1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀነራል ሞተርስና የኦፔል ዕጣ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 20 2001

የአሜሪካ የአውቶሞቢል ኩባንያ ጀነራል ሞተርስ በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ከክስረት አደጋ ላይ የወደቀውን የጀርመን አምራች ኦፔልን ለመሸጥ የሚያደርገውን ውሣኔ ማጓተቱን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/JInF
ምስል picture-alliance/ dpa

ውሣኔው መጋተቱ በጀርመን መንግሥት ዘንድ ብርቱ ስጋትና ግራ መጋባትን ጭምር ነው ያስከተለው። ኩባንያው ውሣኔውን ለማጓተቱ የሰጠው ምክንያት ከቀረቡት ሁለት ገዢዎች አንዱን ለመምረጥ ገና በቂ መረጃ የለኝም የሚል ነው። ሆኖም ታዛቢዎች እንደሚሉት ሌላ ምክንያትም አልጠፋም። የኩባንያው የበላይ አካል ከአሥር ቀናት በኋላ እንደገና የሚሰበሰብ ሲሆን ኦፔልን ለመሸጥ ይወስን ወይም በዕጁ ማቆየቱን ይምረጥ ለጊዜው እንዲህ ብሎ መናገሩ ያዳግታል። በወቅቱ ግን ለወራትና ሣምንታት ሲጓተት የመጣው ውሣኔ ዕውን አለመሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን የኦፔል ሠራተኞችና ኩባንያውንም መልሶ የሕልውና ስጋት ላይ ነው የጣለው።

ኦፔልን ለመግዛት ፉክክር የያዙት ኩባንያዎች የቤልጂጉ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ድርጅት ሪፕልዉድ ኢንተርናሺናል RHJ በአንድ በኩልና በሌላ ወገን ደግሞ የአውስትሮ-ካናዳው ልዋጭ ዕቃ አቅራቢ ኩባንያ ማግና ናቸው። የመጀመሪያው ለጀነራል ሞተርስ የቀረበው ሲሆን የጀርመን መንግሥት የኋለኛውን ይመርጣል። ታዲያ የጀነራል ሞተርስ ውሣኔ እንደገና የመጓተት ዜና ከሚቀጥለው ወር ፌደራላዊ ምርጫ አንጻር የጀርመንን ፖለቲከኞች አመቺ ባልሆነ ሰዓት ላይ ነው የጠመደው።

የአሜሪካው ግዙፍ የአውቶሞቢል ኩባንያ በኦፔል የወደፊት ዕጣ ላይ የሚያደርገውን ውሣኔ ሲያሸጋሽግ ወራትና ሣምንታት አልፈዋል። የበላይ አስተዳዳሪዎቹ በቀረበላቸው ምርጫ ላይ ለመወሰን በወቅቱ ብዙም ፍላጎት ያላቸው መስሎ አይታይም። ይህ ደግሞ የጀርመኗን ቻንስለር ወደውጭ አቀራረባቸው ለዘብ ይበል እንጂ እጅጉን ነው ያስቆጣው።

“በጀነራል ሞተርስ ዘንድ ከመጨረሻ ውሣኔ ላይ ባለመደረሱ በጣም ነው የማዝነው። ሆኖም በቅርቡ እንደሚሆን ተሥፋ አደርጋለሁ። ለኦፔል ተቀጣሪዎችና ለኩባንያው የኤኮኖሚ ይዞታም በአስችኳይ ከውሣኔ መደረሱ አስፈላጊ ነው”

የኦፔል ይዞታ በአንድ በኩል፤ የጀርመንና የአሜሪካ ግንኙነት በሌላው፤ ለበርሊኑ መንግሥት ፍላጎቱን ሚዛን በጠበቀ ሁኔታ እንዲያራምድ የሚያስገድድ ነው። ስለዚህም የፌደራሉ መንግሥት አፈ-ቀላጤ ኡልሪሽ ቪልሄልም እንዳስረዱት ግቡ የድርድሩን መንፈስ አመቺ አድርጎ መቀጠሉ ይሆናል።

“ጉዳዩን አብሮ እንጂ በውዝግብ መፍታት አይቻልም። በመሆኑም ከ GM ኩባንያና ከአሜሪካ መስተዳድር ጋር ያሉንን ግንኙነቶች እንጠቀማለን። በሣምንቱ መጨረሻ በቻንስለሯ ቢሮና በዋይትሐውስ፤ ከጀነራል ሞተርስ ጋርም ግንኙነት ተደርጎ ነበር”

በዚህ በያዝነው ሣምንት መጀመሪያም አንድ የአሜሪካው ኩባንያ አመራር ዓባል በመንግሥት ድጎማና የፊናንስ አቅርቦት ጉዳይ ከኦፔል ወኪሎች፤ እንዲሁም ከጀርመን ሚኒስትሮችና የክፍለ-ሐገራት ተጠሪዎች ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ሆኖም ከዚህም ንግግር በኋላ የኦፔል ዕጣ ግልጽ ሊሆን አልቻለም። የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ካርል-ቴኦዶር-ፎን-ጉተንበርግ ባለፈው ምሽት እንዳስረዱት እርግጥ ከአንዳንድ ወገን እንደተሰማው ድርድሩ አልከሸፈም። ጀነራል ሞተርስ መፍትሄ በመሻቱ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት። ሚኒስትሩ እንዳሉት ስምምነት ላይ መደረሱ ምናልባት ከመስከረሙ ፌደራላዊ ምርጫ ወቅት ባሻገር ሊዘልቅ የሚችል ነው።
ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ቆይተው በወደፊቱ የንግግር ሂደት ጣልቃ ለመግባት ነው የሚፈልጉት። ይህ ደግሞ ከተቃዋሚው ወገን ትችትን ማስከተሉ አልቀረም። ለምሳሌ የአረንጋዴው ፓርቲ ሊቀ-መንበር ክላውዲያ ሮት በከፍተኛው የሥልጣን ደረጃ የበለጠ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

“አሁን ግልጽ በሆነ መንገድ ግፊት መደረግ ይኖርበታል። ከአሜሪካ መንግሥትም ሆነ ከጀነራል ሞተርስ ጋር በሚካሄደው ንግግር! የሚፈለገው ኦፔል የራሱን መንገድ ተከትሎ ወደፊት እንዲራመድ ማስቻል ነው። የጀርመን ግብር ከፋይ ሕዝብ ገንዘብ በከንቱ አሜሪካ ውስጥ ፈሶ መቅረት የለበትም”

በሌላ በኩል ጀርመናዊው የአውሮፓ ሕብረት የኢንዱስትሪ ኮሜሣር ጉንተር ፈርሆይገን ፌደራሉ መንግሥት በኦፔል የወደፊት ይዞታ ላይ በሚካሄደው ድርድር ቁጥብነት ሊያሳይ ይገባዋል ባይ ናቸው። ለአውሮፓ የጀነራል ሞተርስ ኩባንያ የወደፊት ዕጣ አሁንም ሃላፊነቱ በዴትሮይቱ ባለቤት ዕጅ መሆኑን አጥብቄ ላሳስብ እወዳለሁ ነው ያሉት። መንግሥት ኩባንያውን ተክቶ ሃላፊነቱን ሊወስድ እንደማይችል ያስከነዘቡት ፈርሆይገን የጀነራል ሞተርስ የአውሮፓ ቅርንጫፍ የወደፊት ዕጣ ውሣኔ የአውሮፓ አገሮችና የአሜሪካ የፖለቲካ ግንኙነት ጥያቄ እንዳይሆንም አስጠንቅቀዋል።

ይሁንና ብዙም ሰሚ ማግንታቸው የሚያጠራጥር ነው። በምርጫ ቅስቀሣ ላይ የሚገኙት ቻንስለሯም ሆኑ ሌሎች ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግፊት ከማድረግ መቆጠቡን የሚመርጡ አይመስልም። እርግጥ በሌላ በኩል ጥያቄው የጀርመን መንግሥት በቂ የተጽዕኖ አቅም ይኖረዋል ወይ ነው። የበርሊኑ መስተዳድር ኦፔልን ለመግዛት ከሚፈልገው ኩባንያ ከማግና ጋር ከወገነ ቆይቷል። የጀነራል ሞተርስ ምርጫ ደግሞ ቢቀር ለጊዜው ሌላ ነው። ኩባንያው ማግናን ላለመፈለጉም የራሱ ምክንያት አለው። የአውስትሮ-ካናዳው ኩባንያ 55 በመቶውን ድርሻ በመያዝ አዲሱን ኦፔል ለመመስረት የሚፈልገው ከሩሢያ ተባባሪው ጋር ነው።
የጀነራል ሞተርስ ድርሻ በ 35 ከመቶ የተወሰነ ይሆናል። ድርድሩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚናገሩት የ GM ፍርሃቻ በተለይ ማግና የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለሩሢያ አበሩ ሊያሸጋግር ይችላል፤ በአዲሱ ኦፔል ኩባንያ ላይ ተዕዕኖ የማድረግ አቅምም አጣለሁ የሚል ነው። የአውቶሞቢሉ ዘርፍ የኤኮኖሚ ባለሙያ ቮልፍጋንግ ሮተር እንደሚሉት ስጋቱ እርግጥ መሠረተ-ቢስ አይደለም።

“ሩሢያ ራሷ የምታመርተውን አውቶሞቢሏን ላዳን በምዕራቡ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለማሻሻል ትልቅ ፍላጎት አላት። ከዚሁ ሌላ ሩሢያ አዳጊ ገበያ ያላት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ማግና ድርሻውን ከገዛ ጀነራል ሞተርስ በሩሢያ ገበያ ላይ ከኦፔል ተጓዳኝ አኳያ ጠንካራ ፉክክር ነው የሚገጥመው”

ያም ሆነ ይህ የጀርመን ፌደራል መንግሥትና ፌደራል ክፍለ-ሕገራት ጀነራል ሞተርስ ኦፔልን ለማግና ከሸጠ 4,5 ሚሊያርድ ኤውሮ ብድር ሊሰጡት ወስነዋል። ሆኖም የዴትሮይቱ ኩባንያ ሪፕልዉድን ከመረጠ ምንጩ መዘጋቱ ነው። በሌላ በኩል ሣምንታት በፈጀው ውጣ ውረድ የተነሣ ሌላ ሶሥተኛ አማራጭም ማተኮሪያ መሆኑ አልቀረም። ይሄውም ኦፔል የኪሣራ ማመልከቻ ማቅረቡ ነው። ይህ ከሆነ ጀነራል ሞተርስ ከኦፔል ግዴታዎች ስለሚላቀቅ ከጀርመን መንግሥት መስማማት የለበትም። ግን የገበያው ባለሙያ ቮልፍጋንግ ሮተር እንደሚሉት ኦፔል መልሶ ከጀነራል ሞተርስ ዕጅ መውደቁ ነው። ይህም በተለይ በሠራተኛው ላይ ከባድ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

“አንድነት ካልተገኘ ጀነራል ሞተርስ የጀርመን መንግሥት ከዚህ ቀደም የሰጠውን 1,5 ሚሊያርድ ኤውሮ መሸጋገሪያ ብድር ምናልባት መመለስ ይኖርበታል። ኦፔልም የኪሣራ ማመልከቻ ማቅረብ አለበት። መልሶ ከጀነራል ሞተርስ ዕጅ ይወድቃል ማለት ነው። እናም የሚከተለው ኩባንያው እንደገና ለገበያ ፉክክር እንዲበቃ ጠንካራ መዋቅራዊ ለውጥ ማካሄድ ይሆናል”

ይህ በተለይ የሚጎዳው ሠራተኛውን ነው። በዚህ በጀርመን በአራት ክፍለ-ሐገራት የኦፔል ኩባንያዎች አሉ። ለውጡ ታዲያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሥራ-አጥ እንደሚያደርግ አንድና ሁለት የለውም። ከዚሁ በተጨማሪ በርካታ ልዋጭ ዕቃ አቅራቢ ፋብሪካዎችም እንዲሁ ተጎጂ ነው የሚሆኑት። የጀርመን መንግሥት ኩባንያውን ሕያው አድርጎ ለማቆየት ሲጥር የቆየውም በዚሁ ምክንያት ነው። አሁን በፌደራሉ ምርጫ ዋዜማ ወቅት ደግሞ ጉዳዩ የበለጠ ክብደት ይኖረዋል።

ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ የአውቶሞቢሉን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጨምሮ በጠቅላላው የአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ባደረሰው ችግር የሥራ አጡ ቁጥር ከማቆልቆል ሂደት በኋላ እንደገና ተመልሶ ወደ አራት ሚሊዮን ከፍ ብሏል። የአገሪቱ ኤኮኖሚ ምንም እንኳ ከያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ወዲህ እያገገመ መሆኑ ቢነገርም የሥራ አጡን ቁጥር በሰፊው ለመቀነስ የሚያበቃ ጠንካራ ዕድገት በቅርብ ይታያል ተብሎ አይጠበቅም።

MM/DW

መስፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ