1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳዳብ የሚገኙ ሶማሊያውያን

ረቡዕ፣ ኅዳር 1 2008

ባለፈው ሚያዚያ ወር ጋሪሳ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ከደረሰው የአሸባብ ጥቃት በኋላ የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ዳዳብ የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ እንዲዘጋ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል። የግዳጅ ስደተኞችን ማፈናቀል ስለማይቻል በተለይ የሶማሊያ ስደተኞች በፍቃደኝነት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ ነው።

https://p.dw.com/p/1H47o
Flüchtlingslager Dadaab Kenia
ምስል AP

[No title]

ጋሪሳ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ የአሸባብ ቡድን በሰነዘረው ጥቃት 150 የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ የኬንያ የፀጥታ ፖሊሲ ከባድ ትችት ተሰንዝሮበታል።ያኔም የሀገሪቷን ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ዳዳብ በሶስት ወራት ውስጥ እንዲዘጋ ነበር ወዲያው ለስደተኞች መርጃ ድርጅቱ UNHCR መልዕክት ያስተላለፉት።« ስደተኞቹ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ ሌላ ቦታ ካልሰፈሩ ፤ በጭነት መኪና እና አውቶቢስ እየጫንን ነው ወደ ሀገራቸው የምንወስዳቸው»
ይህ የሩቶ ንግግርም በርካታ የዳዳብ ስደተኞችን ክፉኛ ስጋት ላይ ጥሎ ነበር። «ሶማሊያ ያለው ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም። እኛ አንመለስም። የኬንያ መንግሥት ሁሉም ሶማሊያውያን አሸባሪ እንዳልሆኑ ከግንዛቤ ሊያስገባ ይገባል።»ይላሉ አንድ የሶማሊያ ስደተኛ። ሶማሌዎች ኬንያ ውስጥ በአይነ ቁራኛ ይታያሉ።በተለይ የናይሮቢ ከተማ አካል በሆነችው ኢስትሊ በርካታ ሶማሊያውያን ይኖራሉ። በአንድ ወቅት የሽብር ማስጠንቀቂያ ደርሶም በርካቶች ለማጣራት ነው ተብለው በቁጥጥር ስር ውለዋል። በተለይ ዳዳብ የሚገኙ ስደተኞች ላይ ጥርጣሬው ከፍተኛ ነው።በግዳጅ ሰዎችን ማፈናቀል የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ቤት የማይቀበለው ነው። ይህ ኬንያም ያፀደቀችው ነው ይላሉ ዱክ ምዋንቻ ከUNHCR ፤ « ስደተኞች በፍቃደኝነት ነው መመለስ ወይም ወደ ሌላ ቦታ መፈናቀል ያለባቸው። ሰዎች ራሳቸው ናቸው ስለመመለስ መወሰን ያለባቸው። በዓለም አቀፋዊ ህግ መሰረት ማንም ሰው ስደተኞች እንዲመለሱ ማስገደድ አይችልም።»

ብዙ ዳዳብ የሚገኙ ሰዎች ጫና እንደሚደረግባቸው ይናገራሩ። እንደሚጠረጠሩ፣ ክብር እንደማያገኙ ወይም ጠንካራ የፀጥታ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው በርካታ ሶማሊያውያን ይናገራሉ።«እኔ የሶማሊያ ዜግነት ነው ያለኝ። ተወልጄ ያደኩት ግን ኬንያ ነው። ይሁንና እንደ ስደተኛ እና የውጭ ዜጋ ነው የምታየው። ከናይሮቢ ማለፍ እንኳን አይፈቀድልኝም። በነዚህ መጠለያዎች ተወስኜ እገኛለሁ።»
የ23 ዓመቱ ወጣት አብዱላህ የሁለተኛው የስደተኛ ትውልድ ነው። ሶማሊያን እስካሁን ሄዶ ባያውቅም ወደእዛ መሄድ ይፈልጋል። « እስካሁን 5300 በፍቃደኝነት ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ሶማሌዎ አሉ።ይህ ጥሩ ነገር ነው።»
ዳዳብ ውስጥ 350 000 ስደተኞች ይኖራሉ። አብዛኞችም ሶማሊያ ውስጥ እንደ አዲስ ኑሮን መመስረት ይቻላል ብለው አያምኑም። ይህ ማለት ደግሞ መጠለያ ጣቢያው እንዲህ በቀላሉ ሊዘጋ እንደማይችል ነው።

Flüchtinge in Dadaab Kenia
ዳዳብ የሚገኙ ስደተኞችምስል Reuters/Herman Kariuki
Kenia Garissa Universität Anschlag Trauer
የአሸባብ ጥቃት በጋሪሳምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa


ሊንዳ ሽታውደ/ ልደት አበበ
አርያም ተክሌ