1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመንና ብራዚል በሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ

ረቡዕ፣ ግንቦት 7 2005

በግዙፏ ላቲን አሜሪካዊት ሀገር ፤ ብራዚል፣ ካለፈው እሁድ አንስቶ እስከ ዓርብ በጉብኝት ላይ የሚገኙት፤ የጀርመን ርእሰ ብሔር ዮአኪም ጋውክ፤ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዲልማ ሩሴፍ ጋር በመሆን፤ ሁለቱ ን አገሮች በሚያሥተሣሥሩ የትብብር መስኮች

https://p.dw.com/p/18YSi
ምስል DW/R. Krieger

ላይ አትኩረዋል። ጋውክና ሩሴፍ፣ ጀርመንን የሚያስተዋውቁ 400 ያህል ፕሮጀክቶችና የውይይት መድረኮች እንዲዘጋጁ በማድረግ ፤ አንድ ዓመት ማለትም እስከሰኔ 2006 ዓ ም ድረስ የሚዘልቅ፤ «የጀርመን ዓመት በብራዚል» የተሰኘውን ትርዒት ከሁለቱ አገሮች የተውጣጣ የሙዚቃ ቡድን ባደመቀው ሥነ ሥርዓት መርቀው መክፈታቸው ታውቋል።

Stadien Fußball WM 2014 Brasilien Estádio do Maracanã Rio de Janeiro
ምስል VANDERLEI ALMEIDA/AFP/Getty Images

በአሁኑ ጊዜ ፤ ከላቲን አሜሪካ ሃገራት በመላ፤ ከጀርመን ጋር እጅግ ሰፋ ያለ የንግድ ግንኙነት ያላት ሀገር ብራዚል ናት፤ ሁለቱ አገሮች፤ በኤኮኖሚ ፤ በንግድ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ፣ በኢንጂኔሪንግና በማሺን ኢንዱስትሪም ሰፊ ግንኙነት ነው ያላቸው።

ጀርመንና ብራዚል እ ጎ አ በ 2002 ዓ ም፤ «ስልታዊ ጉድኝት » ያሉትን የጋራ ስምምነት እንደሚያጠናክሩ ተስፋቸውን የገለጡት ፣ የብራዚሏ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዲልማ ሩሴፍ ፣ የሁለቱን አገሮች ትብብር ለመገንባት ፣ በጀርመን ሀገር በሥራ ላይ ተሠማርተው በሚገኙት 50 የብራዚል ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች አማካኝነት፤ በመካከለኛ ኩባንያዎች በኩል የሳይንስ ፤ የሥነ ቴክኒክና የኢንዱስትሪ ፈጠራው ተግባር ይበልጥ በጠበቀው ግንኙነት መሠረት መጎልበት እንዳለበት ነው የሚያምኑት።

በሥነ ቴክኒክ ትልቅ እመርታ ያሳየችው ሀገር ፣ ብራዚል፤ አሁንም ከጀርመን ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ፣ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶቿን ለማበራከት ማቀዷ አልቀረም። የብራዚል የኢንዱስትሪ ውጤቶች ከሚባሉት አንዱ ፣ “Embraer“ የተሰኘው ሳዖ ፓውሎ አቅራቢያ ፣ ሳዖ ሆሴ ዶሽ ካምፖሽ ላይ የሚገኘው ኩባንያ የሚሠራው መለስተኛው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ነው። የብራዚሉ «ኤምበርኤር» ከዩናይትድ እስቴትሱ፤ «ቦይንግ»፣ የፈረንሳይ፤ ጀርመን ፤ ብሪታንያ ፤ እስፓኝና የጥቂት ተጨማሪ አገሮች ንብረት ከሆነው «ኤርቡስ» ና ፤ ከጀርመኑ «ቦምባርዲየር ኤይሮስፔስ » ቀጥሎ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የ 4ኛነቱን ሥፍራ የያዘ መሆኑ ነው የሚነገርለት። ለሲብል አገልግሎት የሚውሉ ፤ መለስተና የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች ብቻ ሳይሆን ፤ የጦር አኤሮፕላኖችንም ያመርታል።
ኩባንያው አዲስ ከሠራው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች መካከል፤ «ፌኖም 100» የተሰኘው ፣ ጀርመን ውስጥ ባለፈው የአኤሮፕላኖች ትርዒት፤ Friedrichshafen ከተማ ላይ ታይቶ ነበረ። አነስ ያለው የዚህ አኤሮፕላን ሞዴል 6,5 ሚሊዮን ያህል ዩውሮ ያወጣል። ደንበኞች የጠነጠኑ ሃብታም ነጋዴዎችና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች ናቸው። የአኤሮፕላኑ ሽያጭ ክፍል ኀላፊ ፤ ጀርመናዊው Georg Müller
እንዲህ ይላሉ፣


«ኤምብርኤር ፣ በመሠረቱ፣ የማጓጓዣ አኤሮፕላን ሲሆን፤ ሉፍታንሳንና ኤርፍራንስን የመሳሰሉ ታላላቅ ደንበኞች አሉት። ሁለቱም በኤምብርኤር አኤሮፕላኖች ይገለገላሉ። ምንልባትም እርስዎ፣ ባለፉት ሳምንታት ኤምብርኤር በሠራው አኤሮፕላን በረው ይሆናል። ሉፍታንዛ ፤ በአሁኑ ጊዜ ፤ 50 ያህል ኤምብርኤር አኤሮፕላኖች አሉት።»
ይኸው የብራዚል አኤሮፕላን ሠሪ ኩባንያ፤ ውጤቱን ለዓለም ለማዳረስ ነው ጥረቱ። እርግጥ ሞተሩን ፤ ከካናዳ ነው የሚያስገባው፤ የአኤሮፕላኑን መሠረታዊ ተሸካሚ አካል ከነተሽከርካሪው ጎማ፤ ከ«ሊብሄር» ኩባንያ ፤ ጀርመን፤ ነው የሚያስመጣው። የብራዚልን ከፍተኛ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶች፤ ብዙዎች ጠበብት በጥርጣሬ ነበረ የሚመለከቱት። አሁን -አሁን ግን ጥራታቸውን በማድነቅ ላይ ናቸው። ፎልከር ኬ ቶማላ የተባሉት የአኤሮፕላን ሥራ ዐዋቂ እንዲህ ይላሉ።
«ማንኛውም ፤ ኤምብርኤርን የተመለከተ ሰው፤ ፤ ኩባንያው ሥራ ላይ ለማዋል የሚያወጣውን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ልብ ያለ፣ ብራዚል፣ የቱን ያህል እጅግ ጥራት ባለው የሥነ ቴክኒክ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መገንዘብ አያዳግተውም። ብራዚላውያን ፤ ተጨንቀው ተጠበው ፤ አሳምረው ቅርጽ በማውጣት የሚሠሩት አኤሮፕላን ፣ በዓለም ውስጥ የመሪነቱን ቦታ ያዝን ከሚሉት ጋር እኩል ዐቢይ ግምት የሚሰጠው ነው።»
በዛ ያሉ የብራዚል ኩባንያዎች፤ በዓለም ውስጥ ታዋቂ ከሆኑት ጎራ ለመሰለፍ አጥብቀው ይሻሉ፣ ስለሆነም በተለያዩ ተግባራት እጅግ የታወቁ አንዳንድ ኩባንያዎችን ሳይቀር መግዛቱን ተያይዘውታል። ለምሳሌም ያህል፤ በ 20 ሚሊዮን ዩውሮ ፤ በጀርመን ሀገር ሮይትሊንገን በተባለችው ከተማ የሚገኘውን ልዩ ማሺን የሚያመርተውን ኢንዱስትሪ ኩባንያ ገዝተውታል። ወደ 50 የሚጠጉ የብራዚል ኩባንያዎች ጀርመን ውስጥ የሥራ እንቅሥቃሴ ያደርጋሉ። በሀምበርግ ፤ የብራዚል የክብር ቆንስል ፣ ያን ኩርሽማን እንደሚገምቱት፤ ባለፉት 2 እና 3 ዓመታት ፤ የብራዚል ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች፤ ጀርመን ውስጥ 3 ቢሊዮን ገደማ ዩውሮ ሥራ ላይ ሳያውሉ አልቀሩም።
«በዛ ያሉ የብራዚል ኩባንያዎች፤ ባለፉት 10 ዓመታት ገደማ በጥሬ ሀብት ዋጋ መጨመር ብዙ ገቢ በማግኘታቸው ገንዘቡን ሥራ ላይ አውለውታል። የገንዘብ ምንዛሪው ፣ በውጭ እዚህም ላይ በአውሮፓ ለብራዚልያውያን አመቺ ሆኖ በመገኘቱ፣ ገንዘብ በውጭ ሥራ ላይ እስከማዋል ደርሰዋል።»
ለብዙዎቹ የብራዚል ኩባንያዎች፤ ጀርመን ፤ ወደ ማዕከላዊውና ምሥራቅ አውሮፓ ለመሸጋገርም ድልድይ ሆናላቸዋለች። የፖላንድ አየር መንገድ LOT ለምሳሌ ያህል የሚያበራቸው አኤሮፕላኖች፤ የብራዚሉ ኤምብርኤር የሠራቸው ናቸው።
በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ፤ እጅግ ግዙፏ ደቡብ አሜሪካዊት ሀገር ብራዚል፤ 8,514,215 አጸፋ ኪሎሜትር የቆዳ ስፋትና ከ 192 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት ሀገር ናት። ህዝቧ በብዛት የተቀላቀለ ሲሆን፣ ጥቁሮችና ክልሶች ከነጩ ማኅበረሰብ በቁጥር ከ 2 ሚሊዮን በላይ ልቀው ይገኛሉ። በቁጥር ከተመናመኑት ነባር ተወላጆች ሌላ፤ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት፣ ከአውሮፓ ፣ ከፖርቱጋላውያን ሌላ ፤ ጣላያኖች፤ ጀርመናውያን፤ እስፓኛውያን ፣ ፖላንዳውያንና ዩክሬናውያን ፤ ከእስያም፤ ጃፓናውያን፤ ኮሪያውያን፤ ሊባኖሳውያንና ሶሪያውያን ይገኛሉ። በመካከለኛው ዘመን በባርነት ተግዘው ብራዚልን ከገነቧት መካከል በዛ ያሉ የአፍሪቃ ዝርዮች ይገኛሉ። እ ጎ አ ከ 1818 ዓ ም አንስቶ ከጀርመን ፈልሰው የገቡት ጀርመናውያን ከ 300,000 የሚበልጥ ሲሆን፤ አብዛኞቹ የሚኖሩት በደቡባዊው የአገሪቱ ከፊል ነው። የአፍሪቃ ዝርዮች የሆኑት ብራዚልያውያን በአመዛኙ የሚኖሩት፤ ሞቃት በሆነው ሰሜናዊው ምሥራቅ የአገሪቱ ከፊል ነው።
ብራዚል፤ ከአዳጊ አገሮች መካከል አንድ እመርታ በማሳየት በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት ሃገራት ጋር ለመስተካከል ከሚጥሩት መካከል አንዷ ናት። በብዝኀ ህይወት (በአጸድና በዱር እንስሳሳትና ዐራዊት) በወንዝ አሣም ዓይነት ፣ በዓለም ውስጥ ፣ ከኮሎምቢያ፤ ሜክሲኮና ኢንዶኔሺያ የምትቀድም በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የታደለች ሀገር ናት። ከአማዞን ወንዝና ገባሪዎቹ መነሻ ምንጮች አንስቶ እስከ አትላንቲክ ውቅያኖስ ጠረፍ በሰፊው የተነጠፈው፣ የፕላኔታችን አረንጓዴ ሳንባ የሚሰኘውና ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በምንጠራ ሥጋት የተደቀነበት ጥቅጥቅ ያለው የአማዞን ደን የሚገኘው በዝችው ሀገር ውስጥ ነው።
ብራዚል ፤ ለትምህርት ዐቢይ ግምት የምትሰጥ ሀገር እንደመሆንዋ መጠን፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ት/ቤት የማስገባት ህጋዊ ግዴታ አለባቸው። ማንበብና መጻፍ የሚችለው ህዝቧ ከ 88 ከመቶ በላይ ሲሆን፤ ከ 150 የማያንሱ ዩንቨርሲቲዎች አሏት። ገሚሱ የመንግሥት ሲሆኑ፣ የተቀሩት የግል ናቸው። ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት የሚበጁ 23 አዳዲስ የምርምር ተቋማት አሏት። አዳዲስ የምርምር ተቋማትን በማደራጀቱ በኩል፣ የታወቀው የጀርመን የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ተቋም «ፍራውንሆፈር ተቋም» እገዛ ያደርጋል።
ብራዚል ፣ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ሰፊ ምርምር በማድረግ የታወቀች ሀገር ናት፤ አንዱ፣ በውሃ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚቻልበት ዘርፍ ሲሆን፤ በፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ በማመንጨትም ረገድ ፤ በተለይ እጅግ ስስ ከሆነ ልዩ ፕላስቲክ የፀሐይን ሙቀት መሳብ እንደሚቻል ያሥመሠከረች ናት። በዓለም ውስጥ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እ ጎ አ በ 1979 በአልኮል ኃይል አውቶሞቢል እንዲሽከረከር የሚያስችለውን ልዩ ሞተርም የሠራች ናት። እ ጎ አ በ 2005 ፤ ቪንሴንቴ ካማርጎ የተባሉት ኢንጂንየር ደግሞ፤ እ ጎ አ በ 2005 በአልኮል (ሜታኖል) የሚሠራ የአኤሮፕላን ሞተር መሥራታቸው ይታወሳል።
ብራዚል ከተለያዩ ሃገራት ገብተው በሠፈሩ ዜጎቿ ዕውቀትና ልምድ በሰፊው ተጠቃሚ መሆኗ አልቀረም። በዚህም ረገድ የጀርመን ዝርዮች የሆኑ ዜጎቿ አስተዋጽዖ በቀላሉ እንደማይገመት ይነገራል። በኤኮኖሚ፣ ንግድ ፣ ባህልና በመሳሰሉት ዘርፎች እንደሚደረገው ሁሉ፤ በሳይንስና ሥነ ቴክኒክም የብራዚልና የጀርመን ትብብር ያማረ-የሠመረ ነው።
የጀርመን ፕሬዚዳንት ዮአኪም ጋውክ 31ኛውን፣ የሁለቱን አገሮች የጋራ የኤኮኖሚ ትርዒት ከትናንት በስቲያ ሲከፍቱ ትብብሩን አድንቀው ፤በአንድ ጉዳይ ብቻ በኅብረት መሰለፍ እንደማይቻል ቀልድ ብጤ ወርወር አድርገዋል። በመጪው 2014 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በብራዚል ይካሄዳል። «እዚያ ላይ ግን ፤ ሁሉም የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን ስለሚጥር፣ በኅብረት መታገል የሚባል ጉዳይ አይኖርም »ነው ያሉት።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Fußballer Fußball Legende Pele Brasilien Edison Arantes do Nascimento
ምስል picture-alliance/dpa
Stadien Fußball WM 2014 Brasilien Arena Pernambuco
ምስል YASUYOSHI CHIBA/AFP/Getty Images
Amazonas Wald
ምስል picture alliance/WILDLIFE
Petrobras Brasilien Amazonas Öl Gas
ምስል picture alliance/AP Photo
Brasilien Reservate Xavantes Stamm
ምስል Reuters
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ