1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ድሕነትና የድሕነት መለኪያዉ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 2000

የአዉሮጳ ሕብረት እንደሚበይነዉ ካማካይ ገቢ ከስልሳ ከመቶ ያነሰ የሚያገኝ ሰዉ እሱ ደሐ ነዉ።

https://p.dw.com/p/E86g
የሐብታሞቹ ደሐ
የሐብታሞቹ ደሐምስል AP

ጀርመን ዉስጥ የድሕነት ኑሮ የሚገፋዉ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ እየጨመረ መምጣቱን አንድ ጥናን አስታወቀ።የጀርመንን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ የሚያጠናዉ መንግሥታዊ ተቋም እንደሚለዉ በሐገሪቱ የኑሮ ደረጃ መመዘኛ መሠረት ከደሐ የሚመደበዉ ሕዝብ ቁጥር ባለፉት ጥቂት አመታት አሻቅቧል፣ አነስተኛ ገቢ ባለዉና በሐብታሙ መካካል ያለዉ የኑሮ ደረጃም አለቅጥ እየሰፋ ነዉ።የጀርመን ፖለቲከኞች ችግሩ መወገድ እንዳለበት ቢያምኑም በመፍትሔዉ ላይ ግን አልተግባቡም።ዛቢነ ኪንካርተስ የዘገበችዉን የነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የሐብት፣ ድሕነት ብያኔ ያዉ እንደ ሁሉም ነገር ሁሉ አንፃራዊ ነዉ።ጀርመኖች ደሐየን ሲሉም SPD በሚል የጀርመንኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሑበርቱስ ሐይል እንደሚሉት ተራብን፣ ተጠማን፣ ተመመን ታረዝን አይደለም።

«በጀርመን ፌደራላዊ ሪፐብሊክ አዲስ የድሕነት መጠን መኖሩን ማረጋገጥ አለብን።ድሕነቱ አንፃራዊ ነዉ።ይሕ ማለት ድሕነቱ የሚለካዉ በማሕበረሰባችን የኑሮ ደረጃ መሠረት እንጂ በመልማት ወይም በማደግ ላይ ካሉ ሐገራት ጋር የሚነፃፀር አይደለም።»

የአዉሮጳ ሕብረት እንደሚበይነዉ ካማካይ ገቢ ከስልሳ ከመቶ ያነሰ የሚያገኝ ሰዉ እሱ ደሐ ነዉ።በጀርመን የኑሮ ደረጃ መመዘኛ በወር ሰባት መቶ ሰማንያ አንድ ዩሮና ከዚያ በታች ገቢ ያለዉ ማለት ነዉ።በዚሕ ብያኔ መሠረት ከየስምቱ የጀርመን ዜጋ-አንዱ ደሐ ነዉ።ከሰማንያ ሚሊዮን ከሚበልጠዉ የሐገሪቱ ሕዝብ አስራ-ሰወስት ከመቶዉ ደግሞ በሥራ-አጥና በማሕበራዊ ኑሮ ድጎማ የሚኖር ነዉ።

ግራ ዘመሙ የፖለቲካ ማሕበር SPD ዝቅተኛ ደሞዝ ወይም ገቢን ለኑሮ ከሚበቃ ደረጃ እንዳያንስ ገድቦ ሥራ መፍጠር አይነተኛ መፍትሔ ነዉ-ባይ ነዉ።SPD ለመንግሥትነት የሚጣመራቸዉ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲና የክርስቲያን ሶሻል ፓርቲ (CDU/CSU) ግን ይሕን ሐሳብ አይቀበሉትም።

እትማማች የሚባሉት የሁለቱ የፖለቲካ ማሕበራት የምክር ቤት አባላት ሠራተኛዉ የሚከፍለዉ ቀረጥ ቢቀነስ ድሕነትን ማቃለል አይገድም የሚል ሌላ ሐሳብ አቅርበዋል።ከCSU የሚወከሉት የሸማቾች ጉዳይ ሚንስትር ሆርስት ዜሐፈር በተለይ የልጆች ጉዳይ መፍጠን አለበት ይላሉ።

«በኛ እቅድ መሠረት ከመጪዉ አመት ጀምሮ እርምጃዉ ከልጆች ገቢ መጀመር አለበት።በሕገ-መንግሥት የተደነገገዉን መብት ማስከበር ሥላለብን ይሕንን ማድረግ ይገባናል።ምክንያቱም የልጆች ገቢ ከቀረጥ ነፃ ካልሆነ ሕልዉናቸዉን በተገቢዉ መንገድ ማስጠበቅ አይቻልም።በሁለተኛ ደረጃ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በጣም ጨምሯል።»

የስፔዴና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ይሕን ሐሳብ አልተቀበሉትም።ምክንያቱም በነሱ እምነት አብዛኞቹ ድሆች የሚከፍሉት ቀረጥ ስለሌለ ከቀረጥ ቅነሳዉ የሚጠቀሙት ጥቂቶች ናቸዉ።ጭልጥ ያለ የግራ መርሕ የሚያቀነቅነዉ የፖለቲካ ማሕበር በፋንታዉ በሐብታሞች ላይ ቀረጥ-ይጨመር የደኸዉ ይቀነስ አይነት መፍትሔ አለዉ።በጀርመን ምክር ቤት የግራ ፓርቲ እንደራሴዎች መሪ ግሪ ጎር ጌይሲ፣-

«ጠቀም ያለ ገቢ ያላቸዉ አሉ።እነዚሕ ብዙ ቢጫኗቸዉም ከድሆቹ ደረጃ አይደርሱም።እኔ ከነሱ አንዱ ነኝ።አንድ ሰዉ ደሐ ሥለሆነ ብቻ የግራ ፖለተከኛ ወይም ደጋፊ ነዉ-ማለት አይቻልም።ይልቅዬ አንድ ሰዉ ድሕነትን ከተዋጋና ድሕነትን ለማስወገድ የሆነ ነገር ለማድረግ ከፈቀደ እሱ ግራ ነዉ።ትልቁ ጥምረት ሥልጣን ከያዘ፣ ከስፔዴና ከአረንጓዴዎቹ ተጣማሪ መንግሥት የሰባት አመታት አመራር በሕዋላ ዛሬም ጀርመን የድሆች ቁጥር መጨመሩን ሲሰማ እስካሁን የተደረገዉ ሁሉ ምንም አለመፈየዱን ያሳያል።ይሕን መለወጥ ይቻላል።መለወጥም አለበት።»

የጀርመን ካቢኔ በጉዳዩ ካንድ ወር በሕዋላ ለመከራከር ቀጠሮ ይዟል።