1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ ማንዴላን አከበረች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 11 2005

ደቡብ አፍሪቃዉያን ዛሬ የነጭ ዘረኛ አገዛዝ ታጋዩን የኔልሰን ማንዴላን 95ኛ የልደት በዓል በታላቅ ድምቀት አክብረዉ ዉለዋል። የነፃነት ታጋዩ አዛዉንት ግን ከአንድ ወር በላይ በሃኪም ቤት አልጋ ላይ ይገኛሉ። በጤናቸዉ ረገድ መሻሻሎች መኖራቸዉን ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማም ሆኑ ልጆቻቸዉ እየገለጹ ነዉ።

https://p.dw.com/p/19ARg
ምስል Reuters

 መላ ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ እሳቸዉ በነፃነት ትግል ያሳለፏቸዉን 67ዓመታት በ67 ደቂቃዎች የግብረ ሠናይ ተግባራት ዘክረዋል።
ከደርባን 30ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘዉ የዋቴርሎ አጎራባች መንደር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በዝማሬ አወድሰዋቸዋል። የመጀመሪያዉ የደቡብ አፍሪቃ ጥቁር መሪ፤ የነጭ ዘረኛ አገዛዝ ተፋላሚና የይቅርታ መንፈስ ያልተለያቸዉ ኔልሰን ማንዴላ ዛሬ 95 ዓመት ሞላቸዉ። እንኳን ሰሞኑን ለረዥም ቀናት ከዛሬ ነገ አበቃ እየተባለ ሃኪም ቤት ገብተዉ ቀርቶ ቀደም ሲልም በያዝነዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሃኪሞች ርዳታ በሻቱበት ጊዜ ከዚህች ቀን ይደርሳሉ ብሎ የገመተ አልነበረም። ቅጠል ያለ ቀኗ አትበጠስምና በህመም አልጋቸዉ ላይ ሆነዉም ሆኑን ግን የዛሬዋ ቀን ላይ ደረሱ፤ ከልቡ የሚወዳቸዉና የሚያከብራዉ ህዝባቸዉም ለዚህች ቀን የየራሱን ዝግጅት አሰናድቶ እሳቸዉ በየቦታዉ እየተገኙ በስማቸዉ የተደረገዉን እያዩ ባይመርቁም በመንፈስ እያሰባቸዉ ዉዴታ ፍቅሩን በየመልኩ ሲገልጸዉ ዋለ። የስዕል አዉደ ርዕዩ፤ የማራቶን ዉድድሩና ሌላዉም የስፖርት እንቅስቃሴ፤ ከምንም በላይ ደግሞ ለ67ዓመቱ የነፃነት ትግልና አስተዋጽኦዋቸዉ መዘከሪያ የ67 ደቂቃዉ ግብረ ሰናይ አገልግሎት በስማቸዉ ተደገሰ፤ ተከናወነ። የማንዴላ የትግልና የመንፈስ አጋሮች ብቻ ሳይሆኑም የነጩ ዘረኛ አገዛዝ የመጨረሻዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ፍሬዴሪክ ዊልያም ደክለርክ በበኩላቸዉ የዛሬዋ ቀን በግርግር ሳይሆን በጸጥታና በአክብሮት መከበር ይኖርባታል ሲሉ አሳስበዋል።  

Südafrika Nelson Mandela
ምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images


ተማሪዎቹ ለማንዴላ ክብር ከዘመሩበት ትምህርት ቤት 35 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የሚገኙት የሞርኒንግ ሳይድ መንደር ኗሪዎች ለነፃነት ተምሳሌቱ ድንቅ ሰዉ ፍቅር መታሰቢያ በመናፈሻ ዉስጥ በሚገኝ የብረት አጥር ላይ የሳጥን ቁልፍ የማንጠልጠል ዘመቻ ጀምረዋል። የዘመቻዉ አስተባባሪ ወጣቶች በአዎንታዊ አስተሳሰብ እንታነፁ የሚያነቃቃ Dreambuilders የተሰኘዉ ድርጅት ኃላፊ ፓትሪክ ኮቴዜ ነዉ፤
«ለእኔ አሁን ያለንበት ወቅት ኔልሰን ማንዴላን እንደሰዉና ዓላማቸዉን፤  በትክክል የምናዉቅበት ወሳኝ ጊዜ ነዉ። አሁን ደግሞ በገሃድ የኔልሰን ማንዴላ ወቅት ነዉ፤ እናም በዚህ ጊዜ እሳቸዉ ለዘመናት የቆሙለትን አክብረን እኛም ለቀጣይ ዓመታት እንደምንቆምለት ማስተዋል ይኖርብናል፤ እናም ይህ እነዚህን ቁልፎች እየቆለፉ ለማስታወሻ ማስቀመጡ የኚህን የታላቅ ሰዉ ተግባር በደቡብ አፍሪቃ እና በመላዉ ዓለም ህያዉ ሆነዉ እንዲኖሩ የማድረጊያ ሃሳብ ነዉ።»
በርካታ ሰዎች ናቸዉ በየዕለቱ ያንን የመናፈሻ ስፍራ በመጎብኘት ለኔልሰን ማንዴላ መልዕክቶችን የሚያሰፍሩባቸዉን ቁልፎች በአጥሩ ላይ ቆልፈዉ የሚሄዱት። አንዳንዶቹም ለማስታወሻ የተደረገዉ ይህ ቁልፍ ነገ ከሚረግፈዉ አበባ ይሻላል ባዮች ናቸዉ፤
«ለክብራቸዉ መገለጫ ከሚቀመጡ አበቦች ይልቅ ይህን ቁልፍ ቆልፎ የማስቀመጡን ሃሳብ በጣም አድንኤዋለሁ፤ እንደዉም ይበልጥ ግላዊነት ያለዉ ስሜት ፈጥሮልኛል። ቁልፉ ላይ ሰዎች ለማስተላለፍ የፈለጉትን የራሳቸዉን መልዕክት አስፍረዉበት ለወጣቶችና ለመላ ደቡብ አፍሪቃ እሳቸዉ ለሠሩት መልካም ተግባር ምስጋናቸዉን ይገልጹበታል። በጣም ድንቅ ሃሳብ ነዉ ብዬ አስባለሁ።»
«ዓለም ዓቀፍ ጀግና ከመሆናቸዉ በተጓዳኝ ለመላ አገራችን ደግሞ እንደ አባት ናቸዉ፤ በርካታ ነገሮች እንዲለወጡ ረድተዋል፤ በ1990ዓ,ም እንደተወለደ ወጣት አብዮት በተካሄደባት አገር እንድናድግ ለእና ምክንያት ሆነዉናል። እጅግ ብዙ ረድተዉናል።»

Mandela Krankenhaus Genesungswünsche 06.07.2013
ምስል Reuters


«ለዚህች አገር መልካም ነገሮች እንዲከናወኑ ጥረዋል፤ ዛሬ የሚታየዉ አገር አባት ናቸዉ፤ የእርቀሰላም ተምሳሌት ናቸዉ፤ እናም በአክብሮት ሊታዩ የሚገባ የአገር አባት ናቸዉ።»
ምንም እንኳን ሃኪም ቤት ቢተኙም ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ሳትሆን መላዉ ዓለም ዛሬ አስቧቸዋል። የተመድ የዛሬ አራት ዓመት ነዉ ይህ የልደታቸዉ ዕለት የኔልሰን ማንዴላ ቀን እንዲሆን የወሰነዉ። በዛሬ ዕለትም በድርጅቱ ጽ/ቤት ልደታቸዉ ሲከበር ዋና ጸሐፊ ባን ጊ ሙን የማንዴላን የፖለቲካ ተግባርና የእርቀሰላም ጥረት አወድሰዋል። በስርዓቱ ላይም የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተንን ጨምሮ የማንዴላ የእስር አጋር አንድሪዉ ሜሊንጋኒ የማኅበራዊ መብት ተጋቾችና የሙዚቃ ሰዎች ተገኝተዋል። እሳቸዉ ቢያዩትም ባያያትም ህዝባቸዉ በአንድ መንፈስ ያከናወኑትን መልካም ተጋድሎ እያሰበ ልደታቸዉን በየራሱ ስልት አክብሮላቸዋል። ከፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ ጽህፈት ቤት የወጣ መግለጫ ይዞታቸዉ እየተሻሻለ መሆኑን አመልክቷል። ከእሳቸዉ በኋላ አገራቸዉ በጀመረችዉ ጎዳና አትዘልቅም የሚል ስጋት ከየአቅጣጫዉ ቢሰነዘርም የቀድሞ ባለቤታቸዉና የትግል አጋራቸዉ ዊኒ ማንዴላ እነዚህ የምጽዓት ነቢዮች ያሉትን ቢሉም አገራችን በኅብረት ተጠናክራ ወደፊት መራመዷን ትቀጥላለች ሲሉ ነገም ተተኪ መኖሩን አመላክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ