1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመናዊቷ የስነ-ጽሁፍ ኖቤል ተሸላሚ

Azeb Tadesseእሑድ፣ ጥቅምት 1 2002

በያዝነዉ አመት በስዊድን ስቶኮልም የሚገኘዉ የኖቤል ሽልማት አካዳሚ የወቅቱ ታላቅ ጸሃፊ ሲል ጀርመናዊትዋን የስነ-ጽሁፍ ሰዉ የአመቱ ተሸላሚ እንዳደረጋት ይፋ አድጓል።

https://p.dw.com/p/K3vu
ደራሲ ሄርታ ሙለርምስል picture-alliance/dpa

በያዝነዉ 2009 የአዉሮጻዉያኑ አመት በስቶኮልም የሚገኘዉ የኖቤል ሽልማት ቢሮ የአመቱ የስነ-ጽሁፍ ኖቤል ሽልማቱን ትዉልደ ሮማንያዊት ለሆነችዉ ጀርመናዊት ደራሲ ሄርታ ሙለር እንደሚያበረክት ገልጾ፣ የአመቱ ታላቅ ጸሃፊ ሲልም ሰይሞአታል።
እ.አ 1987 አ.ም በስደት ወደ ጀርመን የመጣችዉ የ 56 አመትዋ የሮማንያ ተወላጅ ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኻላ በሮማንያ ዉስጥ በጣም ቁጥራቸዉ አነስተኛ ከነበሩት የጀርመን የዘር ሃረግ ከነበራቸዉ ማህበረሰቦች ቤተሰቦችዋ እንደመጡ ስትገልጽ ወላጅ እናትዋ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት በግዳጅ ስራ እንደሄዱ አባትዋም በሮማንያ የጦር ሰራዊት ዉስጥ ሹፊር እንደነበሩ ትገልጻለች። በሮማንያ ዪንቨርስቲ የጀርመንኛ እና የሮማንያ ቋንቋ ትምህርቷን ጠንቅቃ የተማረችዉ ደራሲ ሄርታ ሙለር በቀድሞዋ ሶሻሊስት ሮማንያ ለጥቂት ግዜያት ጀርመንኛ ቋንቋ በማስተርጎም እንዲሁም የጀርመንኛ ቋንቋን በማስተማር አገልግላለች።
ባለፈዉ ሃሙስ መስከረም 28/ 2002 አ.ም የስቶኮልሙ የኖቤል ሽልማት አካዳሚ የሮማንያ ተወላጅ የሆነችዋን ደራሲ የዘንድሮዉን የስነ-ጽሁፍ ሽልማት እንደሚሰጥ በገለጸ ግዜ የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የጀርመን ዜግነት ያላት የሮማንያ ተወላጅ ጀርመንን የከፈለዉ ግንብ በወደቀ በሃያ አመቱ ይህንን ታላቅ ሽልማት ማግኘቷ አንድ አስልደናቂ ምልክት ነዉ ብለዉታል። ደራሲ ሄርታ ሙለር ይህን ሽልማት ስላገኘች ብቻ የደራሲዋ ጀርመንኛ ቋንቋ ስነ-ጽሁፍ ስራዎች በአለም የስነ-ጽሁፍ መድረክ መቅረባቸዉ አስደሳች መሆኑን በማያያዝ ጠቁመዋል። ደራሲ ሄርታ ሙለር ስለ ስራዎችዋ «አስካሁን በሮማንያ ቋንቋ ምንም አይነት የድርሰት ስራዩን አላስቀመጥኩም፣ ግን የድርሰት ስራዎቼን በጀርመንኛ ቋንቋ ልጻፈዉ እንጂ ሃሳቡ፣ ህልሙ ሁሉ፣ የሮማንያዉን ምናቤን ይዤ ነዉ ብዕሪን ከወረቀት የማገናኘዉ»
የሄርታ ሙለር ለዚህ ሽልማት የበቃችዉ በግጥም ስራዎቿ መሆኑ ሲነገር በተለይ ለስደት ያበቃት ኒደሩንገን በተሰኘ በጀርመንኛ ያወጣችዉ የአጭር ልቦለድ ስብስብ ነዉ። የመብት እጦት የነበረባት የቀድሞዋ ሶሻሊስት ሮማንያን የማህበራዊ ህይወትን በመጻፍዋ በሮማንያም እንዳይታተም ታግዶባት ነበር። ባለፉት ጥቂት አመታት ዉስጥ በተለይ በምዕራብ አዉሮጻ የጀርመናዊቷ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በተለያዩ አገሮች ለአንባብያን ቀርበዋል። በተለይ በስዊድን ያሉት አድናቂዎችዋ ለደራሲዋ ስራዎች ያላቸዉን ፍቅር በከፍተኛ ሁኔታ ይገልጻሉ። ታዋቂዋ የስዊድን ደራሲ ኡልሪከ ሚልስ ስለ ጀርመናዊትዋ ጸሃፊ « በእዉነቱ እስካሁን ከአነበብኩዋቸዉ የድርሰት ስራዎች በሙሉ የስዋን የጹሁፍ ስራ በጣም ነዉ የማደንቀዉ። ግሩም የሆነች ጸሃፊ ናት፣ በድርሰት ስራዎችዋ የቃላት አጠቃቀምዋ ግልጽ እና በሚኮረኩር መልኩ ነዉ የምታስቀምጠዉ» እንደ አዉሮጻዉያኑ 1987 አ.ም ከጀርመናዊ ባለቤትዋ ጋር ወደ ጀርመን ለመኖር የተሰደደችዉ ደራሲ ሄርታ ሙለር በተለይ የእናት አገርን ማጣት ወይም የእናት አገር ናፍቆት በሚል የጻፈቻቸዉ የድርሰት ስራዎችዋ ታዋቂነትን አስገኝቶላታል።
ሌላዉ ከደራሲ ሄርታ ሙለር ስራዎች ዉስጥ እዚህ በጀርመን አገር ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያገኘዉ በጀርመንኛ Atemschaukel የተሰኘዉ የድርሰት ስራዋ ነገ እዚህ በጀርመን የጀርመን ያመቱ የድርሰት ስራ በተሰኘ ለሚሰጠዉ የሽልማት ስራ በእጩ ተወዳዳሪነት ቀርቦአል። Atemschaukel ማለት እስትንፋስ በተሰኘዉ የድርሰት ስራዋ አንድ ወጣት እንዴት ወደ ሩስያ በግዳጅ እንደተሰደደ በማሳየት የ 80.000 የጀርመን ሮማንያ ዜግነት ያላቸዉ ህዝቦች ከሁለኛዉ የአለም ጦርነት በኻላ የደረሰባቸዉን አሰቃቂ እጣ ፈንታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ።
የቀድሞዉ የሶሻሊስት ሮማንያ የጥበቃ ቢሮ ደራሲ ሄርታ ሙለር ወደ ጀርመን ተሰዳ መኖር ከጀመረችም ወዲህ ያለማቋረጥ ለጀርመን የብዙሃን መገናኛ በመጻፍ ስምዋን ለማጉደፍ ጥረት አድርጎ ነበር። ሄርታ ሙለር በምስራቁ አዉሮጻ የቀዝቃዛዉ ጦርነት አብቅቶ የጀርመኑ ግንብ ከፈረሰ ወዲህ እንደ አዉሮጻዉያኑ 1995 አ.ም ጀምሮ የጀርመን የደራስያን ማህበር አባል በመሆን እንደገና ወደ ትዉልድ አገርዋ መሄድን ጀመረች።
በትዉልድ አገርዋ በቀድሞዋ ሩማንያ የነበረዉን ፍትህ አልባነት በተለያዩ የድርሰት ስራዎችዋ በጀርመንኛ ቋንቋ ለአንባብያን ያቀረበችዉ ጀርመናዊት ደራሲ በተለይ ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኻላ በተለያዩ አገሮች ይኖሩ የነበሩ ጀርመናዉያን ይደርስባቸዉ የነበረዉን በደል በጽሁፎችዋ አስቀምጣለች። ሄርታ ሙለር በአስደናቂ የጽሁፍ ስራዎችዋ የዘንድሮዉ የስነ-ጽሁፍ ኖቤል ሽልማትን ለማግኘት በቅታለች።

Literatur Nobelpreis für Herta Müller
በጀርመን ለሽልማት በእጩነት የቀረበዉ እስትንፋስ የተሰኘዉ መጻሃፍምስል picture-alliance/ dpa