1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን፤ የኤኮኖሚ ለውጥና ማሕበራዊ ፍትህ 1

ሐሙስ፣ ጥቅምት 24 1998
https://p.dw.com/p/E0eB

በ 60ኛዎቹ ዓመታት የጊዜይቱ ምዕራብ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተንኮታኩቶ የወደቀውን ብሄራዊ ኤኮኖሚ መልሶ በማቅናት ያሣየችው የተፋጠነ ዕርምጃ በጊዜው የምጣኔ-ሐብት ዕድገት “ተዓምር” የሚል ስያሜ የተሰጠውና ከወሰን ባሻገር ሁሉም ያወደሰው፣ ያደነቀው ነበር። ፌደራላዊት ምዕራብ ጀርመን ሁለት ዓሠርተ-ዓመታት ባልሞላ አጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ ቀደምት ከሆኑት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ጥቂት መንግሥታት መካከል አንዷ ልትሆን በቅታለች። “Made in Germany” የኢንዱስትሪ ምርቶቿ በዓለም ላይ አቻ የማይገኝላቸው ሲባሉ ቆይተዋል። ዛሬ ከውሕደቱ በኋላም በዓለምአቀፍ ደረጃ በኤኮኖሚው ዘርፍ፤ በተለይ በውጭ ንግዷ ቀደምት ስትሆን፤ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ባላት ድርሻ ጠንካራዋና በዓለም ሕብረተሰብ ዘንድም ተደማጭነቷ እያደገ የሄደች አገር ናት።

ለ 60ኛዎቹ ዓመታት የጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓምር መከሰት ብዙ ምክንያቶች ነበሩ። የሠለጠነ የሥራ ጉልበትና ዕውቀት መኖሩ፣ የምሥራቅ-ምዕራቡ ክፍፍልና የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ለምዕራቡ ወገን ኤኮኖሚ የፈጠረው ሁኔታ፣ እንዲያም ሲል የምዕራቡ ዓለም መዋዕለ-ነዋይ በሰፊው መፍሰሱ ብርቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ቢሆንም የተዓምራዊው ዕድገት ዋና ምሥጢር ከጦርነት መዓት ውስጥ የወጣው ሕዝብ ይህ ነው በማይባል ታላቅ ተሥፋ አገሪቱን መልሶ ለማቅናት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ በማሰር ቆርጦ መነሣቱ ነው። ይህ የጀርመን ሕዝብ የታታሪነት ባሕርይም ለብዙዎች አገሮች በእርያነት መታየቱ አልቀረም።

የጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት በጊዜው ባደረገው መፋጠንና መስፋፋት የተነሣ ታዲያ ብዙም አልቆየም አገሪቱ በነበራት የሥራ ጉልበት የምርቱን ተግባር መወጣቱ የማይቻል እየሆነ ይሄዳል። ለዚህም ነበር በጊዜው በርካታ የደቡባዊው አውሮፓ እንግዳ ተብዬ ሠራተኞች፤ ከስፓኝ፣ ፖርቱጋል፣ ኢጣሊያ፣ ግሪክ፣ ቱርክና ባልካን ወደዚህ መጥተው የጎደለውን እንዲያሟሉ የተደረገው። እንግዳ ተብለው አብዛኞቹ በዚሁ ትውልድ እስከመተካት ያደረሱት ብዙዎቹ የውጭ ሠራተኞች ለጊዜው የዕድገት ተዓምር፤ እስከዛሬም ለተደረገው የኤኮኖሚ ብልጽግና ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው።

እንደማንኛውም የጀርመን ሠራተኛ የመንግሥት ግብር፣ የጤናና የጡረታ ዋስትና ገንዘብ ከፋዮች በመሆን ለሕብረተሰቡ ማሕበራዊ ሥርዓት ሕልውና ታላቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በየፋብሪካው፣ በየማዕድኑ፣ በግንቢያው ዘርፍ፣ በከተማ ጽዳትና መሰል ተግባራት ተሰማርተው ያገለግላሉ። ብልዕግና ከሰፈነ ወዲህ አገሬው በሚንቀው የሥራ ዘርፍ የሚበዙት እነዚህ የውጭ ተወላጆች ባይኖሩ ኖሮ የየከተማው ገጽታ ምናልባት ሌላ መልክ በያዘ ነበር። በልምዳቸውና በአናኗር ዘያቸው የጀርመንን ሕብረተሰብ በባሕል ማካበታቸውም ሌላው ድርሻቸው ነው። ተዓምራዊው ዕድገት የጋበዛቸው የውጭ ሰራተኞች የተዓምሩ ኣካል መሆናቸውም አልቀረም።

የሆነው ሆኖ የጀርመን ኤኮኖሚ ከ 70ኛዎቹ ዓመታት ዓለምአቀፍ የነዳጅ ዘይት ቀውስ ወዲህ ቀድሞ የነበረውን የዕድገት ዕርምጃ እያለዘበና ቀስ በቀስም ሥራ አጥነት እየተበራከተ መሄድ ይጀምራል። እርግጥ የመንግሥቱም ሆነ የማሕበራዊው ዋስትና ካዝና እንደዛሬው የተሟጠጠ አልነበረምና ሥረ-አጡን መደጎሙ ያን ያህል ከባድ አልሆነም። በነገራችን ላይ በጀርመን በሙያ የተሰማራ ሁሉ ሥራ-አጥ በሚሆንበት ጊዜ የሚደጎምበትን ድርሻ ለመንግሥት ይገብራል። የማሕበራዊ ዋስትናው ስርዓትም በትውልድ የመደጋገፍ ውል ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ በተከታይ ፕሮግራም በሰፊው የምናተከሩበት ጉዳይ ይሆናል፤ ወደ ኤኮኖሚው ችግር መለስ ልበልና፣

ለመሆኑ በወቅቱ የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ይዞታ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው? የአገሪቱ አጠቃላይ የምጣኔ-ሐብት ይዞታ በተለይ ሀለቱ የቀድሞ የጀርመን መንግሥታት ምዕራብና ምሥራቅ ጀርመን መልሰው ከተዋሃዱ ወዲህ በሰፊው ተለውጧል። ዛሬ የሥራ-አጡ ቁጥር ከአምሥት ሚሊዮን የማያንስ ሲሆን በመንግሥት ማሕበራዊ ድጎማ ላይ ጥገኛ የሆነውና የተጧሪውም ቁጥር በሰፊው እየጨመረ ነው። ለጀርመን የምጣኔ-ሐብት ዕድገት መቆርቆዝና ለሥራ-አጡም መበራከት እርግጥ ባለፉት ዓመታት ምዕራባውያን ሃገራትን አንቆ የያዘው ቀውስ የተጠናወተው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሁኔታ ድርሻ አለው። ቢሆንም ዋናው ችግር የማሕበራዊውን ዋስትና ሥርዓት በጊዜው ለመጠገን፤ ሸክሙንም በፍትሃዊ መንገድ ለማከፋፈል ከፖለቲከኞች በኩል ቁርጠርነትም ሆነ ብቃት አለመታየቱ ነው።

ለነገሩ ጀርመን ዛሬም በብልጽግና ቀደምት ከሆኑት በእጣት የሚቆጠሩ አገሮች አንዷ ናት። ሐብቱ አለ፤ ግን ችግሩ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሕብረተሰቡን ግዴታ በባለሃብቶች ላይ ሣይሆን ይበልጡን በሠረቶ አደሩ ሕዝብ ላይ መጫኑ ነው። ቀደም ያለው የቻንስለር ሄልሙት ኮል ወግ አጥባቂ አስተዳደርም ሆነ አሁን በመሰናበት ላይ ያለው በጌርሃርድ ሽሮደር የሚመራው የሶሻል ዴሞክራቶችና የአንጓዴው ፓርቲ ጥምር መንግሥት የማሕበራዊ ጥገና ለውጥ ለማካሄድ በወሰዷቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች በገፍ ትርፍ የሚያጋብሱትን ኢንዱስትሪዎች የተራውን ሕዝብ ያህል ሲጫኑ አልታዩም። ፈልገዋል ወይም ደፍረዋል ለማለትም አይቻልም።

እርግጥ የምርት ዋጋና የሠራተኛው ደሞዝ መጠን በዚህ በጀርመን እጅግ ከፍተኛ ነው፤ በሌሎች አገሮች በርካሽ ለማምረትና ለማትረፍ የተሻለ ዕድል አለ ሲሉ እንኮበልላለን የሚሉትን የኩባንያ ባለቤቶች ለማቆየት ከመጫን ይልቅ ማግባባቱ ግድ መሆኑ አያጠያይቅም። ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ በሰፈነበት አገር፤ በዘመነ ግሎባላይዜሺን ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ትስስር ዘመን ኩባንያዎቹን አስገድዶ ማስቀረት አለመቻሉም ሃቅ ነው። ግን ሐብት፤ ንብረት ላፈሩበት ሕብረተሰብ ዕጣ የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ሊዘነጋ አይገባም። ከምርት መኪናዎች እስከ ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች፣ ከአውቶሞቢል እስከ ንጥረ-ነገርና ሌላም ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት ታላላቁ ዕውቅ የጀርመን ኩባንያዎች ዛሬም በዓለም ገበያ ላይ ሰፊ ድርሻ አላቸው።
የጀርመን የውጭ ንግድ ባለፉት ሶሥት ዓመታት በዓለም ላይ ቀደምቱና አዲስ ክብረ-ወሰን ያስመዘገበ ነበር። የሥራ-ገበያንና የማሕበራዊ ስርዓት ለውጥን አስመልክቶ በአገር ውስጥ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የተደረገው ለውጥ ያስከተለው ሸክም የሠርቶ አደሩን ሕዝብ ያህል አልተጫናቸውም። ታዲያ ይህም ሆኖ ልባቸው ወደ ውጭ ለመኮብለል መነሣቱና ትርፍ አልጠግብ ማለታቸው እዚህ በቅርቡ ሁኔታውን የሚታዘቡ አንዳንድ የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ጉዳይ ጠበብት እንዳሉት አገር ወዳድነታቸውን አጠያያቂ የሚያደርግ ነው።

የጀርመን የአውቶሞቢልና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ባለፉት ዓመታት በዚህ የሚገኙ ኩባንያዎቻቸውን በከፊል ወይም እንዳሉ በመዝጋትና ሠራተኞችን በገፍ በመቀነስ ብዙ ትርፍ ወደሚገኝባቸው ስሎቫኪያንና ቼክ ሬፑብሊክን ወደመሳሰሉት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች፤ እንዲሁም ወደ እሢያ በብዛት ተሻግረው በዚያው አዳዲስ ፋብሪካዎችን መክፈት ይዘዋል። ይህ ደግሞ ለብሄራዊው ኤኮኖሚ ጎጂ ከመሆን ባሻገር መንግሥት የሕብረተሰቡ ዓቢይ ችግር ሆኖ የሚገኘውን ሥራ-አጥነት ለመቀነስ የያዘውን ጥረት ከንቱ እያደረገው ነው።

የመዋዕለ-ነዋይ ወደ ውጭ ማሸግሸግ በተለይም የረጅም ጊዜ ሥራ-አጦች እንዲበራከቱ ወደ ሙያው ዓለም የመመለሳቸውን ሁኔታም ይበልጥ እያከበደው ሄዷል። ሺህ ሰው ሥራ-አገኘ በተባለ ቁጥር ሺህ ደግሞ በፋብሪካዎች ከስሮ መዘጋትም ይሁን ወደ ውጭ መሄድ የተነሣ ይሰናበታል። ችግሩ ዘላቂ እንዳይሆን በጣሙን ነው የሚያሰጋው። ዛሬ የጀርመን ሥራ-አጥ ቁጥር አምሥት ሚሊዮን ደረሰ እየተባለ ይነገር እንጂ እንደ ዕውነቱ የረጅም ጊዜው ተደጓሚ ተጨምሮበት እስከ ሥምንት ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑ ይገመታል። የማሕበራዊ ዋስትናው ስርዓት ብርቱ ፈተና ላይ ነው የሚገኝው።

የጀርመንን ማሕበራዊ ዋስትና ስርዓት ችግር ካነሣን የተለወጠው የሕብረተሰብ አምራችና ተጧሪ ሚዛን አንዱ ጊዜው የደቀነው ትልቅ ችግር ነው። የጀርመን ሕብረተሰብ በአንዳንድ ምዕራባውያን የአውሮፓ አገሮች እንደሚታየው ሁሉ በአመዛኙ ያረጀ እየሆነ ሄዷል። ከሰባ በመቶ የማያንሰው ነዋሪ ለጡረታ ዕድሜ የተቃረበ ወይም በመጦር ላይ ያለ ነው። በዚያ ላይ የሚገባውን ያህል ልጅ አይወለድም። እንግዲህ በወቅቱ ሰርቶ ለመንግሥት ግብር የሚከፍለውና ለማሕበራዊው ዋስትና ስርዓት አስተዋጽኦ የሚያደርገው 30 በመቶ እንኳ አይደርስም።

ይህ ሁኔታ በትውልድ መደጋገፍ ውል ላይ የተመሠረተው ማሕበራዊ ስርዓት ቀደም ባለ መልኩ ሊቀጥል እንዳይችል ያደረገ ነው። ስለዚህም ከመደበኛው የጡረታ ስርዓት ውጭ ሕዝብ ወደፊት እያቆለቀለ መሄዱ የማይቀረውን የአንጋፋ ዕድሜ አበሉን መጠን ለማሻሻል በግሉ ተጨማሪ ዋስትና መግባቱ ግድ ሳይሆንበት የሚቀር አይመስልም። ሁኔታው ከአሁኑ የሕዝቡን ስጋት በማጠናከር የመገብየት ፍላጎቱን እንደገታ፤ በተለያየ መልክ ቆጣቢ እያደረገው ሄዷል። ይህ ለውስጣዊው ገበያ ጎጂ እንደሆነና እየሆነ እንደሚሄድም ብዙ አያጠያይቅም።

ላለፉት ዓመታት የጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት እጦት፤ እንዲያም ሲል እየጠነከረ ለሄደው ሥራ-አጥነትና ማሕበራዊ ችግር ምላሽ ለማግኘት መጪው የጀርመን መንግሥት እስካሁን ከተደረገው ሁሉ የበለጠ ቁርጠኛ ዕርምጃ ይጠበቅበታል። ለውጥ ለማስፈለጉ በሕብረተሰቡ ውስጥ አጠቃላይ የሃሣብ አንድነት አለ። ይሁንና ችግሩ እስካሁን ይሄው የሚጠይቀውን ሸክም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈሉ ላይ ነው። ለማንኛውም የ 60ኛዎቹ የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓምር ቢቀር በቅርብ ላይደገም ታሪክ ሆኖ አልፏል። “ጀርመን ከኤኮኖሚ ዕድገት ተዓምር ወደ ማሕበራዊ ቀውስ”፤ ሣምንት በተከታይ ዝግጅት እንመለስበታለን።