1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ግብርና ሚኒስቴር “ድሮኖችን” መጠቀም ጀምሯል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 2011

በኢትዮጵያ በመዝናኛ እና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ አገልግሎታቸው እየጎላ የመጣው ሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንግስት ተቋማትን ቀልብ መግዛት ይዘዋል። ተቋማቱ ድሮኖችን ለነዳጅ ቱቦ ጥበቃ እና ክትትል፣ ለማዕድን ፍለጋ እና ለግብርና መረጃ አሰባሰብ ለመጠቀም እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/3Aw2G
Rwanda Drone Pictures
ምስል DW/G. Kowene

ግብርና ሚኒስቴር “ድሮኖችን” መጠቀም ጀምሯል

ስለ ሰው አልባ ተንቀሳቃሽ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ሲነሳ ለብዙዎች ቀድመው ፊታቸው ድቅን የሚሉት ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡቱ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ መጠን እና አይነታቸው፤ አገልግሎታቸው እና የሚሳተፉበትም ዘርፍ እየበዛ መጥቷል። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪዲዮ፣ ፊልም እና የሰርግ መሰል ማህበራዊ ክንውኖችን ለመቅረጽ ድሮኖችን መጠቀም እየተዘወተረ ነው። በሌሎች ሀገራት ድሮኖች ከወታደራዊ እና መዝናኛ አገልግሎቶች ባሻገር በኮንስትራክሽን፣ ማዕድን ፍለጋ፣ ኢንሹራንስ እና ሪል ስቴት ዘርፎች የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማትም የሌላውን ዓለም ፈለግ እየተከተሉ ያሉ ይመስላሉ።   

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መድኃኒቶችን፣ ደም እና የህክምና ቁሳቁሶችን በቀላሉ ወደማይደረስባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች በድሮን የማጓጓዝ ውጥኑን ወደ ተግባራዊ ሙከራ አሸጋግሯል። ድሮኖቹ ለታለመላቸው አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ከጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ጋር በትብብር እየሰራ ያለው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቅርቡ ከሌላ መንግስታዊ ተቋም ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ፈጽሟል።መስሪያ ቤቱ ከማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት ድሮኖች በነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ጥበቃ እና ክትትል ላይ እንዲሰማሩ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል። ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪም ድሮኖችን ለማዕድን ፍለጋ ለመጠቀም የሚያስችል እንደሆነ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፕሬስ እና ሚዲያ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ አዲስ መኮንን ያስረዳሉ። 

Asaph Kasujja - Videopgraher arbeitet mit Drohnen
ምስል J. van Loon

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለእነዚህ ተግባራት የሚውሉ ድሮኖችን ያቀርባል። ለነዳጅ ማስተላለፊያዎች ቁጥጥር ማዕከል የሚውል ስርዓት ይዘረጋል፣ ባለሙያዎችንም ያሰለጥናል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድሮኖችን ያቀርባል ሲባል ራሱ አምርቶ ለአገልግሎት ያበቃል ማለት እንዳልሆነ አቶ አዲስ ይገልጻሉ። ይልቁንም በመስሪያ ቤቱ በሚደገፉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የድሮኖችን ዲዛይን በሀገር ውስጥ በማሰራት በውጭ ሀገር ተመርተው እንዲገቡ የማድረግ አካሄድ እንደሚከተሉ ይናገራሉ።  

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለጊዜው የድሮኖችን ዲዛይን በማስተባበር ላይ ቢያተኩርም ወደፊት የድሮን ፍላጎት በሀገርም ውስጥም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ እየጨመረ ከመጣ “የድሮን ፋብሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የማቋቋም ሀሳብ አለ” ይላሉ አቶ አዲስ። መስሪያ ቤታቸው በድሮኖች አማካኝነት የማዕድን ፍለጋ አይነት መረጃዎች ከመሰብሰብ ባሻገር የተሰበሰቡትን በርካታ መረጃዎች በአግባቡ ለመተንተን የሚያስችል ማዕከል እየገነባ እንደሚገኝም ጨምረው ያብራራሉ። 

Afrika Drohnen
ምስል picture-alliance/AP Photo/D. Farrell

መረጃዎችን በድሮን ሰብስቦ በመተንተን ለሚፈለገው ጠቀሜታ የማዋል አካሄድ ወደ ግብርናው ዘርፍም ተሻግሯል። የግብርና ሚኒስቴር አርሶ አደሮች በተለያዩ ቦታዎች ያሏቸውን መሬቶች በመለየት ሰርትፍኬት ለመስጠት ድሮኖችን መጠቀም ጀምሯል። በሚኒስቴሩ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት የካዳስትራል ሰርቬይ ባለሙያ ምዕራፍ ሀብተወልድ ስለሚሰበሰበው መረጃ ምንነት እና ጠቀሜታ ማብራሪያ አላቸው።

ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም እነዚህን መረጃዎች ይሰበስብ የነበረው በአውሮፕላን አማካኝነት ከአየር ላይ በሚነሱ ፎቶዎች እና የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ነበር። መስሪያ ቤቱ ድሮኖችን ለመጠቀም የወሰነበትን ምክንያት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

የግብርና ሚኒስቴር አሁን ለሙከራ እየተገለገለበት የሚገኘውን፣ ንፋስን የሚቋቋም ተለቅ ያለ ድሮን ከነሶፍትዌሩ ለመግዛት እና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን 1.7 ሚሊዮን ብር እንዳወጣ ባለሙያዋ ይናገራሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለእንደዚህ አይነት መረጃ የማሰባሰብ ስራ ከሶማሌ እና አፋር ክልል ውጭ ላሉት ሁሉም ክልሎች ወደፊት አንዳንድ ድሮን የመመደብ እቅድ እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል። ባለሙያዋ እንደ ድሮን አይነት መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳይላኩ አስተዋጽኦ አላቸው ይላሉ። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 


ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ