1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ስደተኞችና ተቃውሞው

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 16 2008

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ወደ ጀርመን በመጉረፍ ላይ ያለው ስደተኛ ጉዳይ የህብረተሰቡ ዐብይ የመነጋገሪያ ርዕስ እንደሆነ ነው ።ስደተኞች መምጣታቸውን የማይቃወሙ እንዳሉ ሁሉ እንዲገቡ መደረግ አልነበረበትም ብለው የሚያማርሩ መጠለያዎችቸውንም የሚያጠቁ ጥቂት አይደሉም ።

https://p.dw.com/p/1Guiq
Deutschland Dresden Pegida Anhänger
ምስል picture-alliance/dpa/A. Burgi

ጀርመን ስደተኞችና ተቃውሞው

ስደተኞች ወደ ጀርመን በብዛት መግባታቸው፣ የገቡትም የሚስተናገዱበት መንገድ ህብረተሰቡን ሲያከራክር የከረመ ጉዳይ ነው ።ጦርነትና ጭቆና ከሃገራቸው አፈናቅሏቸው በአደገኛና እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ጀርመን ለመድረስ የቻሉትን ስደተኞች በጥሩ ሁኔታ የሚያስተናግዱ በበጎ ፈቃድ የተንከባከቡና የሚንከባከቡ ብዙዎች ናቸው ። በአንጻሩ ስደተኞች ለምን ወደ ሃገራችን መጡ ብለው የሚያማርሩ ከዚያም አልፈው የተጠለሉባቸውን እና ወደፊት ለሚመጡትም የተዘጋጁ ቤቶችን የሚያቃጥሉም የህብረተሰብ ክፍሎች አልጠፉም ።በተለይ ቀኝ ፅንፈኞችና ከነርሱ ጋር የሚተባበሩ አመፀኛ ጋጠ ወጥ ቡድኖች በጦርነት ከተመሰቃቀሉ የሙስሊም ሃገራት የተሰደዱ ህዝቦች በብዛት ጀርመን መግባታቸውን አጥብቀው መቃወማቸው ቀጥሏል ። እነዚሁ ኅይሎች ጀርመን ስደተኞችን መቀበሏን የሚደግፉ ፖለቲከኞችንም የጥቃት ዒላማቸው አድርገዋቸዋል ። አንዳንድ ወገኖች ይህን መሰሉ እንቅስቃሴ በአጭሩ ካልተቀጨ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው ።ፕሮፌሰር ቮልፍጋንግ ካሹባ የበርሊኑ የውህደትና የውጭ ዜጎች ጉዳይ የምርምር ተቋም ሃላፊ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት ስጋቱን ለማጥፋት በይሆናል የሚሰጡ አስተያየቶችንና አስቀድሞ የሚደረስባቸውን መጥፎ ድምዳሜዎች መከላከል ያሻል ።

«ፖለቲካው መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ምሁራን ኃይላቸውን አሰባስበው የሚሆነውንና የሚደረገውን ካልተጋፈጡ አዎ አንድ ነገር እየተብላላ ነው ። በዚህ የተነሳም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የቀኝ አክራሪ ቡድኖች ህዝቡ ላይ በሰፈነው ፍርሃት ላይ ለመፈናጠጥ ይሞክራሉ ።አሁን ይህ ፍርሃት ያመጣው ነገር አይታይም ።ጀርመን ውስጥ በተገን ጠያቂዎችና በስደተኞች ምክንያት ፣ማንም መኖሪያ ቤቱን አላጣም ፣ ማንም ሰው ሥራውን አልተነጠቀም፣ ማንም ሰው የቤተሰብ አባላቱ ጉዳት አልደረሰባቸውም ።ከዚያ ይልቅ አሁን የሚሰማው በዋነኛነት ግምቶችና አስቀድሞ መጥፎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ነው ። እናም ይህን ካልተከላከልነው ወደ ችግር እያመራን ነው ። »

Deutschland Dresden Pegida Demonstration
ምስል picture-alliance/dpa/B. Settnik

ምሁሩ ለዚህ አባባላቸው በምሳሌነት ያነሱት ከአንድ ሳምንት በፊት በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ ሄነሪተ ሬከር የተባሉ ፖለቲከኛ ለከተማይቱ ከንቲባነት ለመወዳደር በምርጫ ዘመቻ ላይ ሳሉ በስለት መወጋታቸውን ነው ። በኮሎኝ ማዘጋጃ ቤት የማህበራዊ የውህደትና የአካባቢ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩት ሬከር ከሶሪያ እና ጦርነት ከሚካሄድባቸው ከሌሎች ሃገራት ተሰደው ኮሎኝ ለገቡ ተገን ጠያቂዎች መጠለያ የማመቻቸት ሃላፊነት የተሰጣቸው ባለስልጣን ነበሩ።በምርጫው ዋዜማ አንገታቸው ላይ በስለት የወጋቸው ግለሰብ ጥቃቱን ያደረሰው በውጭ ዜጎች ጥላቻ መንስኤ ነው ማለቱን የከተማይቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል ። ሬከር በጥቃቱ ማግስት ሳይስተጓጓል በተካሄደው ምርጫ የኮሎኝ ከንቲባ በመሆን ተመርጠዋል ። በቀሰ በቀስ ወደ ፖለቲከኞችም የተሻገረው ጥቃት አሳሳቢ ነው ያሉት ካሹባ ያለፈው ሳምንቱ ጥቃት በአንድ ግለሰብ ቢፈፀምም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውን ቡድኖች የሚወክል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል።ካሹባ ፖለቲካው ህብረተሰቡ እና መገናኛ ብዙሃን ጥላቻን የሚያስተጋቡ አስተሳሰቦችንና ቋንቋዎችን በቆራጥነት እንዲጋፈጡ ያሳስባሉ ። ስደተኞች ጀርመን መግባታቸውን የሚቃወሙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ካሹባ በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ይከፍሏቸዋል ።

«አንደኛዎቹ ፀረ ስደተኞች አቋም የያዙትን የሚደግፉና የሚያበረታቱ ናቸው ።ይህ ትልቁ ቡድን ነው ። እነዚህ ሰዎች በ40 ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉና በአንፃራዊነት እስካሁን ፀጥታ የሰፈነበት ህይወት ውስጥ ያሉ ናቸው ።በሚኖሩበት መንደር ወይም ከተማ እስከዛሬ ያላጋጠማቸውን የሚያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ።ሌላኛው ቡድን ደግሞ አነስተኛ ቡድን ነው ። እነዚህ ከቀኝ ፅንፈኞች የሚመደቡ ናቸው ። በዚህ ቡድን ውስጥ የተደራጀ ወንጀል ይፈፀማል ፤ይህም የእሳት ቃጠሎ ፣ የጥቃት ዛቻ ፣ የስደተኞች መጠለያዎች ን ማውደም እንዲሁም ስደተኞችን የሚረዱ ሰዎችን ማጥቃት ን ይጨምራል ። »

Freiwillige Helfer Flüchtlinge Konvoi von Ungarn nach Österreich
ምስል DW/A. Shields

በካሹባ አባባል እነዚህ ሰዎች ከነርሱ የተለየ አስተሳሰብ እና ከአብዛኛው ጀርመን የተለየ መልክ ያላቸውን የሚኖሩበትን ቦታ መምረጥ እንዳይችሉ ይሞክራሉ ። ተጨባጭ ነገር ሳይዙ በፈጠራ ወሪ በሰዉ ላይ ፍርሃት አሳድረው በቋፍ ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ያባብሳሉ ። በዚህን መሰሉ ተግባር ከተሰማሩት ውስጥ እስልምና በምዕራቡ ዓለም እንዳይስፋፋ እታገላለሁ የሚለው ራሱን የአዉሮጳ አርበኞች ብሎ የሚጠራው PEGIDA የተሰኘው ቡድን ነው ። በምሥራቅ ጀርመንዋ በድሬስደን ከተማ ከአንድ ዓመት በፊት ንቅናቄውን ጀምሮ ተቃውሞ ሲበረታበት ገለል ብሎ የነበረው ፔጊዳ በርካታ ስደተኞች ወደ ጀርመን ከገቡ በኋላ እንደገና አንሰራርቷል ። ፔጊዳ ባለፈው ሳምንት በድሬስደን ከ 15 እስከ 20 ሺህ የተገመቱ ሰዎች የተካፈሉበት የውጭ ዜጎች ጥላቻ የተንፀባረቀበት ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል። በሰልፉ ላይየጀርመንን ባንዲራ ያየዙ ታዳሚዎች « ውጡ ! ውጡ! » የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብተዋል ። ለመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና ለምክትል መራሄ መንግሥት ዚግማር ገብርየል የተያዙ ቦታዎች ተብሎ የተፃፈበትና ለሰዎች መስቀያ የተዘጋጀ ገመድ የሚያሳይ ምስል ይዘው የወጡም ሰልፈኞች ነበሩ ። ቡድኑ እንቅስቃሴውን እንደጀመረ ሜርክል ህብረተሰቡ ራሱን ከቡድኑ እንዲያገል ጥሪ አስተላልፈው ነበር ።ቡድኑን አመፅ የሚያነሳሳ እና ቀኝ ፅንፈኛ ያሉት የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዜር ደግሞ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ከቡድኑ ጋር ለሚተባበሩ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል ።

«ከጥቂት ጊዜ ጀምሮ የሕገ መንግሥት ጥበቃ ባለስልጣን «PEGIDA»ን በመከታተልና በመቆጣጠር ላይ ነዉ። እንደምናስታዉሰዉ መጀመርያ ላይ ስለፒጊዳ ምንነት ፅንፈኛ ይሁን አይሁን ብዙ ክርክር አስነስቶ ነበር ። እናም አሁን የትኛዉ ነዉ የሚለዉ አያሻማም፤ ድርጅቱ ቀኝ ፅንፈኛ መሆኑ ታዉቋል። ጥገኝነት ፈላጊዎቹን በጥቅል ወንጀለኛ፤ ፖለቲከኞችን በሙሉ ደግሞ ከሃዲዎች ሲሉ ፈርጀዋል። ይህ ደግሞ ከየትኛዉም ዴሞክራሲያዊ መግባቢያ በጣም የራቀ ነዉ። በመሆኑም ማንኛዉም ስጋቱን ለመናገር ወይም ለማስተጋባት ወደዚያ የሚሄድ ሰዉ ሁሉ ክትትል እንደሚደረግበት ማወቅ ይኖርበታል። »

Wertheim - Brandanschlag Notunterkunft Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/dpa/R. Engmann

ጀርመን የገቡትን ስደተኞች ወንጀለኛ የሚለው ፔጊዳ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ይጠይቃል ።የተለየ አመለካከት እንዳለው የሚናገረው ይኽው በቀኝ ፅንፈኝነት የተፈረጀው ቡድን ከራሱ አመለካከት ውጭ የሆኑ ሌሎች አስተሳሰቦችን መስማትም ሆነ ማወቅ አይፈልግም ። ይህን መሰል አስተሳሰብ የሚያራምዱ ቀኝ ፅንፈኞች በተለያዩ አካባቢዎች የምክር ቤት መቀመጫዎችን አግኝተዋል ። ካሹባ እንደሚሉት የጀርመን ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ግን እንደልባቸው ሊያንቀሳቅሳቸው አልቻለም ።

«በርግጥ ቀኝ ፅንፈኞች በብዙ አካባቢዎች መወጣጫ ለመያዝ ሙከራ ያደርጋሉ ። ይህ ሙከራቸው ግን አይሳካላቸውም ። ምክንያቱም ከመጀመሪያው አንስቶ የሲቪል ማህበራት በግልፅ ሃሳባቸውን ይቃወማሉና ።ይህ ዓይነቱን ገጽታ ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው ። ይህ እንዲያ መሆን የለበትም ፣እኛ የህብረተሰቡ ማዕከል ነን እናንተ ደግሞ ቦታችሁ ጠርዝ ላይ ነው »ብለው የሚናገሩና ልምድ ያላቸው ግለሰቦች ለዚህ ዓይነቱ ዓላማ መቆም ይገባቸዋል ።»

ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ይህን አደገኛ አካሄድ እንዲገታ የሚያሳስቡት ካሹባ መሠረታዊው ችግር ለጉዳይu አስፈላጊው ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱ ነው ሲሉ ያስረዳሉ ።

«መቼም ቢሆን ሁሉንም ነገር በቁጥጥራችን ሥር አድርገን አናውቅም ። ይህን መርሳት የለብንም ። ከቀኝ ፅንፈኖች አመጽ ጋር ከ20 ዓመት በላይ ዘልቀናል እኛ ከአሁን በኋላ ልንቆጣጠረው ያልቻልንና የማንችለው አንድ አነስተኛ መዋቅር አለ ።በግልፅ መባል ያለበት ነገር ቢኖር የፖለቲካው የቀኝ አይን አሁንም እንደታወረ መሆኑን ነው ።በተጨማሪም በዚህ የጭለማ የሚስጥር ትግል ጀርመን ውስጥ የተገደሉትን እና ጉዳት የደረሰባቸውን በርግጥ በትክክል አልተቆጠሩም ። በመቶዎች የሚቆጠሩ መሆናቸው ነው በመካከሉ ያወቅነው ። ስለዚህ ቁጥጥሩ ፈፅሞ ስላልነበረ ለረዥም ጊዜ ተቀብለናቸው ቆይተናል ።»

Bundestag Rede Thomas de Maiziere
ምስል Getty Images/AFP/T. Schwarz

ካሹባ ይህን መሰሉ አመፅ ወዴት ሊደርስ እንደሚችል አሁን እያየን ነው ይላሉ ።የሚጮሁ ጥቂቶች የማይናገሩትን የብዙዎችን ድምጽ መሸፈን መቻላቸው ለአሁኑ ደረጃ አብቅቷቸዋልና ይህ መቀየር አለበት ሲሉም ያሳስባሉ ። የጀርመን መንግሥት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ እንዳስታወቀው በስደተኞች መበርከት ምክንያት የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል ። ሊገባደድ ሁለት ወራት በቀሩት በጎርጎሮሳዊው 2015 በተገን ጠያቂዎች መጠለያዎች ላይ 580 ጥቃቶች መፈፀማቸው ተነግሯል ። መንግሥት በቅርቡ በስደተኞች መጠለያዎች ላይ ሊጣሉ የተቃዱ ሌሎች ጥቃቶችን አክሽፎ ተጠርጣሪዎችን መያዙንም አስታውቋል ።