1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጆይስና የደረሰባት ዘረኛ አድልዎ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2006

አንዲት ትውልደ ኬንያት በቆዳ ቀለሟ ምክንያት እዚህ ጀርመን የደረሰባት አድልዎ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል ። የተላከላትን ጥቅል እቃ ለመቀበል ወደ አንድ የፖስታ አገልግሎት ሰጭ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ጎራ ያለችውን ወይዘሮዋን የድርጅቱ ሠራተኛ ጥቁር ስለሆንሽ አልሰጥም ብላ ትከለክላታለች ።

https://p.dw.com/p/1AcWm
Internationaler Tag gegen Rassismus Deutschland Symbolbild Antirassismus
ምስል Reuters

እቃው የተላከው ለርስዋ መሆኑን ማንነቷን የሚገልፅ መታወቂያ እንዳላት ብታስረዳም የሰማት የለም ። በመጨረሻም የደረሰባትን ወዲያውኑ ለፖሊስ ካሳወቀች በኋላ ንብረቷን በእጇ ለማስገባት ችላለት ። ያነጋገረቻት ሂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች ።

ወይዘሮ ጆይስ ኒቲስ ፣ ዶርስተን በተባለው በምዕራብ ጀርመኑ የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ክፍለ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የዶርስተን ከተማ ነዋሪ ናት ። ጀርመን ስትኖር 17 ዓመት ሆኗታል ። ከፍተኛ ትምህርቷን እዚሁ ጀርመን ነው የተከታተለችው ። ጀርመን ከመጣች ከጀርመናዊ የወለደቻቸው የ 16 ትና የ6 ዓመት ልጆች እናት ናት ። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በምትኖርበት በዚሁ ከተማ ወደ ሚገኝ HERMES በተባለ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩል የተላከላትን ጥቅል ዕቃ ለመውሰድ ትሄዳለች ። እዚያ ስትደርስ የገጠማት ግን ፈፅሞ ያልጠበቀችው ነበር ።

«እዛ ስደርስ ያገኘኋት ሠራተኛ እቃው አለ ፤ግን ልሰጥሽ አልችልም አለችኝ ። ለምን ብዮ ስጠይቅ ለጥቆሮች ምንም ዓይነት እቃ እንደማይሰጡ ነገረችኝ ። እንደገና ለምን ስላት ብዙ ጥቁሮች የነርሱ ያልሆኑ እቃዎችን ለመውሰድ የሃሰት ስም በመጠቀም ስለሚያጭበረብሩ ነው አለችኝ ። እኔ ደግሞ መታወቂያ እንዳለኝና በመታወቂያዬና በጥቅሉ ላይ የተፃፈው አድራሻ ተመሳሳይ ስለሆነ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር እንደማልፈፅም ነገርኳት ።ግን ጥቅሉን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም።»

18.04.2013 DW Deutschland Heute Rassismus

በአጋጣሚው በእጅጉ ያዘነችው ጆይስ ሴትየዋ ማምረሯን ስትገነዘብ ወዲያውኑ ለፖሊስ ደውላ የደረሰባትን አሳወቀች ።

«ለፖሊስ ደውዮ ያለችኝን ስናገር ፖሊሱ የምነግረውን ማመን ስለተቸገረ ሴትየዋን በኔው ስልክ ሲጠይቃት ለኔ የነገረችኝን ማለትም ጥቅሎችን ለጥቁሮች እንደማይሰጡ ለፖሊሱ ደገመችለት ። በዚህ እድለኛ ነበርኩ ምክንያቱም ለኔ ያለችውን ነው የነገረችው ።ምንም ምስክር ስላልነበረኝ ማንም የሆነውን ሊያውቅ አይችልም ነበር ። »

ጉዳዩን ፖሊስ ከሰማ በኋላ ሠራተኛዋ ጥቅሉን ወደ እቃ መስጫው ከወረወረችልኝ በኃላ « ዛሬ በተለየ አስተያየት እሰጥሻለሁ በሌላ ግዜ ግን ይህን አናደርግም »ስትል እቃዋን አስረክባታለች ። ጆይስ እንደምትለው ጀርመን ውስጥ 17 ዓመት ስትኖር የዚህ ዓይነት አድልዎ ገጥሟት አያውቅም ይህ የመጀመሪያዋ ስለሆነም በጣም ተበሳጭታለች ።

« በፍጹም በፍጹም በፍፁም እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም የሆነው ውስጤን በጣም ነው የተሰማኝ ። ላምነው አልቻልኩም ። በጣም ነበር የተናደድኩት አዝኛለሁ ደንግጫለሁ ። የሚታመን አይደለም ። በእውነት አሳፋሪ ነው ። በ2013 ዓም ይህን መሰል ድርጊት መፈፀሙ አስነዋሪ ነው ። »

የጆይስ ታሪክ በመላ ጀርመን ከተሰራጨ በኋላ በርካታ የድጋፍ ኢሜሎች ደርሰዋታል ። ትውልደ ኬንያዊቷ ጆይስ በሆነው ብታዝንም ለጀርመኖች ግን መጥፎ ስሜት የለኝም ትላለች ።

«የሆነው ነገር ስለ ጀርመኖች ያለኝን አመለካከት ይቀይራል አልልም ምክንያቱም ጀርመኖች ሁሉ እንደዛ አይደሉም ። ጀርመኖችን በሙሉ በአንድ ማሰሮ ውስጥ አስቀምጬ ሁሉም አንድ ናቸው አልልም »

የ40 ዓመትዋ ጆይስ እንደምትለው አጋጣሚው ቢያበሳጫትም በሌላ በኩል ደግሞ አጠንክሯታል ። ምናልባት ወደፊት ለጥቁሮች ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ የምሆን ይመስለኛል ትላለች ። ጀርመን ውስጥ ጥቁሮች መሰል ሁኔታ ሲገጥማቸው ለጠብ ከመነሳሳት በመቆጠብ ና በመረጋጋት የደረሰባቸውን ለፖሊስ መንገር ይህ ካልተፈለገም እነዚህን ጉዳዮች ለሚከታተሉ ድርጅቶች ማሳወቅ እንደሚገባቸውም አሳስባለች ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ