1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድንገተኛ ዝናብና ጎርፍ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5 2008

በአፋር፤ሶማሌ እና አማራ ክልል የተፈጠረው ጎርፍ በሰው እና በእንስሳት ላይ ጉዳት አድርሷል። የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጥል በድረ-ገጹ ያሰፈረው ትንበያ ይጠቁማል።

https://p.dw.com/p/1IUlx
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

[No title]

ኤል-ኒኞ በተሰኘው የአየር ጠባይ ምክንያት በድርቅ ከፍተኛ ጫና ያረፈባት ኢትዮጵያ ሰሞኑን ድንገተኛ ዝናብ እና ጎርፍ እያስተናገደች ትገኛለች። በዶቼ ቬለ የዋትስ አፕ መስመራችን ከተላኩልን መልዕክቶች መካከል ሚያዝያ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. «ማታ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በአፋር ክልል ዳሊፋጌ ወረዳ ጃራ ቀበሌ ያሉ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል» የአፋር ክልሉ አድማጭ «በተለይ ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳቱ ከበድ ይላል። የአራት መምህራን ቤት ደግሞ በጎርፍ ተወስዷል። ጉዳዩን ብናሳውቅም አንድም አካል የደረሰልን የለም።» ሲሉ አክለዋል።

በጉዳዩ ላይ በዶይቼ ቬለ የፌስቡክ ማህበራዊ ገጽ አስተያየት ከጠየቅናቸው ሰዎች መካከል መልከ ፄዴቅ መካሻ የተባሉ ግለሰብ « በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ጎርፍ ብዙ ሰዎችን ከቤት እያፈናቀለና ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ግን አልታወቀም።» ሲሉ ጽፈዋል።
መጋቢት 23 ቀን 2008 ድንገተኛው ጎርፍ እና ዝናብ ደ/ወሎ ደላንታ ወረዳ በእንስሳት ሃብት ላይ ጉዳት አድርሷል። ድንገተኛው ዝናብ የፈጠረው ጎርፍም በዓለም አቀፉ የገጠር መንገድ ግንባታ መርሃግብር በሚሠሩ ድልድዮች እና መንገዶች ላይ ጉዳት ማድረሱን አቶ በድሩ ሰዒድ ይናገራሉ።

ከሳምንት በፊት በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ የጣለው ድንገተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከ23 በላይ ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በድረ-ገጹ በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከተሞች ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል። ባለፈዉ ሳምንትም ኤጀንሲዉ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል እና በየአካባቢዉ ከወዲሁ የጥንቃቄ ርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስቧል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ