1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ስደተኞች ሥጋት ና ሠልፍ

ዓርብ፣ የካቲት 6 2007

ደቡብ አፍሪቃ ከዘር መድሎ ሥርዓት ነፃ ከወጣች ወዲሕ ከ1,6 ሚሊዮን የሚበልጥ ስደተኞች ይኖሩባታል ተብሎ ይገመታል።የነጭ ዘረኞቹ ሥራዓት «ሐገር አልባ» አድርጓቸዉ የነበሩት የቀድሞዎቹ ስደተኞች ግን የዛሬዉቹን ለማስታናገድ የፈቀዱ አልመሰሉም።

https://p.dw.com/p/1EbGN
2010
ምስል picture-alliance/dpa

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በሐገሩ ለሚኖሩ የዉጪ ሐገር በተለይም ለአፍሪቃዉያን ሥደተኞች ተገቢዉን ከለላና ጥበቃ እንዲያደርግላቸዉ ስደተኞቹ ጠየቁ።ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ ደቡብ አፍሪቃ በሚኖሩ የሌላ የአፍሪቃ ሐገራት ስደተኞች ላይ የሚፈፀመዉ ግድያ፤ድብደባና ዘረፋ ባለፉት አራት ሳምንታት እየተባባሳ ነዉ።ትናንት ጁሐንስበርግ አደባባይ የተሰለፉት ስደተኞች እንዳስታወቁት የሚፈፀምባቸዉን በደል ለማስወገድ የደቡብ አፍሪቃ ፀጥታ አስከባሪዎች ብዙም አልጣሩም።

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ የዉጪ ዜጎች፤ በተለይም አፍሪቃዉያን ስደተኞች ሲገደሉ፤ሲደበደቡና ሲዘረፉ፤ ያሁኑ በርግጥ የመጀመሪያዉ አይደለም።ካንድ ወር በፊት ስዌቶ-ጁሐንስበርግ ዉስጥ የዉጪ ተወላጆችን ሱቅ ለመዝረፍ ሞከረ የተባለ አንድ የአስራ-አራት ዓመት ወጣት ከተገደለ ወዲሕ ግን ግፍ፤ በደሉ የዉሎ አምሽቶ ትዕይንት ሆኗል።

በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ሊቀመንበር አቶ ታምሩ አበበ እንደሚሉት ባለፈዉ አንድ ወር ዉስጥ ብቻ ስድስት ኢትዮጵያዉያን ተገድለዋል፤ብዙዎች ተደብድበዋል። ተዘርፈዋልም።

Ausländerfeindlichkeit in Südafrika
ምስል DW

የትናንቱን የአደባባይ ሠልፍ ካደራጁት ተቋማት ዋነኛዉ የአፍሪቃዉያን የዉጪ ነዋሪዎች መድረክ የተሰኘዉ ማሕበር ነዉ።የማሕበሩ ፕሬዝዳንት ባፉ ክሎድ እንደሚሉት ፖሊስ በዉጪ ዜጎች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት ለመከላከል ብዙም የፈየደዉ የለም።እንዲያዉም አንዳዴ ፀጥታ አስከባሪዎች የዉጪ ዜጎች ሲደበደቡና ሲዘረፉ እያዩ እንዳላዩ ሆነዉ ያልፋሉ።ወይም ጥቃቱን ፈጥነዉ አያስቆሙም።ይሕ ይቁም ነዉ-የሰድተኛዉ ጥያቄ፤ በባፉ አገላለጥ «ጥበቃ ይደረግልን።»

«ይበልጥ ጥበቃ እንዲደረግልን ነዉ የምንጠይቀዉ።ምክንያቱም ይሕ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ አንዳዴ በዉጪ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈፀም ፖሊስ ዝም ብሎ የሚያበት አጋጣሚ አለ።ሥለዚሕ ፖሊሶቹ ጥበቃ እንዲያደርጉልንና የዉጪ ተወላጆችም (የመኖር) መብት እንዳለን እንዲያዉቁት ነዉ።»

የደቡብ አፍሪቃ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት እንዳዲስ ያገረሸዉ የዉጪ ተወላጆች ጥላቻ፤ ግድያና ዘረፋ መነሻዉ ለአካለ መጠን ያልደረሰዉ ደቡብ አፍሪቃዊ ወጣት መገደል ነዉ።አቶ ታምሩ ግን የወጣቱ መገደል «ለኳሽ» ሰበብ እንጂ ትክክለኛዉ ምክንያት አይደለም ባይ ናቸዉ።አቶ ታምሩ እንደሚሉት ስደተኛዉ የማጅራት መቺዉም፤ ሥራ በማጣቱ፤ በመንግሥት አሰራር እና በባለስልጣናቱ ሙስና የተበሳጨዉም ሁሉ ዒላማ ሆኗል።

Ausländerfeindlichkeit in Südafrika
ምስል DW

ደቡብ አፍሪቃ ከዘር መድሎ ሥርዓት ነፃ ከወጣች ወዲሕ ከ1,6 ሚሊዮን የሚበልጥ ስደተኞች ይኖሩባታል ተብሎ ይገመታል።የነጭ ዘረኞቹ ሥራዓት «ሐገር አልባ» አድርጓቸዉ የነበሩት የቀድሞዎቹ ስደተኞች ግን የዛሬዉቹን ለማስታናገድ የፈቀዱ አልመሰሉም።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ