1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳርፉርን በተመለከተ የዩናይትድ ስቴትስ ሃሳብ ጫና በዝቶበታል

ዓርብ፣ የካቲት 11 1997

የዳርፉር የጦር ወንጀለኞች ጉዳይ በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት መታየት አለበት የሚለዉ ሃሳብ አሁንም ግፊቱ ቀጥሏል። ከተቃዋሚዎቻቸዉ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ወገኖች አስተዳደራቸዉ የሰዉዘር ማጥፋት ነዉ ያዉን የዳርፉር እልቂት በሄጉ አለም አቀፍ የወንጀል ችሎት እንዲታይ ማድረግ እንዳለበት እየተጠየቁ ነዉ።

https://p.dw.com/p/E0kL

ይህ ሁሉ ግፊት ቢኖርም እምቢተኛዋ ዩናይትድ ስቴትስ ጉዳዩን እልባት ወደማያገኝበት ችሎት ካልሄደ ማለቷን ቀጥላበታለች።
ረጅም ሰዓት የፈጀዉና ለፀጥታዉ ምክር ቤት በትላንትናዉ ዕለት በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ካናዳዊቷ ሉዊስ አርቦር የቀረበዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ የሄጉ ችሎት 300,000 አፍሪካዉያን ያለቁበት የዳርፉር ጉዳይ ሊታይበት የሚገባ ወሳኝ መድረክ ነዉ።
እንደ ኮሚሺነሯ አገላለፅ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ችሎት መምራቱ እየተካሄደ ያለዉን ህገወጥ ተግባር ለማስቆምና ወደፊትም እንዳይፈፀም ለማድረግ አይነተኛ መንገድ ነዉ።
የአርቦር ሃሳብ በአለም ዙሪያ በታወቁት ሁለት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅች በኒዉ ዮርኩ ሂዩማን ራይትስ ዎችና በለንደኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የድጋፍ ተጨማሪ አስተያየት ተጠናክሯል።
የአምነስቲ አፍሪካ የፕሮግራም ዳይሬክተር ኮልዋሎ ኦላኒያ እንዳሉት የሱዳን ህዝብ ፍትህና ካሳ ያስፈልገዋል።
ገናለገና ከዩናይትድ ስቴትስ የፓለቲካ ዕቅድ ጋር የሚጣጣም አይደለም በሚል ተልካሻ ምክንያት ይህን ፍትህ ሊያጡ አይገባም ነዉ መከራከሪያቸዉ።
የሂዩማን ራይትስ ዎች አለም አቀፍ የፍትህ ፕሮግራም ሃላፊ ሪቻርድ ዲከርም በዳርፉር የሚገኘዉ ህዝብ እየደረሰበት ባለዉ ገደብ የለሽ የጭካኔ ተግባር ሳቢያ መሰቃየቱን መቀጠሉን ነዉ ያስታወቁት።
በመሆኑም የቡሽ አስተዳደር የጉዳዩን በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት መቅረብ አስመልክቶ እያሳየ ያለዉ ተቃዉሞ የዳርፉር ህዝብ ፍትህ እንዳያገኝ ከማጓተት በቀር የሚረባ እንዳልሆነም ጨምረዉ ገልፀዋል።
የፀጥታዉ ምክር ቤትም የተባበሩት መንግስታት የሰየመዉ ኮሚሽን ያቀረበዉን ጥያቄ በማፅደቁ የቡሽ አስተዳደር ጉዳዩን ለመግፋት በሚያዳግት አጣብቂኝ ዉስጥ ቢሆንም ተስፋ ሰጪ ነገር አልታየም።
የአስተዳደሩ ፍላጎት የዳርፉር ጉዳይ በሄግ ሳይሆን በሩዋንዳ የተፈፀመዉን የሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀል አጣርቶ ለማቅረብ አስር አመታትም ፈጅቶ ባልቋጨዉ በአሩሻ ታንዛንያ ችሎት ይታይ የሚል ነበር።
ዲከር እንደሚሉት ለዳርፉር ጉዳይ አዲስ ችሎት በዚያ ይከፈት የሚለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጥያቄ የሚያሳየዉ ለሚከተለዉ መፍትሄ ያላትን ጥላቻ ብቻ ነዉ።
ቢሆን እንኳን አዲሱ ተጨማሪ ችሎት ፍጥነት የማይኖረዉና የታሰበዉ ስራም በአግባቡ እንዲከናወን በስልጣኑ መቆየት የሚችል አይነት አይደለም።
እንደሳቸዉ አገላለፅ የአሩሻዉ ችሎት ማየት የጀመረዉን የሩዋንዳ ጉዳይ በዕቅዱ መሰረት ለማከናወን እንኳን አለ የተባለዉን የመረጃ ምንጭ ሁሉ አዳርሶ መጨረስ ይኖርበታል።
የዩናይትድ ስቴትስ ተቀፅላ ችሎት በዚህ ሁኔታ ላይ እንዲደረብና እንዲታይ መፈለግ ማለት ቀድሞ በሞላ መኪና ዉስጥ ተጨማሪ ተጓዦች አሳፍሮ ይጨናነቁ ብሎ እንደማለት ነዉ ይላሉ ዲከር።
በአንፃሩ ግን ሁለት አመት የሞላዉ የአለም አቀፍ የወንጀል ችሎት ጉዳዮች ብዛት ያልተጣበበ፤ የተሟላ የሰዉሃይልና የምርምር ተግባር ማከናወን የሚያስችል አቅም ያለዉ ነዉ።
በተጨማሪም አመሰራረቱ ሲታሰብ በማያሻማ ሁኔታ የጦር ወንጀሎችን፤ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ አስከፉ ተግባራትንና የሰዉ ዘር ማጥፋትን ለመዳነት ታስቦ ነበር።
ያም ቢሆን የቡሽ አስተዳደር ከመሰረቱ የዚህን ችሎት የመቋቋም ሃሳብ ከመቃወም አንስቶ ችሎቱ በሚሰራቸዉ ስራዎች ለመተባበር ፈቃደኛ አልነበረም።
ገና ከጠዋቱ ምስረታዉን አስመልክቶ እ.ኤ.አ. በ1998 ዓ.ም. በሮም በተደረገዉ ስብሰባ የተወሰነዉን ዉሳኔ በመደገፍ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን እንዲሁም የአፍሪካ መንግስታት በመስማማት 139አገራት ሲፈርሙ በግንባር ቀደምትነት የተቃወመች እሷ ነበረች።
ከዚህ በመነሳትም ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን የጦር ኃይልና በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የተለየ የሰላምና የደህንነት ሃላፊነት በተመለከተ አለም አቀፍ ችሎቱ ለሉአላዊነቷ የሚያሰጋ እንደሆነ በወቅቱ በይፋ ተናገረች።
በእሷ እምነት አለም አቀፍ የወንጀል ችሎቱ በተለይ በፓለቲካ አመለካከት በሚፈጠሩ ክሶች ሳቢያ ዜጎቿ ላይ ያነጣጠረ አደጋ ሊጋርጥ ይችላል ባይ ናት።
በተጨማሪም የፀጥቱ ምክር ቤት ባለፈዉ አመት ተባባሪ ያልሆኑ አገራት ዜጎችን ከአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ነፃ እንዲሆኑ አናደርግም የሚል ዉሳኔ ባስተላለፈበት ወቅት በተባበሩት መንግስታት ዉስጥ በተለያየ ሃላፊነት ላይ የነበሩ ዜጎቿ እንዲለቁ አድርጋለች።
ትናንት ከዉይይቱ በኋላ የአዉሮፓ ህብረት የዉጪ ጊዳይ ፓሊስ ተወካይ ዣቪየር ሶላና የዩናይትድ ስቴትስ ተቃዉሞ ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸዉ ነዉ የተናገሩት።
ዜጎቿ ከአሜሪካ ዉጪ ባለ ችሎት እንዲዳኙ ያለመፈለግ አቋም ካላት አገር ጋር በሚደረገዉ ክርክርም ለዉጥ እናመጣለን ብዬ አላስብም ባይ ናቸዉ ሶላና።
በሰብአዊ መብተሟጋቾቹ ወገኖችም ሆነ በተባበሩት መንስግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኮሚሽን እምነት ደግሞ የአሜሪካም ሆነ የሱዳን መንግስት የሚያቀርቡት አማራጭ ችሎት ተቀባይነት አይኖረዉም።