1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመንና ከፍተኛ የምርምር ተቋማቷ፣

ረቡዕ፣ ጥቅምት 4 2002

በዘንድሮው 2002 ወይም 2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት የኖቤል ተሸላሚዎች አብዛኞቹ አሜሪካውያን ናቸው ከሰላም ሽልማት አንስቶ፣ በህክምና ሳይንስ ፣ ሥነ ቅመማ ፣ ፊዚክስ ኤኮኒሚም ጭምር አሜሪካውያኑ ሆነዋል ያሸነፉት።

https://p.dw.com/p/K6BE
በጀርመን ሀገር፣ የ ማክስ ፕላንክ የምርምር ተቋማት የሚገኙባቸው ከተሞችና ጣቢያዎች፣ምስል DW

በሥነ ቅመማ ከ 2 አሜሪካውያን መካከል በ 3ኛነት አዳ ዮናት የተባሉ እሥራኤላዊ ከመጨመራቸውና በሥነ ጽሑፍ ጀርመናዊቷ ሄርታ ሙዑለር ከማሸነፋቸው በስተቀር፣ ከ 13 የሽልማት አሸናፊዎች መካከል 11ዱ የአሜሪካ ዜጎች ናቸው።

ከ 2ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ወዲህ አሜሪካውያን በሳይንስ በዛ ያለውን ሽልማት ማግኘታቸው የታወቀ ነው። በተለይ እ ጎ አ በ 2006 , በ 1983 እና በ 1976 በሳይንስ ዘርፎች የተመደቡትን ሽልማቶች በአጠቃላይ የወሰዱ አሜሪካውያን ነበሩ። በአጠቃላይ፣ እ ጎ አ ከ1945 ዓ ም ወዲህ፣ አሜሪካውያን በ ህክምና ሳይንስ 89 ፣ በፊዚክስ 74፣ በሥነ ቅመማ ደግሞ 58፣ ሽልማቶችን አፍሰዋል።

በዘንድሮው የሳይንስ ኖቤል ሽልማት ጀርመን አንዱንም አለማግኘቷ ቁጭት ሳያሳድርባት አልቀረም። የሚያወላዳ የተፈጥሮ ሀብት በተለይ ማዕድናት የሌሏቸው ጀርመንና ጃፓን ፣ ትልቁ ደጀናቸውም ሆነ መመኪያቸው የሳይንስ ምርምርና ሥነ ቴክኒክ መሆኑን ያምኑበታል። በመሆኑም፣ ጀርመን ፣ በዚህ ረገድ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ፣ ምን ላይ መተኮር እንዳለበት በምርመራ ላይ ናት።

ባለፉት ዓመታት ፣ ጀርመን ፣ ለሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ሰፋ ያለ በጀት ከመመደብ የቦዘነችበት ጊዜ የለም። እ ጎ አ በ 2007 ዓ ም፣ ለምርምርና ዕድገት 8,5 ቢሊዮን ዩውሮ የመደበች ሲሆን ይህም፣ ከ 2006 በጀት የ 4,7 ከመቶ ብልጫ ነበረው። በ2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ፌደራሉ መንግሥት፣ ለትምህርትና ለሳይንሳዊ ምርምር በአጠቃላይ 10 ቢሊዮን ዩውሮ ነው የተመደበው። ምርምሩ ፣ በእርጅና እና በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ላቅ ያለ ትኩረት እንዲያደርግም ይፈለጋል።

ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆና እንድትገኝ፣ 3 ነገሮችን ዋንኛ ዓምዶችዋ አድርጋለች። እነርሱም፣ ዩኒቨርሲቲዎቿ፣ የምርምር ተቋማትና ኤኮኖሚዋ ናቸው። እ ጎ አ እስከ 2012 ዓ ም፣ በዩኒቨርስቲዎቿ ለሚገኙ ከፍተኛ የምርምር ተቋማት ከመንግሥት 1,9 ቢሊዮን ዩውሮ ይመደባል። በጀርመን ሀገር ከሚገኙት በመቶ ከሚቆጠሩት ዩኒቨርስቲዎች መካከል፣ በታዛቢዎች ግምገማ ፣ አጅግ የታወቁ ወይም በከፍተኛ ደረጃ ሁሉም የተሟላላቸው የሚባሉት 9 ናቸው። 40 ያህል አዳዲስ በዶክተርነት ማዕረግ የሚያስመርቁ ፣ እንዲሁም ሌሎች ወደ 40 የሚጠጉ ጠበብት፣ በኅብረት ምርምር የሚያካሂዱባቸው ኮሌጆች ወይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሉ።

ይሁን እንጂ ትብብሩ የሚፈለገውን ያህል የተጠናከረ እንዳልሆነና በዚህ ረገድ ላቅ ያለ ተግባር ማከናወን እንደሚያሻ በመነገር ላይ ነው። አጠቃላዩን የጀርመን የምርምር ተቋማት የሚመራው የጀርመን የምርምር ማኅበረሰብ የተሰኘው ሲሆን የዚህ ማኅበር ፕሬዚዳንት Matthias Kleiner እንዲህ ይላሉ።

«በኅብረት፣ እጅግ የተሳካ ምርምር የሚያካሂዱት ለምሳሌ ያህል እንደምናየው ከሆነ፣ ከማክስ ፕላንክ ተቋማት ጋር የሚሠሩት ናቸው። እጅግ ተፈላጊ የሆነው የምርምር ሃሳብ ወይም እርምጃ፣ ከዩኒቨርስቲዎች ውጭ በሚገኙ የምርምር ተቋማትም ላይ የሚያተኩረው ነው። ስለሆነም፣ የምርምር ዕድልን በአዲስ መልክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ፣ በቀጥታ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር መተባበር የግድ ነው።»

በጀርመን ሀገር ፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መሠረታዊ ሳይንሳዊ ምርምር የሚያካሂዱ ጠበብት የሚሳተፉባቸው 76 የ ማክስ ፕላንክ ተቋማት ይገኛሉ። ማክስ ፕላንክ፣ ከቀደምት እጅግ ታዋቂ የጀርመን ሊቃውንት አንዱና፣ እ ጎ አ በ 1918 ዓ ም ፣ በፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚ እንደነበሩ አይዘነጋም። ሌላው በጀርመን የታወቀው ስ,-ጥር የምርምር ተቋም፣ የሄልም ሆልትዝ የምርምር ማኅበር ( Helmholtz Gemeinschaft) የተሰኘው ነው። የዚሁ የምርምር ማኅበር ፕሬዚዳንት Jürgen Mlynek---

«የሄልምሆልትዝ የምርምር ማኅበር ተልእኮ ለብሔራዊ ጥቅም በረጅም ጊዜ አቅድ በማትኮር ስልታዊ ምርምር ማድረግ ነው። ሐሳብችንም፣ ተግባራችንም ትልቅ ነው። የምንዘረጋቸው ፕሮጀክቶች፤ አንድ ዩኒቨርስቲ ወይም አንድ አነስ ያለ የምርምር ተቋም ከቶ ማከናወን የማይችላቸውን ነው።»

የሄልምሆልትዝ የምርምር ማኅበርም ሆነ ተቋም ካተኮረባቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ በጀርመን የነቀርሳ በሽታ መቆጣጠሪያ ማእከል በኩል፣ የራሱን ድርሻ ማበርከት ሲሆን፣ የተጠቀሰው ተቋም ባለደረባ Harald zur Hausen በህክምና ሳይንስ የኖቤል ሽልማት ለማግኘት የበቁት የማኅጸን ጫፍ ነቀርሳ በተኀዋሲ እንደሚመጣ በማረጋገጣቸው ነው።

ሄልምሆልትዝ ተቋም ፣ ከዚህ ሌላ፣ በመልክዓ-ምድራዊ ሳይንስ ፣ በምድር ነውጥ፣ በሥነ- ፈለክ እንዲሁም በኅዋና የበረራ ሥነ ቴክኒክ ላይ ያተኮረ መሆኑም ይታወቃል። ጀርመን የታወቁ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች ቢኖሯትም፣ እጅግ አመርቂ ለሆነ ውጤት በመካከላቸው ጠንከር ያለ ትብብር እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።

ተክሌ የኋላ፣Negash Mohammed