1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ እና የኤ ኤን ሲ ድል

ዓርብ፣ ሚያዝያ 8 1996

በመላ አፍሪቃ ከፍተኛ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ትርጓሜ በያዘችው ሀገር፡ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የአፍሪቃውያኑ ብሔረተኞች ኮንግረስ፡ ኤ ኤን ሲ ጉልሁን ድል አገኘ። የዘር አድልዎ አገዛዝ፡ አፓርታይድ ከተገረሠሠ ከአሥር ዓመታት በኋላ የተካሄደው የዚሁ ሦስተኛው ነፃና ኅቡዕ ምርጫ ውጤት የኤ ኤን ሲ እና የመሪው የፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ ብቸኛውን አመራር አረጋግጦዋል፤ ብዙኃኑን ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን በነጮቹ የዘረኝነት

https://p.dw.com/p/E0l2
የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ
የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪምስል AP

ፖሊሲ አንፃር ያካሄዱትን ወደ አንድ መቶ ዓመት ገደማ የሆነውን የነፃነት ትግል ምዕራፍ ዘግቶዋል፤ መራጩ ሕዝብ በኤ ኤን ሲ ላይ ያለው እምነትም ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ አሳይቶዋል። ይህም ኤ ኤን ሲ ላይ ለደቡብ አፍሪቃ ብቻ ሳይሆን ለመላ አፍሪቃም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አመልክቶዋል፤ ይሁንና፡ የኤ ኤን ሲ ፓርቲ፡ ቢፈልግም እንኳን ይህ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት መቻሉ አጠራጣሪ ነው።

የአፍሪቃውያኑ ብሔረተኞች ኮንግረስ፡ ኤ ኤን ሲ በብሔራዊውና ባካባቢያዊው ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ ድል እንደሚቀዳጅና አዲሱ ምክር ቤትም ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪን ከአሥራ አንድ ቀን በኋላ ዳግም እንደሚመርጥ ገና ከምርጫው በፊት ግልፅ ነበር፤ ሲያጠያይቅ የሰነበተው ኤ ኤን ሲ በምክር ቤት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ለመለወጥ የሚያስችለውን ሁለት ሦስተኛውን ድምፅ ያገኛል አያገኝም የሚለው ጉዳይ ነበር። መራጩ ሕዝብ ከጥቂት ቀናት በፊት ባካሄደው ዴሞክራሲያዊው ምርጫ ይህንኑ ኃላፊነት ቢያንስ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለኤ ኤን ሲ ሰጥተዋል። በሌሎች አፍሪቃውያት ሀገሮች የሚታየውን ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር ፍፁሙ የድምፅ ብልጫ የሚያስፈልግበት አሠራር አሁን በደቡብ አፍሪቃም ገሀድ ሆኖዋል፤ ይሁንና፡ ደቡብ አፍሪቃን፡ ሞገሥ ካገኙት ከጥቂቶቹ የአህጉሩ መንግሥታት በስተቀር፡ ከሌሎቹ የይስሙላውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ካቋቋሙት ብዙዎቹ አፍሪቃውያት ሀገሮች ልዩ የሚያደርጋት ወሳኙ ነጥብ፡ የደቡብ አፍሪቃ የምርጫ ኮሚስዮን ጠቅላላውን ምክር ቤታዊ ምርጫ በጥንቃቄ ማዘጋጀቱ፡ ምርጫውን ግልፅ፡ ነፃ እና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ማካሄዱና መራጩ ሕዝብም በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል የሚመርጥበትን ዕድል ማቅረቡ ነው።

የመምረጥ መብት ያላቸው ደቡብ አፍሪቃዋንም በዚሁ ዕድል ተጠቅመው፡ ድምፃቸውን ሀገሪቱን ከዘር አድልዎ አመራርና ከድህነት ቀንበር ላላቀቀው፡ እንዲሁም ለብዙኋኑ ድሆች ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ቢያንስ መጠነኛውን ሁነኛ የኅልውና ትርጉም ላስገኘው የፖለቲካ ኃይል-ኤ ኤን ሲ ሰጥተዋል። ምንም እንኳን ብልፅግና፡ ነፃነትና ክብር ይገኛል የሚለው ትፅቢት እንደተጠበቀው ተፋጥኖ በሰፊው ገሀድ ባይሆንም፡ ኤ ኤን ሲ አሁንም እንደበፊቱ በሀገሪቱ ተወዳጁ ፓርቲ ነው።
ደቡብ አፍሪቃ ባለፉት አሥር ዓመታት የመጀመሪያዋን ዴሞክራሲያዊ ትምህርት አግኝታለች፤ በሽግግሩ ዘመን ከታየው ፖለቲካዊ የኃይል ተግባርም ተላቃለች። ይህ አዲስ ተስፋ ከመፈንጠቁ ሌላ ለደቡብ አፍሪቃን ከሌሎቹ አፍሪቃውያት ሀገሮች የተሻለ ገፅታ አሰጥቶዋታል። ይሁንና፡ ደቡብ አፍሪቃ ሁለተኛውን የዴሞክራሲ ትምህርት በመማር፡ የኤ ኤን ሲ አመራር ወደ አንድ ፓርቲ አምባገነን አገዛዝ እንዳይቀየር ማከላከል ይኖርባታል። ይህ ለአፍሪቃ ደህና ቀን ታስገኝ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለባት ደቡብ አፍሪቃን እንደሌሎቹ ዴሞክራሲ እንደጎደለባቸው አፍሪቃውያት ሀገሮች እንዳያደርግ ያሠጋል፤ ምክንያቱም፡ ሥልጣን ለሙስና የሚጋብዝበትና ፍፁሙ ሥልጣንም ጨርሶ ሙስና ውስጥ የሚያዘፍቅበት ሁኔታ ደቡብ አፍሪቃንም ሊነካ ይችላልና።

ኤ ኤንሲ በጥሬ አላባ በታደለችውና እንደ ስፋትዋ ብዙ ሕዝብ በማይኖርባት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ፍትሓዊና የተመጣጠነ የመሬት ድልድል ማስገኘት፡ ቀሣፊውን ኤቸ አይ ቪ ኤድስ መታገል እና ተጨማሪ የሥራ ቦታ የመፍጠር ትልቅ ሥራ ይጠብቀዋል። ይህንኑ ኃላፊነት የሚወጣበትም ሥራ በፓርቲው ውስጥ የታመቀውን ልዩነት ይፋ ሊያወጣና የአንድ ፓርቲ አምባገነን አገዛዝ ገሀድ የሚሆንበትን ሂደት በጊዜው ሊያስቆም ይችላል። በሀገሪቱ ያሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተጠብቀው እንዲቆዩና እንዲሻሻሉ ከተፈለገም፡ መራጩ ሕዝብ ፖለቲካዊ ንቃተ ኅሊናውን ማዳበር ይጠበቅበታል። ይህ በበኩሉ ቢያንስ ለብዙኃኑ የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ጥቅም ሊያመጣ የሚችል የኤኮኖሚ ዕድገት ሊያስገኝ ይችላል። ከዚያም አልፎ ለመላ አፍሪቃ ሁነኛ አቅጣጫ ጠቋሚ ሊሆን እንደሚችል ተመልክቶዋል።