሣይኖረው አልቀረም።

የደቡብ አፍሪቃ ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት 3.7 በመቶ በሆነ መጠን ዕድገት አሣይቷል። ይህም ከ 2000 ዓ.ም. ወዲህ የተፋጠነው መሆኑ ነው። በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት ደግሞ የ 4 በመቶ ዕድገት ይጠበቃል። በዕድገቱ የተቀረው የአፍሪቃ ክፍል ተጠቃሚ መሆኑ እንደማይቀር ቢገመትም ይህ ሊሆን መቻል አለመቻሉን ጠብቆ መታዘቡ ይመረጣል።

ደቡብ አፍሪቃ በክፍለ-ዓለሚቱ የዕድገት ቁንጮ መሆኗ ለልማት አስፈላጊ የሆኑት መዋቅራት፤ መሠረታዊው ቅድመ-ሁኔታዎች ከሞላ-ጎደል የተሟሉ መሆናቸው ነው። ከአፓርታይዱ አገዛዝ በኋላ ምንክ እንኳ የብዙሃኑ ጥቁሮች የኑሮ ሁኔታ ገና የሚገባውን ያህል ባያድግም አገሪቱ ዴሞክራሲን ቢቀር ለማሽተት በቅታለች። ኢንዱስትሪውና መገናኛ መዋቅሩ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ሲነጻጸር የተራመደ መሆኑም ለዕድገቱ አንዱ ዋስትና ነው።

ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙት በአብዛኞቹ የእፍሪቃ አገሮች ያለው ሃቅ ግን ከዚህ ሲበዛ የተለየ ነው። በተወሰነች ደረጃ እንኳ ፍትሃዊ አስተዳደር ፈልጎ ማግኘቱ ያዳግታል። የሠለጠነ የሥራ ጉልበት፣ አገርን በሰፊው የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች ለዕድገት ሞሶሶ የሆነው የትምሕርት አገልግሎት ሌላም ብዙ ብዙ ነገር በመጠኑ ሲበዛ ዝቅተኛ ነው። የንግዱና የኢንዱስትሪው መስፋፋትም እንዲሁ!

ከዚህ አንጻር የደቡብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገትና የንግድ ዕርምጃ ለነዚህ አገሮች ዕድገት ሞተር ሊሆን መቻሉ የሚያጠያይቅ ነው። የብዙዎቹን የአፍሪቃ አገሮች ዕድገት አንቀው የያዙት ውስብስብ ችግሮች ቀዳሚ መፍትሄን ይጠይቃሉ። የንግድ ግንኙነቱም ሆነ ትስስሩ የሁለት ወገን ጠቀሜታ ወይም ዕድገት አንቀሳቃሽ ሊሆን የሚችለው ልውውጡ በሁለቱም የአቅም ብቁነት ላይ ሲመሰረት ብቻ ነው።

አፍሪቃ በውስጣዊ አሕጉራዊ ትብብር ችግሮቿን ልትወጣ ቀርቶ ልታለዝብ ብትችል እንኳ ምንኛ ግሩም በሆነ ነበር። ግን ሃቁ ይህን አይመስልም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚሌኒየም ዕቅዱ የአሕጉሪቱን ድህነት በግማሽ ለመቀነስ ተነስቷል። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትም የድሃ ድሃ ለሆኑት አገሮች የዕዳ ምሕረት ለማድረግ በየጊዜው ቃል ይገባሉ። አፍሪቃውያን መንግሥታትም በአዲስ የልማት ሽርክና ፖሊሲ በዕድገትና በበጎ አስተዳደር አቅጣጫ ለማምራት ቆርጠው መነሣታቸው በተደጋጋሚ የተሰማ ጉዳይ ነው። ግን ቃል ተግባር ሲሆን አለመታየቱ ላይ ነው ችግሩ!