1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድህነት ቅነሣና የዕርሻ ልማት ወሣኝ ሚና

ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2000

አብዛኛው የታዳጊው ዓለም ሕዝብ በገጠር አካባቢዎች የሚኖር እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ የኤኮኖሚ ኋላ ቀርነት የተነሣ ድህነቱ ይበልጥ ጎልቶ የሚታይበትም የሕብረተሰብ ክፍል ነው። ስለዚህም ድህነትን በከፊል የመቀነሱ የሚሌኒየም ዕቅድ ስኬት እንዲያገኝ የእርሻ ልማትን ማጠናከሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/E0cb
የዓለም ባንክ ዋሺንግተን ዲ.ሲ.
የዓለም ባንክ ዋሺንግተን ዲ.ሲ.ምስል picture-alliance/dpa

የተባበሩት መንግሥታትን ድህነትን በከፊል ለመቀነስ የተያዘ የሚሌኒየም ግብ አብዛኞቹ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ መንግሥታት በተጣለው ዕቅድ በቀሩት ስምንት ዓመታት ውስጥ ዕውን ማድረግ እንደማይችሉ ዛሬ ከሞላ-ጎደል ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉት። በየአገሩ ያለው ውስጣዊ ማሕበራዊና የልማት አቅድ ችግር አንዱ ሲሆን የእርሻ ልማት በሚገባው መጠን አለማደግና የዓለም ንግድም ፍትሃዊነት አጥቶ መቀጠል ዓበይት ምክንያቶቹ ናቸው። በታዳጊ አገሮች የዕርሻ ልማትን በማጠናከር በሚሊያርድ የሚቆጠር ሕዝብን ከከፋ ድህነት ማላቀቅ እንደሚቻል የዓለም ባንክም ዕምነት ነው።

ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው የገንዘብ ተቋም ለታዳጊ አገሮች የልማት ዕርዳታ በማቅረብ ቀደምቱ መሆኑ ይታወቃል። ባንኩ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ባወጣው የዓለም የልማት ዓመታዊ ዘገባ የእርሻ ዕድገትን ለማጠናከር አለመጣር ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ የያዘውን ግብ ከንቱ እንደሚያደርገው አስገንዝቦ ነበር። ከዘገባው ለመረዳት እንደተቻለው በገጠር አካባቢዎች የሚኖረው አብዛኛው፤ ማለት ሁለት-ሰሥተኛው የዓለም ሕዝብ በያመቱ ለታዳጊው ዓለም ከሚቀርበው 100 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕርዳታ የሚያገኘው አራት ከመቶዋን ድርሻ ብቻ ነው። ከዕድገት የተነጠለ ነው ሊባል ይችላል።

ከሣሃራ በታች ባለው የአፍሪቃ ክፍልና በደቡባዊው እሢያ የገጠሩ ድሃ ሕዝብ ቁጥር ዛሬም መጨመሩን አላቋረጠም። የባንኩ ቀደምት የኤኮኖሚ ባለሙያ ፍራንሱዋስ ቡርጊኞን እንደሚሉት ቁጥሩ ከከተማው ድሃ ሲነጻጸር ቢያንስ ለሚቀጥሉት 30ዓመታት የላቀው ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው። መንግሥታቱ በእርሻው ልማት ዘርፍ ላይ ያላችው ትኩረት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ሲጤን እርግጥ ይህ ብዙም አያስደንቅም። ለአጠቃላይ ዕድገታቸው በተለይ በእርሻ ልማትና ከዚሁ በተያያዘ ግብር ላይ ጥገኛ የሆኑት የአካባቢው መንግሥታት የእርሻ ዘርፉን ዕርምጃ ለመደገፍ ቢበዛ አራት በመቶ የምትሆን በጀታቸውን ቢመድቡ ነው። ዋናው የዕድገት ምሶሶ እንግዲህ ተገቢው ክብደት አልተሰጠውም።

ሃቁ ይህ ሲሆን በሌላ በኩል የእርሻ ልማትን በማራመድ ሊገኝ የሚችለው ጥቅም እጅግ ግዙፍ በሆነ ነበር። ከኢንዱስትሪና ከአልግሎት ሰጭው ዘርፍ ሲነጻጸር በእርሻ ልማት መንኮራኩርነት የሚገኝ አጠቃላይ ዕድገት ሕዝብን ከድህነት አዘቅት በማውጣት አራት ዕጅ ፍቱንነት ሊኖረው እንደሚችል ነው የዓለም ባንክ ዓመታዊ ዘገባ ያመለከተው። ለኤኮኖሚ ዕድገት በሚደረገው ጥረት ጠንካራ የእርሻ ልማት አጀንዳን ማተኮሪያ በማድረግ 900 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ ኑሮውን የሚገፋ የታዳጊው ዓለም ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ የእርሻ ልማት የበለጠ ክብደት ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው።

ሮበርት ዞሊክ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት የባንኩ ፕሬዚደንት ሆነው የተሾሙበትን መቶኛ ቀን ምክንያት በማድረግ ባሰሙት የፖሊሲ ንግግር ተቋማቸው በዓለም ኤኮኖሚ ትስስር በግሎባላይዜሺን ሳቢያ በታዳጊ አገሮች ላይ የተደቀነውን ፈተና በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም የሚከተለውን ስልታዊ መርህ ዘርዝረዋል። ጥረታቸውን ድህነትን በመታገሉ አቅጣጫ ለማራመድ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የጠቆሙት። ቀደም ሲል በዚሁ ጉዳይ 24 ዓባላትን ካቀፈው የባንኩ ቦርድ ጋር ከአንድ አስታራቂ ስምምነት ለመድረስ ችለውም ነበር።
በዚሁ መሠረት ቦርዱ ባንኩ ለታዳጊ አገሮች የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለግሉ የኤሚኖሚ ዘርፍ አበዳሪ ከሆነው International Finance Corporation ከተሰኘ ክንፉ በሚገኝ ትርፍ ለማጠናከር ወስኗል። ዕርምጃው እስካሁን ዋና ተልዕኮው ለድሆች አገሮች መዋቅራዊ ግንባታ ብድር መስጠት የነበረውን ኮርፖሬሺን ሚና ከፍ የሚያደርግም ነው። በአጠቃላይ የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት የተቋማችውን ሶሥት ቢሊዮን ዶላር ለዓለምአቀፉ የልማት ማሕበር ተግባር በመመደብ አበዳሪ መንግሥታት 80 የሚሆኑ ድሆች ሃገራትን ለመርዳት ከ 2009 እስከ 2011 ኪሣቸውን ሰፋ አድርገው እንዲከፍቱ ፈተና ነው የደቀኑት። ባለሥልጣኑ የዕድገት ዕድል መፍጠሩ ብቻ ሣይሆን በድሆችና-በሃብታሞች መካከል ያለውን ልዩነት ያሰፋው የዓለም አኮኖሚ ይበልጥ መተሳሰር በፈጠረው ሁኔታ የዓለም ባንክ ድህነትን ለመታገል ይበልጥ የፈጠራ ችሎታ እንደሚያስፈልገው ጠንቅቀው የተረዱ ይመስላል።
ጥያቄው ሃሣቡን ገቢር ለማድረግ ዕርምጃ መታየቱ ላይ ነው። ቀደም ሲል በ 80ኛና በ 90ኛዎቹ ዓመታት መካከል በገጠር ልማት ረገድ የባንኩ ድጋፍ ማቆልቆል ታይቶበታል። እንደገና መንሰራራት የያዘው ከአራት ዓመታት ወዲህ ነው። ባንኩ በዚህ ዓመት ለእርሻው ዘርፍ 3,1 ቢሊዮን ዶላር መመደቡ ደግሞ የዕድገት አዝማሚያን ይጠቁማል። ዓመታዊው ዘገባ ያመለከተው እንዲያውም ጥረቱ ከፊናንስ አቅርቦት ባሻገር ሌሎች ዕርምጃዎችን መጠቅለል እንዳለበት ነው። የምግብ እህል እንዲጨምር ምርታማነት መጠናከር ይኖርበታል። መለስተኛ ገበሬዎች ከዓለም ገበያ በፍጥነት መስፋፋት እንዲጠቀሙ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶች ማቅረብ ይችሉ ዘንድ መደገፍ አለባቸው። ሃብታም አገሮች በፊናቸው ድሆቹን የሚጎዳ ፖሊሲያቸውን መጠገናቸውም ግድ ነው።

ለምሳሌ ያህል አሜሪካ በአፍሪቃ አምራቾች ላይ የዋጋ ጫና የፈጠረውን የጥጥ ድጎማ መቀነስ ይኖርባታል። በሃብታም አገሮች የታሪፍ ገደብና ሰፊ ድጎማ የምግብ ዋጋ መናር የታዳጊው ዓለም አምራቾች የውጭ ንግድ ተሳትፎ ዝቅተኛ ሆኖ እንዲቀጥል ነው ያደረገው። የዓለም ባንክ ዘገባ በምግብ ፍላጎት መጨመር፣ በኤነርጂ ዋጋ መናር፣ በመሬትና በውሃ እጥረት፣ እንዲሁም በአካባቢ አየር ለውጥ የተነሣ ዓለምአቀፉ የምግብ አቅርቦት አደጋ ላይ እንደሆነም አመልክቷል። ለነገሩ የእርሻ ልማት ጠቀሜታ ለሁሉም እንጂ ለገጠር አካባቢዎች ብቻ አይደለም። ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል 65 በመቶው የሥራ ሃይል የተሰማራው በዚሁ መስክ ሲሆን ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት የ 32 በመቶውም ምንጭ ነው። የአፍሪቃን የእርሻ ልማት መልሶ ማነቃቃቱ በዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ዘንድ ቀደምት ትኩረት ማግኘቱ እንግዲህ ተገቢነት ይኖረዋል።

ይሁንና በሌላ በኩል ለታዳጊው ዓለም የዕርሻ ልማትና አጠቃላይ ዕድገት መጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊ የንግድ ግንኙነት መስፈኑ፣ የበለጸጉት መንግሥታት የገበያ መሰናክላቸውን ማንሣታቸውና ድሆች በሚባሉት አገሮችም የማሕበራዊ ፍትህ ዕውንነት ይበልጥ ወሣኝነት አለው። የዓለም ባንክ በአብዛኛው ገንዘቡን የሚያቀርቡት የበለጸጉ መንግሥታት ተጽዕኖ የሰፈነበት ተቋም ነው። የብዙሃን ድምጻቸው በተቋሙ ዕርምጃዎች ላይ ወሣኝነት አለው። ስለዚህም በዓለም ንግድ ጭምር ሚናችው ሃያል የሆነው እነዚህ መንግሥታት ለፍትሃዊ የኤኮኖሚ ግንኙነት ቀና እስካልሆኑ ድረስ የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት ውጥን በሂደቱ ከንቱ ሆኖ ሊቀር የሚችል ነው።