1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም ተመረጡ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 15 2009

የቀድሞው የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ (ዳይሬክተር ጄነራል) ሆነው ተመረጡ፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የተመረጡት በስዊትዘርላንድ ዤኔቭ እየተደረገ በሚገኘው የድርጅቱ ሰባኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2dStE
Tedros Adhanom Ghebreyesus ehem. Außenminister Äthiopien
ምስል DW/T. Woldeyes

ከብሪታንያዊው ተቀናቃኛቸው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ ከፍተኛ ፉክክር ገጥሟቸው የነበረው ዶ/ር ቴድሮስ በስብሰባው ላይ በተደረገ ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ተመርጠዋል፡፡ ምርጫው በሶስት ዙር የተካሄደ ሲሆን ከበርካታ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሰረት በመጀመሪያው ዙር ዶ/ር ቴድሮስ 95 ድምጽ ሲያገኙ ዶ/ር ናባሮ በ52 ተከትለዋል፡፡ ሶስተኛዋ ተወዳዳሪ ፓኪስታኒዊቷ ሳንያ ኒሽታር 38 ድምጽ ብቻ በማግኘታቸው በምርጫው ደንብ መሰረት በመጀመሪያው ዙር ተሰናብተዋል፡፡

በሁለተኛው ዙር ዶ/ር ቴድሮስ ቢመሩም ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ባለማግኘታቸው ምርጫው ወደ ሶስተኛ ዙር መሸጋገር ግድ ብሏል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በሶስተኛው ዙር ማሸነፋቸውን የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል። 

ዶ/ር ቴድሮስ ድሉን አስቀድመው የገመቱ ይመስላል፡፡ ትላንት ምሽት በይፋዊ ፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ “በመንገዳችን ሁሉ ሀገራችንን ከፍ እያደረግን እዚህ ደርሰናል፡፡ በድል በደመቀው የዲፕሎማሲ ታሪካችን ላይ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ከጫፍ ደርሰናል፡፡ መልዕክቴ ለድል እንዘጋጅ ነው” ሲሉ ጽፈው ነበር፡፡

ከድምጽ  አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ አስቀድሞ ለመጨረሻው ዙር ያለፉት ሶስቱ ተፎካካሪዎች የመጨረሻ ንግግራቸውን እንዲያቀርቡ ተጋብዘው ነበር፡፡ ቅድሚያ የተሰጣቸው ዶ/ር ቴድሮስ ከተመረጡ ሊያሳኳቸው ያቀዷቸውን አምስት አንኳር ጉዳዮችን አስተዋውቀዋል፡፡ “የዓለም የጤና ድርጅት አፍሪካዊ ዳይሬክተር ጄነራል ኖሮት ባያውቅም ማንም ሰው ከአፍሪካ በመሆኔ ምክንያት ብቻ እንዲመርጠኝ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ከባድ የጤና ከባቢ ካለባቸው ቦታዎች በአንዱ የሰራ እና የጤና ስርዓቱን የቀየረን መሪ መምረጥ በእርግጥም ዋጋ አለው፡፡ ያ መሪ ለየት ያለ አተያይ እና ዓለም ከዚህ በፊት ተመልከቶት የማያውቀውን አቅጣጫ ይዞ ይመጣል” ብለዋል በንግግራቸው፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ ለኃላፊነት ቦታው በመመረጣቸው የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን ለመምራት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ብሎም ኢትዮጵያዊ ይሆናሉ    

Tedros Adhanom Ghebreyesus ehem. Außenminister Äthiopien
ምስል DW/T. Woldeyes

ዶ/ር ቴድሮስ ለድርጅቱ ኃላፊነት እንደሚወዳደሩ በይፋ ያሳወቁት የዛሬ ዓመት በግንቦት ወር አጋማሽ ነበር፡፡ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት በ60 ሀገራት ግደማ ጉብኝት በማድረግ ድጋፍ ሲያሰባስቡ ቆይተዋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በጥር 2009 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ከህብረቱ አባል ሀገራት ይፋዊ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ ድጋፉን ተከትሎም እስከ ውድድሩ ማጠናቀቂያ  የአህጉሪቱ ወካይ ተወዳዳሪ ሆነው ቆይተዋል፡፡

የቀድሞው ሚኒስትር ለዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊነት ቦታ እንደሚወዳደሩ በይፋ ካሳወቁ አንስቶ በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ዘንድ የከረረ ድጋፍ እና ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ “ለኃላፊነት ቦታው ይመጥናሉ” የሚሉት ደጋፊዎቻቸው የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ  ሚኒስትር በነበሩ ወቅት ያመጧቸውን ለውጦች በማሳያነት በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪነትም የሀገር ውክልና እና ሀገራዊ ፍቅርን በምክንያትነት በመጥቀስ አንድ ኢትዮጵያዊ ለዓለም አቀፍ የኃላፊነት ደረጃ ሲወዳደር ድጋፍ እንደሚያሻው ሞግተዋል።

በተቃራኒው ወገን ባሉት ግን በዶ/ር ቴድሮስ የፖለቲካ ስልጣን ዘመን የደረሱ ጉዳቶች እና ጥፋቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የካቢኔ አባል በነበሩ ወቅት ለተፈጸሙ ግድያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ሌሎች ጥፋቶች “አባሪ ተባባሪ ናቸው” ሲሉ ይከሷቸዋል፡፡ ለዚህ ድርጊታቸው “በህግ ሊጠየቁ እንጂ ለዓለም አቀፍ የኃላፊነት ቦታ ሊታጩ አይገባም” የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ወቅት ከአንድም አራት ጊዜ በኢትዮጵያ ተከስተው የነበሩ “የኮሌራ ወረረሽኞችን ደብቀዋል” ሲሉም ይወነጅሏቸዋል፡፡

የተቃዋሚዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ክርክር በማህበራዊ መገናኛዎች የተገደበ ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ ሰልፎች ጭምርም የታገዘ ነበር፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መቀመጫ በሆነችው ስዊትዘርላንድ ዤኔቭ በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት የድጋፍ እና የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄደዋል፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ በሚመረጥበት የሰባኛው ስብሰባ መክፈቻ ላይም አቶ ዘላለም ተሰማ የተባሉ የፖለቲካ አቀንቃኝ ተቃውሟቸውን በከፍተኛ ድምጽ አሰምተዋል፡፡ ግለሰቡ ዶ/ር ቴድሮስ “ለቦታው እንደማይገቡ” እና መመረጣቸው “በሰብዓዊነት ላይ መቀለድ” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎች ከስብሰባ አዳራሽ እስኪያስወጧቸው ድረስም በተደጋጋሚ “አፍሪካ በድጋሚ አስቢ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ