1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርቅ በደቡባዊ አፍሪቃ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 7 2008

ኤልኒኞ በተባለው የአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት በድርቅ ተመተዋል። በኢትዮጵያ ከየካቲት እስከ ሚያዝያ መጣል የነበረበት ዝናብ አጥጋቢ ባለመሆኑ ድርቁን ይበልጥ አባብሶታል ።

https://p.dw.com/p/1IVKV
Simbabwe Dürre
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi

[No title]


ድርቁ ከባድ ጉዳት ካስከተለባቸው የደቡብ አፍሪቃዎቹ ሃገራት መካከል ማላዊና ዚምባብዌ ግንባር ቀደሞቹ ሲሆኑ ሞዛምቢክ ሌሶቶና ዛምቢያም የምግብ እጥረት ችግር ገጥሟቸዋል። ደቡብ አፍሪቃም ድርቅ ካጠቃቸው ሃገራት መካከል አንዷናት። ድርቁ የከፋባት ማላዊ ትናንት «የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ አዋጅ» ደንግጋለች።


የማላዊ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ በተራዘመው የ2015/2016 ድርቅ ምክንያት ትናንት «የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ አዋጅ»መደንገጋቸውን አስታውቀዋል። ከሦስት ወራት አንስቶ የመብት ተሟጋቾችና ማሊያውያን መንግሥት የአደጋ ጊዜ አዋጅ እንዲያወጣ ቢወተውቱም ሙታሪካ እና ካቢኔያቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ነበር የከረሙት። ሙታሪካ ትናንት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተመድ መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የግሉ ዘርፍም ለችግሩ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ጊዜ የማላዊ የበቆሎ ፍጆታ 3.2 ሜትሪክ ቶን ይገመታል። በድርቁ ምክንያት ግን 1.072 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በቆሎ ይጎድላል። ፕሬዝዳንት ሙታሪካ እንደተናገሩት የ2015/2016 የተለመደው የዝናብ ወቅት ላይ ኤልኒኞ ከባድ ተጽእኖ አሳድሯል። በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አልጣለም። በማላዊ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት መረጃ መሠረት ካለፈው ጥቅምት እስከ መጋቢት ድረስ በተለይ በሀገሪቱ ደቡብና ማዕከላዊ ክፍሎች የጣለው ዝናብ ከሚፈለገው ያነሰ ነው። ድርቅ ካጠቃቸው አብዛኛዎቹ በ2015 ጎርፍ ጉዳት ያደረሰባቸው ቀበሌዎች ናቸው። በማላዊው ድርቅ ምክንያት የበቆሎ ምርት መጠን በመቀነሱ በቀሪው 2016 እና በመጪው 2017 የምግብ እርዳታ ፈላጊው ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። 2.8 ሚሊዮን ማልያውያን አሳሳቢ የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል። ህዝቡ ይህን ችግር ለማስወገድና ከጥገኝነትም ለመላቀቅ መንግሥት የአሰራር ለውጥ እንዲያደርግ እየጠየቀ ነው። ዶቼ ቬለ ካነጋገራቸው አንዱ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
«የማላዊ ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ ሊሰጠው ይገባል። በማላዊ በአስተማማኝ ሁኔታ እህል ማከማች ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ መንግሥት የሚቀበለው የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ እንፈልጋለን። አንደኛው የመጪው ዓመት በጀት ለንግድ የሚሆን ትላልቅ እርሻ በማስፋፋት ላይ እንዲያተኩር እንፈልጋለን። የድጎማ መርሃ ግብር ቀርቶ ለንግድ በሚካሄድ እርሻ ምግብ እንዲመረት መደረግ አለበት። ምክንያቱም በማላዊ የድጎማ መርሃ ግብር ውጤት አላመጣም። ህዝቡን ከረሃብ ያላላቀቀ መርሃ ግብር ይዘን መቀጠል የለብንም ።»
ሌላው አስተያየት ሰጭ ደግሞ ሀገሪቱ በምግብ ምርት ራሷን የምትችልበት መንገድ ላይ እንዲተኮር አሳስበዋል።
«የምግብ ምርት ጉዳይ ከግብርና ሚኒስቴር ዋነኛ ተግባራት አንዱ ነው። ሀገሪቱ በቂ ምግብ እንድኖራት ማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማጥናትና መፈለግ ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ከሰዎች ምግብ የምንለምንበት ሁኔታ ውስጥ መግባት አንፈልግም። »
ከየካቲት እስከ መጋቢት የተገኘው የበቆሎ ምርት 2.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው። ይህም በ2014/2015 ከተገኘው 2.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የበቆሎ ምርት ጋር ሲነፃጸር በ12.4 በመቶ ያንሳል። ሙታሪካ እንደሚሉት መንግሥታዊው ሰብል ሻጭና ገዥው «የማላዊ የእርሻ ልማት እና የገበያ ኮርፖሪሽን» በ2016/2017 የበቆሎ ዋጋን ለማረጋጋት ለህዝቡ የሚሸጠው 250 ሺህ ሜትሪክ ቶን በቆሎ ያስፈልገዋል። በማላዊ ድርቁ ያስከተላቸውን ችግሮች ለመፍታት፣ የመጠባበቂያ እህል ክምችት፣ ዋጋ ማረጋጋት እንዲሁም በቂ የእርዳታ እህል ያስፈልጋል። ፕሬዝዳንት ሙታሬካ ትናንት ባቀረቡት ጥሪ ሀገሪቱ ከገጠማት የምግብ ቀውስ እንድትላቀቅ 1.2 ሜትሪክ ቶን በቆሎ ያስፈልጋታል ብለዋል።
የዓለም የምግብ መርሃ ግብር እንዳስታወቀው በአሁኑ ጊዜ ማላዊ በድርቁ ክፉኛ ለተጎዱ ከ23 እስከ 28 በሚደርሱ ቀበሌዎች ውስጥ ወደ 3 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ድጋፍ እየሰጠ ነው። የድርጅቱ የደቡባዊ አፍሪቃ ቃል አቀባይ ድርቁ ወደፊት ይባባሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሁኔታዎች እስከሚሻሻሉም ጊዜ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል። በሌላ በኩል ለሞዛምቢኩ ድርቅ እርዳታ የሚውል የ200 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ጥሪ ቢቀርብም ከተመ እና ከእርዳታ ድርጅቶች የተገኘው 15 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከአማጽያን ጋር እንደገና በቀጠለው ውጊያ ምክንያት የእርዳታ አቅርቦቱ ችግር ገጥሞታል። በዚምባብዌም ከገጠሩ ህዝብ ከአንድ አራተኛ በላይ በቂ ምግብ አያገኝም። በአሁኑ ጊዜ WFP 730 ሺህ ለሚሆኑ ዚምባብዌያውያን እርዳታ እየሰጠ ነው። ከዚህ ቀደም ለጎረቤት ሃገራት ምግብ ትሸጥ የነበረችው ደቡብ አፍሪቃ ባለፈው ዓመት ሰብል ባለመያዙ ምክንያት በቆሎ ከውጭ ልታስገባ ነው። በ2015 ደቡብ አፍሪቃን የመታው ድርቅ ሀገሪቱ በመቶ ዓመት ታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ነው ተብሏል።

Simbabwe Dürre Mais Landwirtschaft
ምስል AFP/Getty Images
Peter Mutharika wird neuer Präsident von Malawi 31.05.2014
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe
Simbabwe Dürre Maisfeld
ምስል picture alliance/Photoshot

ሊሎንግዌ ጆርጅ / ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ