1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጆሲና ማሼል፥ የሣሞራ ማሼል ባለቤት

ዓርብ፣ የካቲት 23 2010

ጆሲና ማሼል በሞዛምቢክ ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አላቸው። በፖርቹጋል አገዛዝ ላይ ነፍጥ ያነሱ፤ ወንድ ሴት ሳይሉም በርካቶች ወደ ጦርነቱ እንዲተሙ ያነቃቁ የነፃነት ታጋይ ናቸው ፦ ጆሲና ማሼል። ሴቶች በነፃነት ትግሉ ቦታ አላቸው ብለው ስለሚያምኑም ለሴቶች መብቶች ተሟግተዋል።

https://p.dw.com/p/2tY7i
DW Comic Republic - Josina Machel
ምስል DW

የነጻነት ታጋይዋ ጆሲና ማሼል

ጆሲና ማሼል በሞዛምቢክ ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አላቸው። በፖርቹጋል አገዛዝ ላይ ነፍጥ ያነሱ፤ ወንድ ሴት ሳይሉም በርካቶች ወደ ጦርነቱ እንዲተሙ ያነቃቁ  የነፃነት ታጋይ  ናቸው፦ ጆሲና ማሼል። ሴቶች በነፃነት ትግሉ ቦታ አላቸው ብለው ስለሚያምኑም ለሴቶች መብቶች ተሟግተዋል። እንዳለመታደል ኾኖ ግን ጆሲና ማሼል የሞዛምቢክን ነጻነት ሳያዩ ነው ያለፉት። ታዲያ ሞዛምቢካውያን የሴቶች ቀን በዓልን ጆሲና ማሼል ባረፉበት እለት በማክበር የነጻነት ፋኖዋን ዛሬም ድረስ ይዘክሯቸዋል። የዶይቸ ቬለዋ ግሎሪያ ሱሳ ያቀረበችውን፦ ማንተጋፍቶት ስለሺ እንደሚከተለው አቀናብሮታል። 

የቱንም ያህል የጦር መሣሪያ ቢያጓራ ተስፋ አላስቆረጣቸውም። ጆሲና ማሼል በግዞት ታንዛንያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የሞዛምቢክ የነፃነት ታጋዮችን ለመቀላቀል ቊርጠኛ ነበሩ።  

ለሞዛምቢክ ነጻነት የሚፋለመው «የሞዛምቢክ ነጻነት ግንባር» በምኅጻሩ (FRELIMO) መምሪያ እዝ ለመድረስ ለሁለት ጊዜያት መሞከር ነበረባቸው። እዚያም ለነጻነት ብሎም ለሴቶች መብቶች ታግለዋል።   

ጆሲና ማሼል ዕድለኛ ነበሩ። ወላጃቻቸው ትምህርት ቤት እንዲሄዱ አበረታትተዋቸዋል። ያ በ1945 ለተወለዱ አፍሪቃውያን የተለመደ አልነበረም። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ወደ መዲናይቱ አቅንተው እንዲከታተሉም የቤተሰቦቻቸው እገዛ አልተለያቸውም። እዚያም ጆሲና ማሼል፤ በትውልድ ስማቸው ጆሲና አቢያታር ሙቴምባ በኅቡዕ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ጀመሩ። የነጻነት ንቅናቄ ቡድኑ ፍሬሊሞ ኅቡዕ አባል በመኾንም ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት የሚደረገውን ጦርነት ለመቀላቀል ወሰኑ። ታንዛኒያ የሚገኘው የፍሬሊሞ መምሪያ እዝ ለመድረስ ግን የያኔዋ ወጣት 3,500 ኪሎ ሜትሮች በመጓዝ ለሁለት ጊዜያት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። በእርግጥ በዚያን ወቅት እንደ  ጆሲና ማሼል ሁሉ ከሞዛምቢክ እየሾለኩ የሚወጡ በርካቶች ነበሩ ይላሉ ሞዛምቢኪያዊው የታሪክ ሊቅ ኤጊዲዮ ቫዝ።  

DW Comic Republic - FRELIMO-Camp
ምስል DW

“ጆሲና እና በርካታ ወጣቶች ለነጻነት የሚደረገውን ፍልሚያ ለመቀላቀል ከደቡባዊ ሞዛምቢክ እየሾለኩ የመውጣታቸው ጉዳይ የኾነ አንዳች የተለየ ነገር የሚባል አልነበም። ከወቅቱ ፖለቲካዊ፤ ማኅበረሰባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንጻር ማንኛውም ሰው የሆነ ነገር ማድረግ እንደሚገባው ይሰማዋል ባይ ነኝ። የየዘመኑ ትውልድ የየራሱ ተግዳሮቶች ይኖሩታል። ጆሲና እና ዘመነኞቿም ሀገራቸውን ነጻ የማውጣት ትግሉን ለማፋፋም ውስጣቸውን እንዳዘጋጁ ተረድተው ነበር።”

በእርግጥ ጆሲና ማሼልን ለየት የሚያደርጋቸው ለነፃነት ትግሉ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን መስጠታቸው ነበር። በሞዛምቢኩ የኤድዋርዶ ሞንድሌን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ኢዛቤል ካሲሚሮ ይህን ያብራራሉ።   

“ጆሲና ማሼል፦ ፍሬሊሞን በ1965 እንደተቀላቀሉ የሴቶች ክንፍን በማሠልጠኑ ተግባር ተካፋይ ኾኑ። በ1967 ፍሬሊሞ ስዊትዘርላንድ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ዕድሉን አመቻቸላቸው። እሳቸው ግን የጦርነቱን ሒደት በቅርበት ለመከታተል ይበልጥ እውስጡ የመግባት አስፈላጊነትን በጽኑእ ስላመኑ የትምህርት ዕድሉን ሳይቀበሉ ቀሩ።”

ጆሲና ማሼል ለነጻነት በሚኪያሄደው ጦርነት የሴቶች ሚና ጉልኅ ድርሻ ሊኖረው ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም ነበራቸው። ከፍሬሊሞ የሴቶች ክንፍ ዋነኛ አንቀሳቃሾችም አንዷ ነበሩ። የፍሬሊሞ የሴቶች ክንፍ ለሴቶች የውጊያ ሥልጠና እና የፖለቲካ ትምህርት የሚሰጥበት ነበር። በፍሬሊሞ የሥልጣን እርከንም ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል። በ1969 የፍሬሊሞ የማኅበረሰብ ጉዳይ ክፍል ኃላፊም ኾኑ። ያኔ ገና የ24 ዓመት ወጣት ነበሩ።  

DW Comic Republic - Josina Machel
ምስል DW

ለጋዋ ጆሲና ማሼል ብዙም ሳይቆዩ ታመሙ፤ እናም የጤንነታቸው ኹኔታ እጅግ ማሽቆልቆል ጀመረ። እንዲያም ሆኖ ግን አዲስ ማኅበረሰብን ለመገንባት ያለዕረፍት መታተራቸውን ቀጠሉ ይላሉ ሞዛምቢካዊው የታሪክ ተመራማሪ ኤጊዲዮ ቫዝ።  

“ስለ ጆሲና መናገር ካለብኝ ለራሳቸው ጊዜ ሳይሰጡ በሥራ የተጠመዱ መኾናቸውን ነው። ያም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አልነበረም፤ ይልቁንስ ስለሕዝቡ፤ ሕይወት ስለማዳኑ፤ የተባበረ፤ አንተ ትብስ አንቺ እየተባባለ ለጋራ ጥቅም የቆመ ማኅበረሰብን ስለመገንባት ነበር ይጨነቁ የነበረው።”

በ1969 ጆሲና ሣሞራ ማሼልን አገቡ። ሞዛምቢክ በ1975 ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃነቷን ስታውጅ ሣሞራ ማሼል የሀገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት መኾን ችለዋል። ጆሲና ማሼል ግን ሀገራቸው ከፖርቹጋል ነጻ የወጣችበትን ቀን በሕይወት ዘመናቸው ለማየት አልታደሉም። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1971 ታንዛኒያ ውስጥ በሚገኝ ሐኪም ቤት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ጆሲና ማሼል ያረፉበት እለት ሚያዝያ 7 ሞዛምቢክ ውስጥ የሴቶች ቀን ተብሎ ዛሬም ድረስ ይከበራል። 

ግሎሪያ ሶሳ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ