1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ክልል፤ የአባይ ጉዳይ እና የትግራይ «ምርጫ»

ዓርብ፣ ሰኔ 19 2012

የትግራይ ክልል ምርጫ ለማከናወን ድጋፍ እንዲደረግለት ምርጫ ቦርድን መጠየቊ እና ጥያቄው «ሕጋዊ» አለመኾኑ መነገሩ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል። ሲዳማን ተከትሎ በደቡብ ክልል የተለያዩ ብሔሮች የክልል ጥያቄ ማስነሳታቸውም የመነጋገሪያ ነጥብ ኾኗል። የ«ሕዳሴው ግድብ» ላይ የተሰጡ አስተያየቶችንም አካተናል።

https://p.dw.com/p/3eOb3
Äthiopien Luftbild Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል DW/Negassa Desalegen

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የትግራይ ክልል ምርጫ ለማከናወን ድጋፍ እንዲደረግለት ምርጫ ቦርድን መጠየቊ እና ጥያቄው «ሕጋዊ» አለመኾኑ መነገሩ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል። የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ያደነቊ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ የትግራይ ክልል ምርጫ ለማከናወን መወሰኑን የደገፉ፤ ከአላስፈላጊ እልህ ይልቅ መነጋገሩ እንደሚበጅ አጽንኦት የሰጡ በርካቶች ናቸው። የሲዳማ ክልልን ተከትሎ በደቡብ ክልል የተለያዩ ብሔሮች ተመሳሳይ ጥያቄ ማስነሳታቸውም ሌላኛው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የመነጋገሪያ ነጥብ ኾኗል። የዛሬው መሰናዶዋችን የ«ሕዳሴው ግድብ» ላይ የተሰጡ አስተያየቶችም ታክለውበታል።

የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ»

የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ»ን በተመለከተ ኢትዮጵያ እስካሁን የያዘችውን አቋም በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ደግፈዋል። በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው፦ኢትዮጵያ ለየትኛውም ጫና እንደማትንበረከክ መግለጣቸው እና ግብጽ ከእንግዲህ ድርድሩን አቋርጣ የምትወጣ ከኾነ «ከዚህ በኋላ ለድርድር አንቀመጥም» ማለታቸውን ብዙዎች ቆራጥ ውሳኔ ብለውታል።

Äthiopien Addis Abeba | Report | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል DW/N. Desalegen

በማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ፦ «የእኔ ግድብ ነው»፣ «በቃ ግድቡን ሙሉት» እና «ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ባለመብት» የሚሉ መልእክቶች በስፋት ተንጸባርቀዋል።  ኢትዮጵያ እንደ ግብጾች ኹሉ በተቀናጀ መልክ ስለግድቡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባት የሚጠቁሙ መልእክቶችም ተንሸራሽረዋል። በአባይ ግድብ ድርድር ለግብጽ ማድላቷን በምታስተላልፋቸው የተለያዩ መልእክቶች መሸሸግ የተሳናት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነዋሪ የኾኑ ጥቁር እንደራሴዎች እና ከንቲባዎች ለኢትዮጵያ ድምፃቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።

ይኽን አስመልክቶ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር፦ «በአሜሪካ የጥቁር ከንቲባዎች ኮንፈረንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚና እና ጸሐፊ የሆኑት ቫኒሳ ዊሊያምስ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሆነው እንደሚሰሩ ገለፁ» ሲል ያወጣውን ጽሑፍ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተቀባብለውታል። በአሜሪካ የጥቁር ከንቲባዎችን ጉባኤ (CBM)  በዓለም ዙሪያ ከ39,000 በላይ ጥቁር ከንቲባዎችን እና የተመረጡ ባለሥልጣናትን የሚወክል ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።

የአባይ ግድብ ጉዳይ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ሰዎችን ተመሳሳይ ወይንም ተቀራራቢ አቋም ማስያዙን የማኅበራዊ አውታር ጽሑፎች ይጠቊማሉ።  ኾኖም አልፎ አልፎ ከያዙት የመንግሥት ስልጣን አንጻር የማይገቡ አስተያየት የሚሰጡ ዲፕሎማቶች በተለያዩ ሃገራት መታየታቸው ብዙዎችን አስደምሟል ብሎም አስቆጥቷል። ከእነዚህ ከዲፕሎማቶች በኩል የሚሰጡ አስተያየቶች በሌሎች ሀገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እና በአባይ ግድቡ ዙሪያ ላይም ተንጸባርቀዋል።

በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የጻፉት እና በርካቶች የተቀባበሉት ጽሑፍ አምባሳደሩ መንግስት በአባይ ጉዳይ ግብጽ ላይ ከያዘው አቋም በሚጻረር መልኩ በእጅ አዙር ግብጽን የሚደግፍ ነው በሚል በብርቱ አስተችቷቸዋል። የአምባሳደሩ ጽሑፍ፦ «ዛሬም ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚያናቁረን የሚኒሊክ ጦስ መሆኑ መዘንጋት የለበትም» በማለት ይቀጥላል። «በአባይ ወንዝ ላይ ከጣና ጀምሮ ምንም አይነት ግንባታ ላይገነባ፤ ወይንም እንዲገነባ ላይፈቅድ ለእንግሊዞች የፈረመ ሚኒሊክ መሆኑ ተረሳ?» በማለትም ጽፈዋል።

የዳግማዊ ዐጤ ምንሊክ የመታሰቢያ ሐውልት፥ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
የዳግማዊ ዐጤ ምንሊክ የመታሰቢያ ሐውልት፥ አዲስ አበባ ኢትዮጵያምስል DW

ብዙዎች አባባሉን በመረጃ ያልተፈገፈ እና የተፋለሰ ብለዋል። በአምባሳደር ደረጃ ከሚገኝ ሰው እንዲህ አይነት አስተያየት ሊሰጥ አይገባም በማለት ብዙዎች በአስተያየቱ መቆጣታቸውን በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አንጸባርቀዋል። ጌቶ ደምሰው በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «የተከበሩ አምባሳደ ሱሌይማን ዴዴፎ ሆይ። እርስዎ አምባሣደር ሆነው ሲሾሙ ባሉበት ሀገር የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በመገንባት ታላቅ የዲኘሎማሲ ስራ በመሥራት ለሀገርዎ ውለታ እንዲውሉ እንጂ በበሬ ወለደ ታሪክ ለግብፅ ጥብቅና እንዲቆሙ እንዳልሆነ ያውቃሉ» ብሏል።

ጥላሁን ፅጌ ትዊተር ላይ፦ «ሱሌይማን ዴዴፎ አሁንም አልተባረረም አይደል? አሁንም ኢትዮጵያን ወክሎ ለግብፅ የሚከራከር አምባሳደር ሆኖ እንደተሾመ ነው አይደል?» ሲል ጠይቋል።

የሲዳማ ክልልነት 

ወደ ቀጣዩ ርእሰ ጉዳይ ማለትም የሲዳማ ክልልነት ሒደት ስንሸጋገርም በአባይ ግድብ ላይ እንደተነሳው የዲፕሎማት አወዛጋቢ አስተያየት አይነት መንግሥትን በሚወክሉ ዲፕሎማት መሰጠቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን አስቆጥቷል። የቀደሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ እንዲሁም በጃፓን አምባሳደር የነበሩት በአሁኑ ወቅት በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባ አምባሳደር ማርቆስ ርቄ ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ እና አማርኛ አዛንቀው የሰጡት አስተያየት ነው በሚል የተንሸራሸረው ጽሑፍ ከፍተኛ ትችት አስከትሏል።  

Äthiopien SNNPR Konferenz zur Sidama-Zone
ምስል DW/S. Wegayehu

«ሲዳማ ውስጥ ዛሬ እና በሚቀጥሉት ቀናት የእራስን እድል መሰሰን የእራስን እድል መወሰን ነው። መቼም የሚቀፊፋቸዉ ጥቂት ሰዎች እዚህ ሰፈር እንዳሉ እናውቃለን...» ይላል የዲፕሎማቱ ጽሑፍ። ጽሑፋቸው ላይ አስተያየት ለመስጠት ብቅ ያሉ ሰዎችንም ወረድ ብለውም ዲፕሎማቱ በቃላት ዘልፈዋል።

ዲፕሎማቶች ማኅበራዊ መገናኛዎች ላይ የሚሰጡት አስተያየት አንዳንዴም ወደ አልባሌ ንትርክ እና ስድድብ መውረዱ እንደሚያሳስባቸው የገለጡ አስተያየት ሰጪዎች መንግስት ዲፕሎማት ብሎ የሚልካቸው ሰዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ፖለቲከኛው ኤፍሬም ማዴቦ በዲፕሎማቱ አስተያየት ማፈራቸውን ጠቅሰዋል ትዊተር ላይ።  «እንኳን አገር እራሱን የማይወክል» ያሏቸው ሰዎች «አምባሳደር ዲፕሎማት እየተባሉ አገር መንደር» ኾነች ብለዋል።

አዲሱ የሲዳማ ክልል በመጪው ሳምንት የክልላዊ መንግስት ምስረታ ለማካኼድ አስፈላጊውን መሰናዶ ማጠናቀቁን ባስታወቀበት በአኹነ ወቅት ሌሎች በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሔሮችም ክልል የመኾን መብት ለእኛም ሊከበር ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። የዎላይታ ዞን እንዲሁም የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤቶችን ጨምሮ ጥያቄዎች እዚህም እዚያም ብቅ ማለታቸው ቀድሞ በርካታ ብሔሮች ተሰባስበው የሚኖሩበት የደቡብ ክልልን ወደ መበታተን ሊያመራው ይችላል ሲሉም አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በዛው መጠን ሌሎች ብሔሮች በሌሎች ክልሎች መኖራቸው ሀገር እንድትበተን አላደረገም ስለዚህ ጥያቄ ያነሱ ብሔሮችም መብታቸው ሊከበር ይገባል የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

ኑርሑሴን አብዱልቃድር፦ «ደቡብ ክልል ጥሩ ሽንሸና ላይ ናቸው» ሲል፤ ኤጂ ማክ ደግሞ፦ «ነገ ደግሞ ሀገር ልሁን ይቀጥላል እድሜ ይስጠን» ብሏል። አሸናፊ ሚልኪያስ እዛው ፌስቡክ ላይ በሰጠው አስተያየት፦ «ኦሮሚያ ፡ አማራ፡ ትግራይ ፡ ጋምቤላ ፡ አፋር ፡ ሶማሌ ክልል ሲሆኑ ያልፈረሰችው ኢትዮጵያ ሲዳማ ክልል ስለሆነ አትፈርስም» ብሏል። 

«ዋናዎቹን ከጀርባ ሆኖ ሚዲያ እየፈቀዱ ጉዳዩ ወደፊት ገፍቶ እንዲመጣ እየሰሩ ያሉትን መንግስት አደብ ማስገዛት ካልቻለ ነገሩ ማቆሚያ አይኖረውም። የዶ/ር አብይ መንግስት ቆፍጠን ብሎ እነዚህን አፍንጫው ስር ተቀምጦ ሀገር በሚያተራምሱት ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አለበት።» አስተያየቱ የምንተስኖት ቸሩ አምላክ ነው። ሰንደቄ ዕንዳውቄ ደግሞ፦ «መብታችሁ ነው ክልል መሆን የሚል ህገመንግስት ይዞ መከልከል አይቻልምና ክልል የመሆን መብታቸው መፈቀድ አለበት» ብሏል።  ድሬ ድሬ በሰጠው የፌስቡክ አስተያየቱ፦ «ይገርማል ያን የመሰለ የብዙሀን ማሳያ የሆነ ክልል እንዲህ ሲበታተን የእውነት ያማል» የሚል ጽሑፍ አስፍሯል።

ትግራይ ክልልና ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓርማ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓርማ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል ምክር ቤት የቀረበ ያለውን ጥያቄ በድረ ገጹ አስነብቧል። የትግራይ ክልል ምክር ቤት፦ «ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ኃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን» በሚልም ይነበባል ጥያቄው።  «የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲፈጸምለት ለቦርዱ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ» በሚል ርእስ ስርም ምርጫ ቦርድ ሰኔ 17 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ጥያቄውን «ሕጋዊ መሠረት የለውም» ብሏል። ይኽንኑ የሚያብራራ ጽሑፍም በይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ አስነብቧል።

ኤልያስ ጎዲፋይ ትዊተር ላይ፦ «ምርጫ ቦርድ ለትግራይ መንግስት የሚያስፈልገውን የምርጫ ቁሰቁስ ኣለቀርብም ብላል። እንግዲህ ጥሪ የተደረገላቸው የሰርጉ ኣስተናጋጆች ኣናስተናግድም ካሉ ኣሰተናጋጅ ይቀየራል እንጂ የሰርጉ ቀን ኣይቀርም» ሲል ጽፏል። «ትህነግ ምርጫ አታደርግም። ከአብይ ጋር ለመደራደር ትሞክራለች» የሚል አስተያየት ትዊተር ላይ ያሰፈረው ደግሞ ሃይመሌ ነው። «ህወሃት የራሴን የምርጫ ቦርድ አቋቁሜ፣ ራሴን ታዝቤ፣ ኢትዮጵያንና ዓለምን የሚያስደምም "ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ" አድርጌ የለመድኩትን መቶ በመቶ አሸንፋለሁ እንደምትል ይጠበቃል። መቼም ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም» ይኽ ደግሞ የተሰማ በላይ አስተያየት ነው። ከእልህ ይልቅ ግን መነጋገር እና ወደ አላስፈላጊ ነገሮች አለማምራት እንደሚሻልም አስተያየታቸውን የሰጡ በርካቶች ናቸው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ