1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም ነዉጥ በካርቱም

ሐሙስ፣ ሐምሌ 28 1997

የሱዳን መንግስት ጆን ጋራንግ የሞቱት ሄሊኮፕተራቸዉ በገጠማት መጥፎ የአየር ጠባይ ሳቢያ በደቡብ ሱዳን ከሚገኝ ተራራ ጋር ተላትማ ነዉ ይላል። የተባበሩት መንግስታትም ይህንኑ በማረጋገጥ ተናግሯል ሆኖም በካርቱም የተስፋፋዉ ጭምጭምታ ግን ለጋራንግ ሞት የመንግስት እጅ አለበት የሚለዉን ጥርጣሬ ነዝቷል።

https://p.dw.com/p/E0je

በዚህ ሳቢያም በተለይ የደቡብ ሱዳን አካባቢ ተወላጆችና የጋራንግ ሃሳብ ደጋፊዎች ግጭት ወደቀሰቀሰዉ የተቃዉሞ ሰልፍ እንዲገቡ ገፍቷል።
ባለስልጣናቱም በበኩላቸዉ ጥርጣሬዉን ሃሰት ሲሉ በማጣጣል ተመሳጠሩበት ለተባለዉ የጋራንግ ሞት ትንታኔ በመጠየቅ ላይ ተጠምደዋል።
የጋራንግ ሄሊኮፕተር ሆን ብሎ በተጣለባት አደጋ ነዉ ለመከስከስ የተዳረገችዉ በሚባለዉ ዉንጀላ ላይ የሚሉት ካለ የተጠየቁት የዉጪ መረጃ ካዉንስል ዋና ፀኃፊ የሆኑት ራሺድ ኪዳር ሲመልሱ በዚህ በሃዘን ሰዓት እንዳመጣልን መናገር አንችልም ነዉ ያሉት።
አያይዘዉም የቀድሞዉ የአማፅያን መሪ በዑጋንዳ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት ፈፅመዉ የተመለሱት በዑጋንዳ አዉሮፕላን ነዉ። የሱዳን ባለስልጣናት ስለበረራ ዕቅዳቸዉ የሚያዉቁት ቢኖር ይህን የሰለ ጥቂት መረጃ ብቻ ነበር ብለዋል።
ከዚህ ዉጪ ሰኞ ረፋዱ ላይ መኪናዎችና አዉቶቡሶች መንገዱ ላይ ባለመኖራቸዉ ካርቱም የተወረረች ከተማ መስላ ነበር። የመጀመሪያዉ የጥይት ድምፅ እንደተሰማ ሴቶች ወደየመኖሪያዉ ሲገቡ ወንዶችም ራሳቸዉን ከጥይት ሲከላከሉ ታይቷል።
በርካታ የካርቱም ኗሪዎች በመኖሪያ ቤታቸዉ ጣሪያ ላይ በመዉጣት ከተማዋን ለመቃኘት ባደረጉት ጥረት ፅህፈት ቤታቸዉ ከሚገኝበት ከፕሬዝደንት አልበሽር ቤተመንግስት ጭስ ሲወጣ ከዚያም በከተማዋ የተለያዩ ሶስት ቦታዎች ፍንዳታ ሲከተል ለማየት ችለዋል።
በመሃሉም ፓሊስ ኗሪዎቹን ከየጣሪያዉ እንዲወርዱ ያዘዘ ሲሆን የደህንነት ኃይሎች ከተማዋን ከትላልቅ ህፃዎች አናት ላይ በመዉጣት በተራቸዉ መቃኘት ቀጠሉ።
በዕለቱ ከሰዓት በኋላ ሁሉ ፍንዳታና የጥይት ድምፅ በአብዛኛዉ የካርቱም ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ሲሰማ ነዉ የዋለዉ።
በየመስሪያ ቤቱና በየቤቱ የተሸሸገዉ የከተማዋ ነዋሪም ከታወጀዉ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሌላ የሚያዉቀዉና የሚናገረዉ አልነበረም።
ወደ መሃል ከተማዋ ለመዝለቅ የሞከሩ እግረኞችና የመኪና አሽከሪካሪዎች የከተማዋን አዉራ መንገዶች ባጥለቀለቁት የፓሊስና የጦር ኃይሉ አባላት ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።
የጥበቃ ኃይሎችም ከኋላቸዉ ክፍት በሆኑ መኪኖች ተጭነዉ በከተማዋ መንገዶች ላይ ሲመላለሱ ተስተዉለዋል።
የደንብ ልብስ ያልለበሱ የጥበቃ አባላት ይሁኑ ወይም ኗሪዉ እንደሚለዉ ራሳቸዉን እንዲከላከሉ መሳሪያ የተሰጣቸዉ ባይታወቅም የሲቪል ልብስ የለበሱ መሳሪያ ያነገቡ ሰዎችም መኪና የያዙ ሰላማዊ ሰዎችን እያስቆሙ ሲጠይቁ ነበር።
በነዚሁ የደንብ ልብስ ባልለበሱ ታጣቂዎችም የአመፁ ቀስቃሽ ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ መሬት ላይ ተጥሎ ሲደበደብ በቅርብ ርቀት ማየቱን የአይፒኤስ ዘጋቢ ገልጿል።
ይህ ሁሉ ትርምስ ለአራት ሰዓታት የከተማዋን ፀጥታ ካደፈረሰ በኋላ ካርቱም በመጠኑ የተረጋጋች መሰለች። ባለሱቆችም ከየተሸሸጉበት በመዉጣት በየንብረታቸዉ ላይ የደረሰዉን ጉዳት መቃኘት ጀመሩ። ብዙዎቹም የተሰባበሩ መስታወቶችንና ሸቀጦችን የሚያፀዱበት ጊዜ አልነበራቸዉም።
መንግስት ወዲያዉ የሰዓት ዕላፊ በማወጁም በከተማዋ ይሰማ የነበረዉ የአምቡላንስ የአደጋ ድምፅ ብቻ ነበር።
አያይዞም ከመንግስት የተሰጠዉ መግለጫ ሰላማዊዉ ህዝብ ተረጋግቶ እንዲቆይ የሚማፀን ነበር።
ብዙዎች የጋራንግ ሞት ባለፈዉ ጥር ወር ላይ በሰሜን ሱዳን እስላማዊ መንግስትና በደቡብ ሱዳን በሚንቀሳቀሰዉ የደቡብ ህዝቦች ንቅናቄ SPLM መካከል የተደረሰዉን የሰላም ስምምነት እንዳያደፈርሰዉ ሰግተዋል።
በዛዉ ልክ ደግሞ ጋራንግ አልሞቱም ብለዉ የሚከራከሩ በርካታ ናቸዉ። ጋራንግ በምንም መንገድ አልሞቱም ሞታቸዉ እዉነት ከሆነ እኔም እሞታለሁ ያለዉ የመጨረሻ ስሙን ብቻ ለጋዜጠኛ የነገረዉ የደቡብ ሱዳን ተወላጁ ዊሊያም ነበር።
በስምምነቱ መሰረት ነበር ጋራንግ ከ20 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምክትል ፕሬዝደንትነት ቃለ መሃላ ሊፈፅሙ ወደካርቱም ባለፈዉ ሐምሌ 2 የተገኙት።
አሁንም የበሽር አስተዳደር የሰላም ዉሉ ከጋራንግ ሞትም በኋላ ይቀጥላል በማለት በተደጋጋሚ እየገለፀ ነዉ። የSPLM ኮማንደር የሆኑት ከድርም እንዲሁ የሰላም ስምምነቱ የጋራንግና የበሽር ጉዳይ ሳይሆን በሁለቱም ወገን የሚገኙ የሱዳን ህዝቦች ዉል መሆኑን ነዉ የሚገልፁት።
ሳልቫ ኪር ማያርዲት ናቸዉ በጋራንግ ቦታ ምክትል ፕሬዝደንትነቱን ከደቡብ አማጽያን ወገን የሚይዙት ተብሎ ይጠበቃል።