1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድሆች አገሮችና ዕድገታቸው፤

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2005

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ-ህዝብ ጠበብት ጥናታዊ ትንበያ እንደሚጠቁመው ከሆነ ፣ ምድራችን፣ እ ጎ አ እስከ 2100 ዓ መተ ምኅረት፤ 11 ቢሊዮን ያህል ዜጎችን ማስተናገድ ግድ ሳይሆንባት አይቀርም። አሁን የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን ነው።

https://p.dw.com/p/19OHW
ምስል picture-alliance/PhotoPQR/LeParisien

ወደፊት ፣ የህዝቡ ቁጥር እጅግ የሚንረው ደግሞ እጅግ በደኸዩት አገሮች ነው። ይህ በፊናው ፣ ከዕድገት ጋር ባለመመጣጠን ብርቱ ሳንክ ነው የሚፈጥረው። የህዝብ ቁጥር አለቅጥ ከፍ የሚለው ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ነው።

Bildergalerie Grün in Afrika
ምስል picture-alliance/Photoshot

የተባበሩት መንግሥታት የህዝብ መመጠኛ ልዩ ድጎማ በመጀመሪያ እንደተነበየው ሳይሆን፤ በአንዳንድ አገሮች ልጅ የመውለዱ ፍላጎት ፣ ከፍ አለ እንጂ አልቀነሰም። የጀርመን የሥነ ህዝብ ድርጅት ቃል አቀባይና የፖለቲካ ምሁር   ዑተ ሽታልማይስተር እንደሚሉት፤ ስለ ቤተሰብ መምሪያ ፣ ስለ ከላኤ-ፅንስና ስለመሳሰለው ማብራሪያ ተስፋ የተደረገውን ያህል ለህዝብ አልቀረበም።

«መጥፎ ሁኔታ ሊያጋጥም የቻለው፤ የቤተሰብ መምሪያ አገልግሎት ለማግኘት፤ ስለ ከላዔ ፅንስም ማብራሪያ የሚሰጥበት ሁኔታ ፤ ተስፋ የተጣለበትን ያህል አለመስፋፋቱ ነው።»

በያመቱ፣ የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ በአዳጊ አገሮች 80 ሚሊዮን ያህል ሴቶች፤ ሳይፈልጉ ነው የሚያረግዙት። ምክንያት ፣ የቤተሰብ መምሪያ ትምህርትና ከላኤ ጽንስ አለማግኘት ነው። ታዲያ በረጅም ጊዜ ሂደት፤ ብርቱ መዘዝ ይኖረዋል። ቁጥጥር በማይደረግበት የህዝብ አኀዝ ጭማሪ፣ ለምሳሌ ያህል፣ እ ጎ አ በ 2100 ዓ ም፤ የዓለም ህዝብ ቁጥር 28,6 ቢሊዮን ደረስ ሊያሻቅብ እንደሚችል ነው የሚተነበየው።

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ- ህዝብ የልዩ በጀት ጉዳይ መ/ቤት የአሁኑን ዘገባ መንስዔ አድርጎ እንደሚለው ከሆነ የህዝብ  ቁጥር የሚንረው ፣ አሁምንም ቢሆን ዜጎቻቸውን  መመገብ ባልቻሉ አገሮች ነው።  በዓለም ዙሪያ ጥሬ ሀብቶች፤ ውሃ፤ የኃይል ምንጭ ፣ እንዲሁም የምግብ ዓይነቶች ይመናመናሉ ዋጋቸውም እጅጉን ውድ ይሆናል። የአካባቢ ውድመትም ይስፋፋል። ዶቸ ቨለ ያነጋገራቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት  የልማት መርኀ-ግብር፣ ዋና ስራ አስኪያጅ ፣ ሔለን ክላርክ፤ የሠለጠነ የሰው ጉልበት አኀዝ እንዲጨምር ካልተደረገ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ተገንዝቦ ፤ ከዚሁ አኳያ ጥረት ካልተደረገ የማኅበራዊ ኑሮን ለማሳደግ፤ ተፈጥሮን በጠበቀ መልኩ የኤኮኖሚ ዕድገት መዋቅርን የሚያሻሽል ፣ ጥሩ አመራር ያለውና ሰላምን የሚያስፍን መንግሥት ከሌለ  አደጋ ነው የሚታያቸው።

« በሚመጡት 12/13 ዓመታት ፣ የድህነትን መልክዓ -ምድር፣ በተወሰኑ ቦታዎች ጎልቶ እናየዋለን። ይህም ውዝግብ፤ የተስፋፋ የትጥቅ ፍልሚያ እንዲሁም ከፍተኛ  የጥፋት አደጋ በሚያንዣብበትና መንሠራራት በሚያዳግትበት ፤ ደካማ አስተዳደርና የሚንገዳገድ መንግሥት ባለበት አገር ነው። »

Addis Abeba
ምስል derejeb/Fotolia

የሠለጠነ የሰው ጉልበት የማፍራቱ ተግባር በቀጣይነት መከናወን የሚገባው ጉዳይ ነው። የተፈጥሮ አካባቢ እንዲጠበቅም ተገቢው ክብካቤ ሊደረግ ይገባል። ፍትኀዊ የማኅበራዊ ኑሮ ዕድገትና የኤኮኖሚ ልማት መተሣሠር ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይቻል  ነገር አይደለም። ብዙ ህዝብ ያላት ድሃይቱ ሀገር ኢትዮጵያ እንኳ እ ጎ አ እስከ 2025 ዜጎቿ መካከለኛ ገቢ ያላቸው እንዲሆኑ የማደረግ ዓላማ አላት።

አሁንም ሔለን ክላርክ---

«በዓለም ውስጥ እጅግ ከደኸዩት ሃገራት አንዷ ፣ ለማንሠራራት የሠለጠነ የሰው ጉልበት የመጨመር ስልት ከነደፈችና ለተፈጥሮ አካባቢ በሚበጅ ሁኔታ ልታውለው ካሰበች፤ ሌሎች በዛ ያሉ አገሮችም፣ እንደ ኢትዮጵያ ፣  የማይጨበጥ ቢመስልም እንኳ፤ ተመሳሳይ ተስፋ መሠነቃቸውን ልናይ እንችላለን። »

ይሁን እንጂ በሚመጡት ዐሠርተ -ዓመታት ሴቶችና ልጃገረዶች፣ በትምህርትና ማሠልጠኛ እንዲገፉ በዛ ያለ ውች መመደብ ይኖርበታል ሲሉ ነው ሔለን ክላርክ የሚያስገዝቡት።

ሴቶችንና ልጃገረዶችን ያላሳተፈ ሀገር ፤ በአቅም ግንባታ ቢዳከም የሚያስገርም አይሆንም። የዓለም ሥነ ህዝብ፤ የጀርመን ድርጅት  ባልደረባ ፣ ዑተ ሽታል ማይስተርም፣ ዋናው የዕድገት ቁልፍ ትምህርት መሆኑን ነው የገለጡት። «ነብር መንግሥታት » በመባል የታወቁት የደቡብ ምሥራቅ እስያ መንግሥታት፣ በትክክለኛው ጊዜ በትምህርትና ሥራ ላይ  ገንዘብ ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ ነው፤ አስደማሚ ውጤት ማስመዘገብ የቻሉት። አፍሪቃውያን ፣ የሚበጅ መርኅ ተከትለው በዚህ  ረገድ ጠንክረው ከሠሩ፣ እመርታቸው ፣ የነብር ሳይሆን የአንበሳ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል።  ቤተሰብን መመጠን የሚያስችለውም  ትምህርት ነው። ታዲያ እ ጎ አ በ 2100 የተሳካ የምድራችን ስዕል ሊታይ የሚችለው ምን ቢደረግ እንደሆነ ፤ ዑተ ሽታልማየር  ሲያመላክቱ--

«ድህነት የሌለባት ዓለም፤ ረሃብ ፤ አደጋ  የማይከሠትባት ፣ መቼና ፣ ምን ያህል ልጆች ለማግኘት ቤተ-ሰብ መወሰን የሚችልባት ዓለም  ብትሆን ያምራል።»

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ