1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመንና ሕዳር ዘጠኝ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 29 2004

ሕዳር ዘጠኝ በጀርመን ታሪክ ብዙ ጊዜ ብዙ እዉነት ተፈፅሞበታል።የ1989ኙ ክስተት ግን በርግጥ የደስታ ነዉ።

https://p.dw.com/p/Rvg2
ግንቡ የነበረበት ስፍራ ዛሬምስል DW

የጎርጎሮሳዉያኑ ሕዳር ዘጠኝ በዘመናዊዉ የጀርመን ታሪክ ልዩ ሥፍራ ዓለዉ።ሕዳር ዘጠኝ ባንድ በኩል በ1938 የጀርመን ናትሴዎች አይሁዶችን በመደዳ ለመግደል፥ሐብት ንብረት፥ ታሪካቸዉን ለማጥፋት የዘመቱበት፥አስደንጋጭ ሽብር የሚታወስበት ፥ደግሞ በተቃራኒዉ በ1989 የበርሊን ግንብ የተናደበት አስደሳች ዕለት ነዉ።በ1918 የመጀመሪያዉ የጀርመን ሪፐብሊክ የታወጀዉ፥ በአምስተኛዉ ዓመት ደግሞ ይሕንኑ ሪፐብሊካዊ ሥርዓት ለማስወገድ ሒትለር የመሯቸዉ ሐይላት የመፈንቅለ መንግሥት የሞከሩበት ክስተትም ከዚሑ ዕለት ጋር የተያያዘ ነዉ።ማርሴል ፉርስቴናዉ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ሕዳር ዘጠኝ ነዉ-ዛሬ ሁለት አስራ-አንድ-እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር።ለጀርመኖች ምዕራብና-ሥራቅ ለሁለት የመገመሳቸዉ፥ለተቀረዉ ዓለም ደግሞ የቀዝዛዉ ጦርነት ፍጥጫ ምልክት የሆነዉ የበርሊን ግንብ ከተናደ ዘንድሮ-ዛሬ ሃያ-አንደኛ ዓመቱን ደፈነ።ግንቡ በተናደ ባመቱ ጀርመን ከአርባ አንድ ዓመታት መነጣጠል በሕዋላ ዳግም ተዋሐደች።ጥቅም ሰወስት 1990።እና በጀርመን ምድር ሁለተኛዉ አምባገነናዊ ሥርዓት ተወገደ።በአዉሮጳ የሶሻሊስታዊ ሥርዓት አብነት የነበረችዉ የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (DDR በጀርመንኛዉ ምሕፃረ-ቃል) ከዓለም ካርታ ተፋቀች።የምዕራብ-ምሥራቅ ግጭትም ተወገደ።
ድሮ ደግሞ ንጉስ ቪልሔልም ዳግማዊ የሚመሩት ዘዉዳዊ ሥርዓት ተወገደ።መቼ ሕዳር ዘጠኝ።1918።የጀርመን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ፊሊፕ ሻይደማን የመጀመሪያዉን ሪፐብሊካዊ ሥርዓት ያወጁትም የዚያኑ ዕለት ነዉ።

«ወዝ አደሮችና ወታደሮች የዚሕን ቀን ታሪካዊ ትርጉም ተገንዘቡ።ተሰምቶ የማያዉቅ ዕዉነት ተፈፅሟል።ትልቅና ከባድ ሥራ ይጠብቀናል።ሁሉም ነገር ለሕዝብና በሕዝብ።የሰረኛዉን ንናቄ የሚያዉክ ምንም ነገር እንዳይፈፀም እንመኛለን።ተባበሩ።ሐላፊነታችሁን በቅንነትና በታማኝነት ተወጡ።ያረጀና የበሰበሰዉ ዘዉዳዊ ሥርዓት ተገርስሷል።አዲሱ ለዘላለም ይኑር፥የጀርመን ሪፐብሊክ ለዘላለም ትኑር።»

ብዙ ግን አልቆየም።የግራና የቀኝ ሐይላት ይተጠፋፉ ያዙ።ሕዳር ዘጠኝ።ሌላ ዓመት።-1923።ሌላ ታሪክ። የብሔራዊ ሶሻሊስት ፓርቲ አባላት መንግሥትን በመቃወም ሙኒክ ዉስጥ ወደሚገኘዉ ትልቅ አዳራሽ በሠልፍ ተመሙ።የሰልፉ መሪ አዶልፍ ሒትለር።በአስረኛዉ ዓመት የጀርመንን የመሪነትን ሥልጣን ጠቅልሎ ያዘ።እና ዓለምን ያነደደዉን ሁለኛዉን ታላቅ ጦርነት ለኮሱ።

Berlin DDR Grenze Mauer Checkpoint Charlie 27.10.1961
ግንቡ-በጂዲአር በኩልምስል picture alliance/dpa

ሒትለር ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በ1942 አይሁዶችን የማጥፋቱ ዘመቻ በይፋ እስከተከፈፀበት ጊዜ ድረስ አይሁዶች ተራ በተራ ይገደሉ ነበር።ሌላ ሕዳር ዘጠኝ።1938።ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ሊፈዳ ወራት ቀሩት።ሌላ ዘግናኝ ክስተት።የዚያን ዕለት በመላዉ ጀርመን የሚገኙ የአይሁድ ሙክራቦች ጋዩ። የአይሁድ መደብሮች ተመዘበሩ።ናይትሴዎች «የራይሸስክሪስታልናኽት-መራሐ ግብር» ባሉት የጥፋት ዘመቻ አንድ መቶ ያሕል አይሁዶች ተገደሉ።ሃያ-ስድስት ሺሕ ያሕል ወደማጎሪያ ሠፈር ተጋዙ።

የአይሁዶች ጅምላ ጭፍጨፋ-ሆሎኮስት የመጀመሪያዉ ምዕራፍ።የብሔራዊሶሻሊስቶች የሰራተኞች ግንባር የተሰኘዉ ቡድን መሪ ሮበርት ሌይ ዘግናኙን ምግባር አልሸሸጉም ነበር።«አይሁድ ይወገዳል-መወገድ አለበትም።አይሁድ ይጠፋል-መጥፋትም አለበት።ይሕ የኛ ቅዱስ እምነታችን ነዉ።»

Holocaust Denkmal Berlin Flash-Galerie
የሆሎካስት መታሰቢያምስል DW/Nelioubin

የ1938ቱ ሕዳር ዘጠኝ ከ1989ኙ ሕዳር ዘጠኝ ጋር ፍፁም ተቃራኒ፥ በርግጥም የጥፋት ዕለት ነበር።የ1989ኙ ሕዳር ዘጠኝ የበርሊን ግንብ የመመጀሪያዉ ቀዳዳ የተሸነቆረበት፥ አጠቃላዩ ያረጀዉ ኮሚንስታዊ ሥርዓት የተገረሰሰበት፥ የጀርመን ዳግም ዉሕደት የተንፀባረቀበት ዕለት ነዉ።ሕዳር ዘጠኝ በጀርመን ታሪክ ብዙ ጊዜ ብዙ እዉነት ተፈፅሞበታል።የ1989ኙ ክስተት ግን በርግጥ የደስታ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ