1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን የሚኖሩ ቱርኮች ኤርዶኻንን ለምን ይመርጣሉ?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12 2009

ቱርክ የፕሬዝደንቱን ስልጣን የሚያሰፋ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ የፊታችን ሚያዚያ ህዝበ ዉሳኔ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ነዉ። ጀርመን ዉስጥ 1,4 ሚሊየን የሚሆኑ መምርጥ የሚችሉ የቱርክ ዜጎች ይኖራሉ። የቱርክ መንግሥት እነዚህ ዜጎቹ በህዝበ ዉሳኔዉ እንዲሳተፉ ቅስቀሳዉን በተለያየ መንገድ እያካሄደ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/2ZgCl
Türken in Berlin gegen den Putsch
ምስል picture-alliance/dpa/P. Zinken

Erdogans Fans unter Deutschtürken - MP3-Stereo


ጀርመን ዉስጥ የሚኖሩ የቱርክ ዜጎች መንፈሳቸዉ ከሀገራቸዉ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነዉ። ስልጣን ላይ ለሚገኙት ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንም ለየት ያለ ስሜት እና ድጋፍ ያሳያሉ። በጀርመን የቱርክ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ጎካይ ሶፉግሉ በሀገራቸዉ የሚታየዉም ምን ይሁን ምን እዚህ የሚገኘዉ የቱርክ ዜጋ ኤርዶኻንን ለመደገፍ የሚንቀሳቀስበት ዋና ምክንያት ከማንነት ክብር ጋር ይገናኛል ይላሉ።
«ምክንያቱም በኤርዶኻን ዉስጥ የጠፋ ክብራቸዉን የሚመልስ ማንነት አይተዋል። ጠረጴዛዉ ላይ ቆሞ የት ድረስ እንደሚሄድ የሚያሳይ መሪ። የበታችነት ስሜቶች ሁሉ የሚያስወግድ ሰዉ።»
ጀርመን ዉስጥ ወደ 1,4 ሚሊየን የሚጠጉ የቱርክ፤ እንዲሁም የቱርክ እና የጀርመን ጥምር ዜግነት ያላቸዉ ትዉልደ ቱርክ ይኖራሉ። እነዚህ የቱርክ ዜጎች  በመጪዉ ሚያዝያ ሊካሄድ በታቀደዉ ህዝበ ዉሳኔ እንዲሳተፉ የቱርክ መንግሥት አጥብቆ ይፈልጋል። ምንም እንኳን የዛሬ ሁለት ዓመት በተካሄደዉ ምርጫ 40 በመቶ የሚሆነዉ ብቻ ቢሳተፍም ድምጻቸዉ ወሳኝ ሚና እንዳለዉ ይታመናል። ምክንያቱም ጀርመንም ቢኖሩ ቱርክ ዉስጥ በሚካሄደዉ ምርጫ ባላቸዉ ከፍተኛ ተሳትፎ ምክንያት ቱርክ ዉስጥ ካለዉ ዜጋ በበለጠ ለኤርዶኻን ወግ አጥባቂ እስልምና አካሄድ የላቀ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ዋናዉ ምክንያት የበታችነት እንዳይሰማቸዉ ከሚያደርግ  ስሜት ጋር የተያያዘ መሆኑን ነዉ በጀርመን የቱርክ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር የሚናገሩት።
«ይህን ማብራራት የሚያዳግት ከስሜት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነዉ። ኤርዶኻን የሚፈጥሩት ስሜት፤ አንድ ሰዉ የጥንካሬ፣ የትልቅነት እና ኃይል እንዲሰማዉ ያደርጋል። ይህን ለማስረዳት ያስቸግራል። ኤርዶኻንን እስከሞት ድረስ ከሚወዱ ሰዎች ጋርም ሳወራ ከምዕራባዉያን ፖለቲከኞች ጋር ሲነጋገር አያጎበድድም ከማለት ሌላ ከሱ ያገኙትን አዎንታዊ ነገር ሊያስረዱኝ አይችሉም። እናም ያንን ነዉ የምንፈልገዉ።»
በቱርክ የታሰበዉ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የፕሬዝደንት ኤርዶኻንን ስልጣን በማጠናከር በሀገሪቱ የአንድ ሰዉ አምባገነንነትን ያሰፍናል የሚል ትችት እየተሰነዘረበት ነዉ። የታሰበዉ ማሻሻያ ይደረግ ወይም አይደረግ በሚለዉ ህዝበ ዉሳኔ በጀርመን የሚኖሩ የቱርክ ዜጎችም እንዲሳተፉበት ለማድረግ በኮሎኝ፣ ሀምቡርግ እና ጋግናዉ የተዘጋጁ የቅስቀሳ መድረኮች መቀነስ ወይም መስተጓጎል  እዚህ የሚኖሩትን አብዛኞቹን የቱርክ ዜጎች ቅር አስቆጥቷል። በተቃራኒዉ በትዉልድ ሀገራቸዉ የመናገር እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እጅግ ተገድቧል ይባላል። ተቺዎች የኤርዶኻን ደጋፊዎች በሀገራቸዉ መንግሥት አስተዳደር የተገደቡትን ዴሞክራሲያዊ መብቶች እዚህ ጀርመን ባለዉ አጋጣሚ ተጠቅመዉ ለማጣጣም ይሞክራሉ በሚል ይወቅሳሉ። ጎካይ ሶፉግሉ ይህን ተቃርኖ ማብራራት እንደሚያዳግት አልሸሸጉም።
«ይህን ተቃርኖ ማብራራት ያስቸግራል፤ ምክንያታዊ አይደለም። አዳራሽ ባለመፈቀዱ ምክንያት ለመከለያ የተዘጋጀዉ አጥር ድረስ ሄደዉ ጮኸዋል። በሌላ በኩል ቱርክ ዉስጥ ተቃዋሚዎች ሕገ መንግሥቱ እንኳን ሳይለወጥ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ እና የመሰብሰብ ነፃነት እንደሌላቸዉ ያያሉ። በዚያ ላይ ተቃዉሞ አያሰሙም። ይህን የተመሳቀለ አቋም ማንም ሊያብራራ አይችልም።» 
ብዙዎቹ የቱርክ ዜጎች በጎርጎሪዮሳዊዉ 1960 እና 70ዎቹ ነዉ በተጋባዥ ሠራተኝነት ወደ ጀርመን የመጡት። በወግ አጥባቂነት፣ በሃይማኖተኝነት እና በወገንተኝነት የሚፈረጁት ቱርኮች፤ በአንፃራዊነት ለቀቅ ያለ በሚባለዉ የጀርመን ኅብረተሰብ ዉስጥ የራሳቸዉን ደሴት ፈጥረዉ ትዉልድ እየተኩ ይኖራሉ። ከአናቶሊያ የመጡት የቀድሞዉቹ የቱርክ ፈላሲያን በኤርዶኻን ጥብቅ ወዳጅነት ይታወቃሉ። ወጣቱ ትዉልዳቸዉም ተወልዶ ካደገበት ከጀርመኑ ማኅበረሰብ ወጣ ብሎ የኤርዶኻን አድናቂ ነዉ። ታላት ካምራን በማንሃይም የማኅበረሰብ ዉህደት እና በሃይማኖቶች መካከል ዉይይት የሚያካሂደዉ ተቋም ኃላፊ ናቸዉ። ቱርኮች ኤርዶኻንን ከሀገራቸዉ ነጥለዉ እንደማይመለከቱ ነዉ የሚያስረዱት፤
ጀርመን ዉስጥ የሚኖሩ ቱርኮች ከሀገራቸዉጋር ጠንካራ ትስስር አላቸዉ።ኤርዶኻን ከስነልቦና አኳያ ቱርክን ይወክላሉ።አብዛኞቹ ቱርካዉያን ከባህላቸዉ ጋር የተቆራኙ ናቸዉ። ኤርዶኻን ደግሞ የአናቶሊን ባህል ያንጸባርቃሉ። በዚህም ምክንያት ኤርዶኻን ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ቱርክ ላይ እንደተደረገነዉ የሚወስዱት። ይህ ፈተና ነዉ አሁን ጀርመናዉያን ቱርኮች የገጠመን።» 
የኤርዶኻን ፓርቲ AKP ላለፉት 15 ዓመታት ቱርክን እየመራ ይገኛል። ተንታኞች እንደሚሉት ኤርዶኻንም በሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት እና የኤኮኖሚ እድገትን በማምጣት በአብዛኛዉ ዜጋ ዘንድ በአዎንታ የሚታዩ ፕሬዝደንት ሆነዋል። በተለይ ደግሞ የከከሸፈዉን መፈንቅለ መንግሥት፣ በጎረቤት ሶርያ ያለዉን ጦርነት እንዲሁም የአሸባሪዎችን ጥቃት ሲመለከቱ ከእሳቸዉ የተሻለ ጠንካራ መሪ ለቱርክ አለ ብለዉ አያስቡም። 

Türkei Proteste gegen die Regierung in Istanbul 08.06.2013
የኤርዶኻን ተቃዋሚዎች በቱርክ ምስል picture-alliance/dpa
Recep Tayyip Erdogan / Türkei
ምስል picture-alliance/dpa

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ