1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩጋንዳ የጆሴፍ ኮኒን ፍለጋዋን መቀጠልዋ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 2009

ዩኤስ አሜሪካ በሽሽት ላይ የሚገኙትን የዩጋንዳ ዓማፂ የሎርድ ሬዚስተንስ አርሚ፣ በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ «ኤል አርኤ» ቡድን መሪ ጆሴፍ ኮኒን ለመያዝ ለተጀመረው ዓለም አቀፍ የፍለጋ ዘመቻ ታደርገው የነበረውን ትብብር ማብቃቷን ገለጸች። ዩጋንዳ ግን ካለ አሜሪካ ድጋፍም ፍለጋዋን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

https://p.dw.com/p/2aTN2
Ugandische Truppen jagen LRA im Kongo 2009
ምስል DW/S. Schlindwein

Fokus Afrika A 01.03.2017 - MP3-Stereo

የዩኤስ አሜሪካ የአፍሪቃ እዝ፣ «አፍሪኮም» ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ዩኤስ አሜሪካ የኮኒ ቡድን በመዳከሙ ፍለጋውን መቀጠሉ ትርጉም አይኖረውም በሚል እጎአ ከ2011 ዓም ወዲህ በዩጋንዳ ባሰማራችው የጦር ቡድን፣ ከ12 በሚበልጡ የጦር አማካሪዎች ጭምር ተሰጠው የነበረውን ትብብር ታበቃለች። በመግለጫው መሰረት ግን፣ ዩኤስ አሜሪካ ይህንኑ ትብብሯን ብታበቃም፣ በዩጋንዳ እና ባካባቢ መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ ካካባቢው ሀገራት ጋር የፀጥታ ጥበቃ ትብብሯን ታጠናክራለች። ዩኤስ አሜሪካ ለብዙ ዓመታት ላደረገችላት ድጋፍ ዩጋንዳ ምስጋናዋን ማቅረቧን የገለጹት የዩጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋድየር ጀነራል ሪቻርድ ካሬሚሬ፣ ዩኤስ አሜሪካ ለኮኒ ፍለጋ በጦር አማካሪዎችዋ አማካኝነት ስታደርገው የነበረውን ትብብሯን ላቋረጠችበት ውሳኔዋ «ኤልአርኤ» ተዳክሟል በሚል በሰጠችው  ምክንያት እንደማይስማሙ አስታውቋል።

የ«ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣ ኤል አርኤ»  ቡድን መሪ ጆሴፍ ኮኒን ለመያዝ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተደረገው ዘመቻ 800 ሚልዮን ዶላር ነው የወጣበት። ዓመፁን  በሰሜናዊ ዩጋንዳ የጀመረው እና በኋላም ወደ አካባቢው ሀገራት ያስፋፋው «ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣» ከተቋቋመበት እጎአ 1987 ዓም ወዲህ ከ100,000 የሚበልጥ ሰው መግደሉን እና 60,000 ህፃናትን ማገቱን የተመድ ዘገባዎች ያሳያሉ።   የጦር ምንጮች እንዳመለከቱት፣ «ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣»  በብዙ ትናንሽ ቡድኖች የተከፋፈለ ሲሆን፣ እነዚህ ቡድኖች በብዛት በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። 
ዩኤስ አሜሪካ ጆሴፍ ኮኒን አድኖ የመያዙን ዓለም አቀፍ ፍለጋ ዘመቻ ማብቃቷን ይፋ ካደረገች ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በአፍሪቃ አስከፊ የጭካኔ ተግባር በመፈፀማቸው ከሚታወቁት ቡድኖች አንዱ የሆነው የ«ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣» መሪ ኮኒ ዋነኛ ረዳት የሆኑት ሻለቃ ማይክል ኦሞና በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለዩጋንዳ መከላከያ ሰራዊት እጃቸውን መስጠታቸው ተሰምቷል።  እንደ ዩጋንዳ ጦር ኃይል ምክትል ቃል አቀባይ ሻለቃ ኪኮንቾ ታባሮ ገለጻ፣ የሻለቃ ማይክል ኦሞና ለዩጋንዳ ጦር ኃይላት እጃቸውን መስጠት በዩጋንዳ መንግሥት አንፃር ካለፉት 25 ዓመታት በላይ የሚዋጋውን  የ «ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣» አቋም ይበልጡን ያዳክመዋል።  

Infografik LRA The Lord’s Resistance Army Englisch

ኦሞና ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር በ «ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ» የታገቱት እና በጆሴፍ ኮኒ ለውጊያ ተግባር የተመለመሉት። ከ «ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣» ማምለጥ የተሳካላቸው ሻለቃ ማይክል ኦሞና ከዩጋንዳ ጦር ጋር በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሲተባበር ለቆየው የዩኤስ አሜሪካ ጦር ቡድን እጃቸውን ከሰጡ  በኋላ የ«ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣» ን እንዴት እንደተቀላቀሉ በቋንቋቸው ሉዎ አስረድተዋል።

« እጎአ በ1994 ዓም አንድ ቀን ማታ ከቤቴ ታግቼ ወደ ጫካ ተወሰድኩኝ። ከሆነ ጊዜ በኋላ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ደረስን። በዚያ ኦቹዌ ከተባለ አንድ ጓደኛዬ ጋር መገናኘት ቻልኩኝ። እና ሁሌ ያለሁበትን ቦታ እነግረው ነበር። ለዚህም ይመስለኛል እስከዛሬ  በህይወት ልቆይ የቻልኩት። ወደ ጫካ ከተወሰድኩ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ማለትም እጎአ ከ1995 እስከ 2017 ዓም በራድዮ ኦፕሬተርነት ሰርቻለሁ። »
ኦሞና በቡድኑ በቆዩባቸው 23 ዓመታት፣ በተለይ ጆሴፍ ኮኒ የሚያደርጓቸውን ግንኙነት ሲያቀነባብሩ እና የቡድኑን አባላት ከማንኛውም የሚደቀን አደጋ ሲያስጠነቅቁ እንደነበር  ገልጸዋል። ከ«ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ» ማምለጥ የተሳካላቸው ሻለቃ ማይክል ኦሞና ከዩጋንዳ መንግሥት ጋር ተባብረው ለመስራት ቃል በመግባት፣ ሌሎች የ«ኤልአርኤ» አባላት ወደ ትውልድ ቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚያበረታቱ አስታውቀዋል።  በዩጋንዳ መንግሥት እና በ«ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ» ዓማፅያን መካከል የቀጠለው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በግንባር ቀደምትነት የሽምግልና ጥረት ያካሄዱት የጉሉ ከተማ ቤተ ክርስትያን አቡን ጆን ባብቲስት ኦዳማ ተጨማሪ ዓማፅያን በቀጣዩቹ ጊዚያትም እጃቸው እንደሚሰጡ ተስፋ ማድረጋቸውን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። 

USA unterstützen Uganda bei der Jagt auf Joseph Kony
ምስል picture-alliance/dpa/Price

« የዩኤስ አሜሪካ ወዳጆቻችን፣ እናመ/ሠግናለን፣ ላደረጋችሁልን ሁሉ እግዚአብሔር ይክፈላችሁ። በኛ ድጋፍ ተጨማሪ ዓመፃያን ቡድኑን ለቀው ይወጣሉ ብለን እንጠብቃለን። እግዚአብሄርን የምንለምነው አሁንም በጫካ ያሉትን ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ነው። ዩጋንዳ ከጠፉት ልጆችሽ መካከል አንዱን መልሰሽ በማግኘትሽ ተደሰቺ። » 

ከዩኤስ አሜሪካ ጋር ተባብሮ የሰራው የዩጋንዳ መከላከያ ሰራዊት «የኤልአርኤ» ዓማፅያን አሉበት በተባለው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጫካ ዓማፅያኑ እጃቸውን እንዲሰጡ እና ምህረት እንዲጠይቁ የሚያሳስብ ጽሑፍ የሰፈረባቸውን ጥራዞች በትኖዋል። የሻለቃ ማይክል ኦሞና እጅ መስጠት በ«ኤልአርኤ» መሪ ጆሴፍ ኮኒ እና ተከታዮቻቸው አንፃር የተጀመረው ዘመቻ ፍሬ እያስገኘ መሆኑንም እንዳረጋገጠ የዩጋንዳ ጦር ኃይል ምክትል ቃል አቀባይ ሻለቃ ኪኮንቾ ታባሮ አስታውቀዋል። 

« ከፍተኛ የጦር ቡድን አባላት፣  ቡድናቸውን የሚከዱበት ድርጊት፣  አቅማቸው መዳከሙን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነው። እና አሁን ጥረታችን በጠቅላላ ያተኮረው  የ«ኤልአርኤ»ን እብደት ማብቃት የሚያስችሉ እርምጃዎች በማዘጋጀቱ ላይ ነው። በየጫካው ለተሸሸጉ የ«ኤልአርኤ» ዓማፅያን ሁሉ ከያሉበት እንዲወጡ ጥሪ አድርገንላቸዋል፤ በአካባቢው የዓማፂውን ቡድን የእብደት ተግባር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማብቃት ቆርጦ የተነሳ የተጠናከረ የፀጥታ መዋቅር እንደተዘረጋም መልዕክት አስተላልፈንላቸዋል። »

የ35 ዓመቱ ኦሞና አሁን ወደ ትውልድ ከተማው ጉሉ የተመለሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ዩጋንዳውያን የሕግ ባለሙያዎች የ«ኤልአርኤ» ሰለባዎች ለተመላሽ ዓማፅያን ይቅርታ እንዲያደርጉ የሚቻልበትን መንገድ በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ።  በዩጋንዳ የፍትህ ሚንስቴር በከፍተኛ አማካሪነት የሚሰሩት ማርግሬት አጆክ የሀገሪቱ መንግሥት ለዓማፅያኑ ያዘጋጀው የምሕረት መርሀግብር ሰለባዎቹንም ማጠቃለል እንደሚገባው  አሳስበዋል።
« ሕጋዊነቱ የተረጋገጠ የምሕረት ሂደት ሊኖረን ይገባል። እንደኔ አስተሳሰብ፣ የምሕረቱ መርሀግብር ጥቃት ፈፅሟል የሚባለውን ግለሰብ ፣ የጥቃት ሰለባዎቹን ይቅርታ መጠየቅ ማስቻል አለበት። ተመላሹ ዓማፂ ይቅርታ ከጠየቀ እና ሰለባዎቹ ይቅርታ ካደረጉለት፣ በኋላም፣  የምሕረት ሰርቲፊኬት ካገኘ  ፣ ይህ፣  በህብረተሰቡ ውስጥ መልሶ የሚዋኃድበትን ሁኔታ ያቃልልለታል ማለት ነው። »  

Niederlande Dominic Ongwen vor dem  Internationalen Strafgerichtshof
ምስል picture-alliance/AP Photo/P. Dejong

የዩኤስ አሜሪካ ጦር ጆሴፍ ኮኒን በመፈለጉ ዘመቻ ላይ ከዩጋንዳ ጦር ጋር መተባባር ከጀመረ ወዲህ የዓማፂው ቡድን ህፃናትን የሚያግትበት ተግባር በጉልህ ቀንሷል።  ልክ እንደ ኦሞና ገና ሕፃን እያለ በ«ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ» ታግቶ በውጊያ ተግባር ተሰማርቶ የነበረው የቀድሞ ከፍተኛ መሪ እና የኮኒ የቅርብ ረዳት ዶሚኒክ ኦንግዌ እጎአ ጥር ፣ 2015 ዓም እጁን መስጠቱ ይታወሳል።  ኦንግዌን በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅሟል በሚል በወቅቱ ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ቡድን ፣ «አይ ሲ ሲ» በተመሰረተበት ክስ  ችሎት የቀረበው የመጀመሪያው የ««ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ»  አባል ናቸው። «አይ ሲ ሲ» በሽምቅ ተዋጊው ቡድን መሪ ጆሴፍ ኮኒ ላይ በስብዕና አንፃር በፈፀሙት ወንጀል የእስር ማዘዣ አስተላልፎባቸዋል።   

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ