1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የቅኝ ግዛት ታሪክ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2013

ጀርመን ውስጥ የቅኝ ግዛት ዘመን ምልክቶች ጎልተውም ባይሆን አሁንም መታየታቸው አልቀረም።በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚባሉ ጀርመናውያን ጀርመን ውስጥ በስማቸው መንገዶች ተሰይመውላቸዋል ልዩ ልዩ መታሰቢያዎችም ቆመውላቸዋል።የቀድሞ ቅኝ ተገዥዎች ጀርመን ቤተ መዘክሮች የሚገኙ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱላቸው እየወተወቱ ነው።

https://p.dw.com/p/3sen7
Deutsch-Südwestafrika Zeichnung Hereroaufstand 1904/5

ጀርመን ለቅኝ ግዛት ታሪኳ ምን ያህል ዕውቅና ሰጥታለች?

በጀርመን የቅን ግዛት ታሪክ ጀርመን የአፍሪቃ ሃገራትን ቅኝ የመግዛት ጥረቷን ያጠናከረችው ምዕራባውያን አፍሪቃን ለመቀራመት በጎርጎሮሳዊው 1884 ከተስማሙበት የበርሊኑ ጉባኤ በኋላ ነበር።ጀርመን  በወቅቱ ቅኝ ያልተያዙት የአፍሪቃ ሃገራት ይገባኙናል በማለት ከብሪታንያ እና ከፈረንሳይ ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃ የሚገኝ ግዛት ነበር የመሰረተችው።ያኔ በከፊል ከተቆጣጠሯቸው አገራት ውስጥ የአሁኖቹ ብሩንዲ ፣ሩዋንዳ ፣ ታንዛንያ ፣ናሚብያ ፣ካሜሩን ፣ጋቦን ፣ኮንጎ ፣ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፣ቻድ ፣ናይጀሪያ ፣ቶጎ ፣ጋና ፣ኒው ጊኒ እና ሌሎች የምዕራብ ፓስፊኮቹ የሚክሮኔስያን አካባቢዎች ይገኙበታል።ሆኖም በጎርጎሮሳዊው 1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ጀርመን ቅኝ ገዥነት ከተቆጣጠራቻቸው  አካባቢዎች አብዛኛዎቹ በተባበሩት ኅይሎች ተወረው ተወስደውባታል።ቅኝ ግዛቶቿን በይፋ የተነጠቀችውም በ1819 ነበር።አልተሳካም እንጂ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ከለኮሰው ከጀርመን ናዚ ጦር እቅዶች ውስጥ እነዚህን ቅኝ ግዛቶች መልሶ መያዝ አንዱ ነበር።    
የዶቼቬለው ዳንኤል ፔልስ እንደዘገበው ከያኔዎቹ የጀርመን ቅኝ ግዛቶች አንዷ በነበረችው በናሚብያ በአሁኑ ጊዜ የጀርመን ቅኝ ግዛት ምልክቶች በየቦታው ይታያሉ።  ጀርመናዊ የመንገድ ስሞች፣የንግድ መደብሮች እንዲሁም በቅኝ ግዛት ዘመን የተሰራ ቤተ ክርስትያን በናሚብያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ የሚገኙ የቅኝ ግዛት ዘመን አሻራዎች ናቸው።የጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን ወታደሮች በናሚብያዎቹ የሄሬሮና የናማ ህዝቦች ላይ የተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀሎችም እንዲሁ የዚያ ዘመን መታወሻዎች ናቸው።ይህ እያንዳንዱ ናሚብያዊ የሚያውቀው ጥቁር ምዕራፍ ነው።ይሁንና ጉዳዩ አሁን ጀርመን ውስጥ ብዙም ቦታ የሚሰጠው አይደለም።ናይታ ሂሾኖ መንግሥታዊ ያልሆነው የጀርመን «ዓለም አቀፍና አካባቢዊ ጉዳዮች ጥናት ተቋም» በምህጻሩ ጊጋ የአፍሪቃ ጥናቶች ሃላፊ ናቸው።በርሳቸው አስተያየት ናሚብያውያንና እና ጀርመናውያን በቅኝ ግዛት ወቅት በጀርመን የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያዩበት መንድ በጣም የተለያየ ነው።
«ናሚብያውያን ስለ ቅኝ ግዛት ዘመን በጣም እናውቃለን። ምክንያቱም የምናያቸው ኪነ ህንጻዎች ቅኝ ግዛት በምጣኔ ሃብታችን ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በቀን ተቀን ህይወታችን የምናየው ነው። ሆኖም ጀርመን ውስጥ፣ ጀርመን ቅኝ ግዛቶች እንደነበሯት ፍጹም ትረሳዋለህ።ስለዚህ በናሚብያና በጀርመን መካከል ያለው ግንኙነት የታላቅና የታናሽ ወንድም ሆኖ ታላቅ ወንድም የተፈጸመውን እንደረሳው ዓይነት ነው።»
በማለት ነበር ጊጋ በቅርቡ በሰሜን ጀርመንዋ ከተማ በሃምቡርግ ውስጥ ባስተናገደው ጉባኤ ላይ የተናገሩት።ሚሼል ሙንተርፌሪንግ የጀርመን የውች ጉዳይ ሚኒስትር ዴታ ባለፈው ህዳር ለጀርመን ፓርላማ ባሰሙት ንግግር ጀርመን ቅኝ ገዥ የነበረችበት ወቅት አጭር ስለነበር ጉዳቱ ያን ያህል የጎላ አይደለም የሚል አስተሳሰብ አሁንም እንዳለ አስረድተዋል።
« የጀርመን ቅኝ ግዛት ዘመን አጭር ስለነበረ ብዙም በደል አልደረሰም በሚል የሆነውን አይቶ እንዳላየ የማለፍ ትክክለኛ ያልሆነ ግንዛቤ ለረዥም ጊዜ  ጀርመን ውስጥ ቆይቷል።ይህ አሁንም ይሰማል። ችግሩ ይህ ያረጀ ያፈጀ ነገር ነው።»  
የጀርመን መንግሥት አፍሪቃ ውስጥ በዘመነ ቅኝ ግዛት ለተወሰዱ እርምጃዎች በይፋ እውቅና ለመስጠት ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ወስዶበታል።በጎርጎሮሳዊው 2018 ማለትም ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ሃገሪቱን ተጣምረው ይመሩ የነበሩት እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት በምህጻሩ CDU እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች የጀርመንን የቅኝ ግዛት ጉዳይ እንደ አዲስ ለመመልከት የተስማሙት።  
ሆኖም ጀርመን ውስጥ የቅኝ ግዛት ዘመን ምልክቶች ጎልተውም ባይሆን አሁንም መታየታቸው አልቀረም።በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚባሉ ጀርመናውያን ጀርመን ውስጥ በስማቸው መንገዶች ተሰይመውላቸዋል ልዩ ልዩ መታሰቢያዎችም ቆመውላቸዋል።የቀድሞ ቅኝ ተገዥዎች ጀርመን ቤተ መዘክሮች የሚገኙ በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱላቸው እየወተወቱ ነው።የቀድሞዋ የጀርመን ቅኝ ግዛት የናሚቢያ የፖለቲካ አራማጆች የናሚብያና የጀርመን መንግስታት ጀርመን በወቅቱ በናሚብያ ላደረሰችው በደል መስጠት በሚገባት ካሳ ላይ እንዲስማሙ ሲጎተጉቱ ቆይተዋል። አሁን የጀርመን መንግሥት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ነው የተገለጸው።ከመካከላቸው  በቅኝ ግዛት ወቅት ተዘርፈው ጀርመን የመጡ ቅርሳ ቅርሶችን በሚመለከት የጀርመን ቤተ መዘክሮች ማድረግ የሚገባቸውን መተግበር ጀምረዋል።አሁን የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች የተዘረፉ ቅርሶቻቸው እንዲመለሱላቸው የሚጠይቁበት አንድ የመገናኛ ማዕከል ተቋቁሟል። ፖለቲከኞችም ከቀድሞ አሁን ጉዳዩን ይበልጥ እያንቀሳቀሱ ነው።ለምሳሌ የጀርመን የባህል ሚኒስትር ሞኒካ ጉተርስ «የቤኒን ነሀሶች » በመባል በሚታወቁት የተዘረፉ ቅርሶች እጣ ፈንታ ላይ ለመነጋገር የሚመለከታቸውን አካላት ለውይይት ጋብዘዋል።እነዚህ ታዋቂ ቅርሶች ወደ መጡበት ሃገር እንዲመለሱ ናይጀሪያ ጠይቃለች። በርሊን በሚገኘው «የፕሩስያን ባህላዊ ቅርሶች ድርጅት» 440 የቤኒን ነሀሶች ይገኛሉ።ቤተ መዘክሩ በዓለማችን በተዘረፉ ቅርሶች ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።ሌሎች ከመዳብና ዚንክ  ቅይጥ እንዲሁም ከዝሆን ጥርስ የተሰሩ ቅርሶችም በዚህ ቤተ መዘክር ተቀምጠዋል።እነዚህ ቅርሶች በጎርጎሮሳዊው 1897 ቤኒን ሲቲ ተብላ ትጠራ ከነበረው ከአሁንዋ ናይጀሪያ ቤተ መንግሥት ነው የተዘረፉት።በወቅቱ ቁጥራቸው 1200 እንደሚሆን የተገመተ የልዩ ኃይል ወታደሮች ከተማዋን ወረው ቤተ መንግሥቱን መዝብረውና ዘርፈው ቅርሶቹ ወደ ብሪታንያ ቤተ መዘክር ከተወሰዱ በኋላ የበርሊኑን ቤተ መዘክር ጨምሮ ሌሎች  የአውሮጳ ቤተመዘክሮች በጨረታ ተሻምተዋቸዋል።
የጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን ታሪክ የማወቅ ፍላጎት እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ ቤተ መዘክሮች በቅኝ ግዛት ዘመን ወደ ጀርመን የመጡ የሰው ልጅ አጽሞችን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችን ለሳይንሳዊ ምርምሮች እየመለሱ ነው።ከተሞች በቅኝ ገዥዎች ለሰየሟቸው መንገዶች ሌላ ስም እየሰጡ ነው። በምሥራቅ አፍሪቃ በቅኝ ገዥዎች ላይ የተነሳ አመጽን በግፍ ባስቆመው በሔርማን ፎን ዊስማን  የተሰየመው ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የሚገኘው መንገድ  ባለፈው አርብ ሌላ ስም ተሰጥቶታል።ሆኖም ሂሾኖ እንደሚሉት በቂ ሥራ እየተከናወነ አይደለም።
«ፍላጎት ስለሌለ በቂ ሥራ እየተሰራ አይደለም።በቂ መረጃ ስለ ጉዳዩ ፍላጎት የሚያሳዩት ጥቂቶች ናቸው እነርሱም ጥናቶች ስለሚያካሂዱ ነው። ምክንያታቸው እዚህ ዘመዶች ስላሏቸው ስለ ጉዳዩ ስለሰሙ ይሆናል ምክንያታቸው በውነት ጉዳዩ በጀርመን ፖለቲካ ቀዳሚውን ስፍራ አላገኘም።»
ከጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም አንስቶ በጀርመን ቅኝ ግዛት ዘመን በናሚቢያዎቹ የሄሬሮና የናማ ጎሳዎች ላይ ለተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ጀርመን በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ ድርድር ሲካሄድ ቢቆይም እስካሁን ምንም ውጤት ላይ አልተደረሰም።የታንዛኒያ መንግስትም በዚህ ዓመት በየካቲት ወር ጀርመን ታንዛኒያን በቅኝ ግዛት በያዘችበት ወቅት ለተፈጸሙ በደሎች መስጠት ይገባታል በምትለው ካሳ ላይ  ድርድር እንዲጀመር ጥሪ ማቅረቧን ተናግራ ነበር።ይሁንና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የታንዛኒያ መንግሥት የካሳውን ጉዳይ በተመለከተ በርሊንን በይፋ አልጠየቀም።የጀርመን ፓርላማም እስካሁን ስለ ጉዳዩ የተናገረው ነገር የለም።በጀርመን ቅኝ ገዝዎች ላይ ከጎርጎሮሳዊው 1905 እስከ 1907 በተካሄደው  ማጂ ማጂ በተባለው አመጽ  የ250 ሺህ ሰዎች ህይወት አልፏል። 
በሌላ በኩል በጀርመን የትምህርት ስርዓት ውስጥ የቅኝ ግዛት ጉዳይ የሚያስፈልገውን ቦታ አለማግኘቱ አሳሳቢ ሆኗል። የቅኝ ግዛት ታሪክ አዋቂ ዩርገን ትሲመርማን በጊጋው ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፣ ጉዳዩ በአብዛኛዎቹ ትምሕርት ቤቶች ትኩረት አልተሰጠውም።
«የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎቼን ስለ ጀርመን የቅኝ ግዛት ምን ታውቃላችሁ በከፈተኛደረጃ ትምህርት ቤትስ ምን ተማራችሁ ብዮ ስጠይቃቸው አንደኛዎቹ ቡድኖች ምንም የማውቁ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በደንብ የሚያውቁ ናቸው።በተለይ ስለ ሄሬሮው የዘር ማጥፋት እናም ለምንድነው ተብለው ሲጠየቁ በአስተማሪው የሚወሰን እንደሆነ ነው የሚናገሩት።»
የታሪክ ምሁሩ ትሲመርማን እንደተናገሩት ከተማሪዎቻቸው አብዛኛዎቹ ስለ አፍሪቃም ሆነ ስለ ቅኝ ግዛት ምንም አያውቁም።ጥሩ አስተማሪ ያጋጠማቸው ደግሞ ታሪኩን በደንብ ያውቃሉ።በስርዓተ ትምሕርቱ ውስጥ ጉዳዩ ከአንድ ና ከሁለትም ሰዓት በላይ ቦታ አልተሰጠውም።በጀርመን ተማሪዎችን ስለ ቅኝ ግዛት ማስተማሩ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሂሾኖ እምነት ነው።የጀርመን ፖሊሲዎች በፌደራል መንግሥቱ ሳይሆን በእያንዳንዱ ፌደራዊ ግዛት በሚወሰኑበት በጀርመን ይህን ማሳካቱ ቀላል አይሆንም።

Geraubte Kulturgüter aus der Kolonialzeit
ምስል Wolfgang Kluge/picture alliance
Aufstand der Herero in Südwestafrika 1904
ምስል picture-alliance/dpa/F. Rohrmann
Namibia Windhuk | Denkmal zur Erinnerung an den Völkermord an den Herero und Nama
ምስል picture-alliance/dpa/J. Bätz

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ