1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪቃውያን እይታ

ቅዳሜ፣ ጥር 12 2010

ልክ ዛሬ ከአንድ ዓመት በፊት የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት በመሆን ቃለ መሀላ የፈጸሙት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪቃ ብዙ ወዳጆች አላፈሩም። የአህጉሩ ነዋሪዎች ትራምፕ ከጥቂት ቀናት በፊት ስደትን አስመልክተው ስለ አፍሪቃ በሰነዘሩት ጸያፍ አስተያየት እጅግ ተቆጥተዋል። ግን ሁሉም አይደሉም ስለ ትራምፕ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው።

https://p.dw.com/p/2rAuN
USA Donald Trump spricht vor afrikanischen Staatschefs
ምስል Getty Images/AFP/B. Smialowski

ዶናልድ ትራምፕ

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በብዙ የአፍሪቃ ሀገራት መነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል። አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ወደ ዮኤስ የሚገቡ የውጭ ዜጎችን በሚመለከተው ረቂቅ ሕግ ላይ በዋይት ሀውስ ቤተ መንግሥት ከአንዳንድ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደራሴዎች ጋር በተደረገ ምክክር ላይ የአፍሪቃ እና ሐይቲ መጤዎቹን በማንቋሸሽ የተጠቀሙበት ወይም ተጠቀሙበት የተባለው  ጸያፍ አነጋገር በአፍሪቃ ብዙዎችን አስቆጥቷል። ትራምፕ ቆሻሻ ቦታን ለመግለጽ የሚውለውን ጸያፍ ቃል መጠቀማቸው በአህጉሩ ስለሳቸው ያለውን አሉታዊ አመለካከት አጠናክሮዋል ፣ ብዙዎችም ትራምፕን ዘረኛ ብለዋቸዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ዓመት በፊት ስልጣን በያዙ ሰሞን ብዙዎች ፣ በተለይ የሙስሊም ሀገራት ተወላጆች  ዩኤስ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግድ ሕግ የፈረሙበት ርምጃቸው በአፍሪቃ ብርቱ ቁጣ መቀስቀሱ አይዘነጋም። እገዳው ካረፈባቸው ሀገራት መካከል ከአፍሪቃ ሱዳን፣ ሶማልያ እና ሊቢያ ይገኙባቸዋል።
ይህን ተከትሎ ብዙ አፍሪቃውያን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዶናልድ ትራምፕ አኳያ ቁጣቸውን ቢገልጹም፣ ድጋፋቸውን የሰጡ ጥቂቶች አይደሉም። በፌስቡክ አስተያየታቸውን ያስቀመጡት የአንጎላ ዜጋ ቢስፖ ኢኖሴንስዮ ትራምፕን በዩኤስ አሜሪካ ታሪክ ውስጥ የታዩ በጣም መጥፎ እና ስነ ልቡናዊ ችግር ያለባቸው መሪ ናቸው ብለው፣ አሜሪካውያን ወደፊት ፕሬዚደንታቸውን በጥንቃቄ እንዲመርጡ አሳስቧል። በኢኖሴንስዮ አንጻር ኢቤርት ጋርሲያ እስካሁን ትራምፕ ለሀቅ መቆማቸውን ያሳዩ እና የከፉ አፍሪቃውያን ፕሬዚደንቶችን ያጋላጡ መሪ ናቸው ብለዋል። እስማየል ቶጎላኒ ደግሞ ትራምፕ ፣ ድክመቶች ቢኖሯቸውም ፣ ዩኤስ አሜሪካን እንደገና ታልቅ እንዳደረጉ በመግለጽ፣ መከባበር እንዲኖር ከተፈለገ ዓለም እንደ እርሳቸው ዓይነት መሪ ያስፈልጋታል ብለዋል። ይሁን እንጂ፣ ብዙው ስለ ዶናልድ ትራምፕ በብዛት የሚሰነዘረው አስተያየት  አሁንም አሉታዊ ነው። የማሊው ዜጋ ሴኩ ሳማኬ የማያስተማምኑ መሪ ሲሏቸው፣  ዩኤስ አሜሪካ ብቻ ሳይሆን አፍሪቃን ጨምሮ መላው ዓለም የሚኮራበት ስራ ሰርተዋል ከሚሏቸው የቀድሞው አሜሪካዊ መሪ ባራክ ኦባማ ጋር ያነጻጸሩት ኬንያዊው ምጋንጋ ምዋናሚቼዞ ደግሞ ትራምፕ ለዩኤስ አሜሪካ ጠላት ከማፍራት ያለፈ ይህ ነው የሚባል ጠቃሚ ስራ  እንደልሰሩ ተናግረዋል። 
ዶናልድ ትራምፕ ካሰሙት ወደ ዮኤስ የሚገቡ የውጭ ዜጎችን በሚመለከተው ሕግ ላይ በተደረገ ምክክር ላይ የአፍሪቃ እና ሐይቲ መጤዎቹን በማንቋሸሽ የተጠቀሙበትን እና ጸያፍ እና አክብሮት የጎደለውን አነጋገር ገዢው የደቡብ አፍሪቃ ፓርቲ፣ የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ እጅግ የሚያስቆጣ ብሎ ተችቶታል። የቦትስዋና መንግሥት ደግሞ አስተያየቱን ኃላፊነት የጎደለው እና ዘረኛ ብሎታል። የትራምፕ አስተያየት ያስቆጣቸው ብዙ አፍሪቃውያት ሀገራትም በመዲናዎቻቸው የሚገኙትን የዩኤስ አሜሪካ አምባሳደሮችን ወደ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጠርተዋል። የአፍሪቃ ህብረት ቃል አቀባይ ኤባ ካሎንዶ እንዳሉት፣ የትራምፕ አስተያየት  ህብረቱን ያሳሰበው ሲሆን፣ በተለይ ብዙ አፍሪቃውያን ወደ ዩኤስ አሜሪካ በባርነት የተወሰዱበት ታሪካዊ ሀቅ ሲታሰብ፣ አነጋገራቸው በየትኛውም ባህሪ እና ልማድ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው።  
በደቡብ አፍሪቃ የዘሮች ግንኙነት ጥናት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ፍራንስ ክሮንየ  ግን  ብዙ አፍሪቃውያን ከሚሉት የተለየ አመለካከት ነው ያላቸው።
« ትራምፕ የተጠቀሙበት አነጋገር መልካም አስተዳደር በጣም በጎደላቸውአፍሪቃውያት ሀገራት አኳያ የተሳሳተ አይደለም። እነዚህ መንግሥታት የሰብዓዊ መብትን የሚጥሱበት እና አገሮቻቸውን እንደደኸዩ የሚያስቀሩ ኤኮኖሚያዊ ወሳኔዎችን የሚወስዱበት ርምጃቸው ነው ሀገራቱን ጥቂቶቹ ትራምፕን የሚተቹ ግለሰቦች፣  ጋዜጠኞች እና ቅር የተሰኙ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የመብት ተሟጋቾች ጭምር ሊኖሩባቸው የማይፈልጉ ቦታዎች ያደረጓቸው። »
የትራምፕ አስተዳደር በአፍሪቃ አኳያ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል ብለው እንደማያስቡ  ፍራንስ ክሮንየ ገልጸዋል። እንደ ክሮንየ አስተያየት፣ አፍሪቃ እንኳንስ ለዋይት ሀውስ ቤተ መንግሥት ይቅርና፣ በአሜሪካውያኑ ፖለቲከኞች እና ዲፕሎማቶችም ዘንድ ቢሆን ያን ያህል ትኩረት ያላገኘች አህጉር በመሆኗ፣ የተለያዩት የዩኤስ አሜሪካ አስተዳደሮች በአፍሪቃ አኳያ የተከተሉትን መርህ ማነጻጸር ትክክል እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
« ለአፍሪቃ ከጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ይልቅ የኦባማ የተሻለ ነበር የሚል አስተያየት ይሰማ ነበር። ይሁንና፣  ይህን አባባል የሚደግፍ የጎላ የንግድ፣ የርዳታ አሰጣጥ ወይም ዲፕሎማቲክ መርህ የለም። በብዙ አፍሪቃውያንም ዘንድ የተስፋፋው አስተያየት፣ ትራምፕ በሚመሩት መንግሥትም ስር አፍሪቃ ንዑሱን ጥቅም ብቻ ነው ያገኘችው የሚል ነው። »

Präsident George Bush Laura Bush in Arusha, Tansania
ምስል AP
Versammlung der Afrikanischen Union - 30 teilnehmende afrikanische Nationen
ምስል Getty Images/AFP/M. Turkia
Afrika Somalia Proteste, Demonstation
ምስል picture alliance/AP Photo/F.A. Warsameh

በደቡብ አፍሪቃ ጆሀንስበርግ ከተማ የሚገኘው የአፍሪቃውያን ጋዜጠኞች ማዕከል የተባለው የጋዜጠኞች መረብ ዋና አዘጋጅ የሆነው የዚምባብዌው ተወላጅ፣ ጋዜጠኛ ሴቪየስ ክዊኒካ ግን ትራምፕ በአንድ ዓመት የስልጣን ዘመናቸው በአፍሪቃ ላይ አሳሳቢ ተፅዕኖ እንዳሳረፉ ነው የተሰማው። አፍሪቃ  ያን አምባገነኖች ከትራምፕ አስተዳደር ርምጃ እንደማያሰጋቸው ፣ እንዲያውም፣ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብም ነው ያለው። 
« አፍሪቃ ትራምፕን ሁሌ የሚደነፉ እና በሚገባ ሳያስቡ አስተያየት የሚሰጡ አድርጋ ትመለከታለች። ዩኤስ አሜሪካን ከመሰለ አንድ ኃያል መንግሥት የሚሰሙ ትራምፕ የሚሰነዝሯቸውን ዓይነቶች አስተያየት አምባገነኖችን በሀገሮቻቸው የሰብዓዊ መብት የሚጥሱበትን አሰራራቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታታል። የሕግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብትን በማክበር ቀዳሚውን ቦታ የያዘችው ዩኤስ አሜሪካ አሁን በዓለም ጥላቻን መስበክ እና በየአጋጣሚውም ዓለምን በመከፋፈል ላይ ትገኛለች። »    
በትራምፕ አስተያየት ቅር የተሰኙት የአፍሪቃውያን ጋዜጠኞች ማዕከል ባልደረቦች በየቀኑ ስለሳቸው ዘገባ እንደሚያቀርቡ  ክዊኒካ  ገልጿል።
« ትራምፕ የሚሰነዝሩት አስተያየት በዓለም  ብዙ ክርክር ነው የሚያስነሳው። በተለይ ከጥቂት ቀናት በፊት በአፍሪቃ አኳያ የሰነዘሩት ጸያፍ አነጋገር ትልቅ ቁጣ አፈራርቋል። በአሜሪካ ከብብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሀገሪቱን በመገንባቱ ስራ ለብዝበዛ ለተዳረጉት አፍሪቃውያን አንድም ክብር የላቸውም። »
እንደ ክዊኒካ አስተያየት፣ አከራካሪው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከርሳቸው በፊት ሀገሪቱን በመሩት ርዕሳነ ብሔር አንጻር፣ ከአፍሪቃ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ደንታ የላቸውም። 
« ትራምፕ ከአፍሪቃ ጋራ ያላቸው ግንኙነት በጋራ መተማመን እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አይደለም። በወቅቱ እያየነው ያለው ግንኙነት የጌታ እና የባርያ ግንኙነት ነው። እንደሚታወቀው፣ የቀድሞ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንቶች ከአፍሪቃ ጋር ላለው ግንኙነት ትልቅ ቦታ ነበር የሰጡት። »  

አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺቪኮቭስኪ

ልደት አበበ