1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ገና ያልታወቀው፣ የፍጥረተ-ዓለም ምሥጢርና የምድራችን የሙቀት መጠን፣

ረቡዕ፣ ኅዳር 30 2002

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣የሥነ-ፈለክ መታሰቢያ ዘመን የተሰኘው 2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ሊያከትም 22 ቀናት እንደቀሩት፤ የአሜሪካው የኅዋ ተመራማሪ ድርጅት NASA በዛሬው ዕለት

https://p.dw.com/p/KyJl
ሀብል ቴሌስኮፕ በኅዋ ጠለቅ ብሎ ያነሳውና ወደ ምድራችን ያስተላለፈው ፎቶግራፍ፣ምስል AP

ከዚህ ቀደም ሌሎች ካሜራዎች ባላሳዩአቸው አያሌ የብርሃን ዓመት ርቀት ባላቸው የኅዋ አካላት ላይ የሚያማትር Wide-f ield Infrared Survey Explorer(WISE) መሣሪያ የጫነ ሳቴላይት ከ ቫንደንበርግ አየር ኃይል ጣቢያ፣በካሊፎርኒያ ያመጥቃል። በአኅጽሮር WISE የተሰኘው ልዩ ካሜራ፣ ከ HUBBLE እና ከሌሎቹም ካሜራዎች ሁሉ በላቀ ሁኔታ በሚመጡት 9 ወራት፣ በምድራችን ሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች አናት በመሽከርከር ሰማዩን በመላ እንደሚያስስና ከፊሉን ጊዜውን ደግሞ ፣ እጅግ ቀዝቃዛ የሚሰኙትን ርቀታቸው የት-እየለሌ የሆነውን ከዋክብት፣ ጨለማ የዋጣቸውን ሥባሪ ከዋክብትና በብርሃን እጅግ የተንቦገቦጉትን ተጫፋሪ የኅዋ አካላት (ጋላክሲስ)በመፈለግ እንደሚሠማራ ተገልጿል።

ከብሪታንያ፣ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንደገለጹት፣ HUBBLE ቴሌስኮፕ ራሱ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ፣ 13 ቢልዮን የብርሃን ዓመት ርቀት ያላቸውን ፣ ጥንታውያን የተጫፈሩ የኅዋ አካላትን ምስል በትናንቱ ዕለት ወደምድር ልኳል።ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር፣ NASA በ HUBBLE ቴሌስኮፕ ያስገባው አዲሱ፣ Wide Field Camera 3 የተሰኘው መሣሪያ ያነሣቸው የተጫፈሩ የኅዋ አካላት ለፍጥረተ-ዓለም መዘርጋት ሰበብ እንደሆነ የሚነገርለት ዐቢዩ የኅዋ ፍንዳታ ካጋጠመ ከ 600 ሚሊዮን ዓመታት በኋላ የተከሠቱ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ጠቁሞአል ነው የተባለው።

ፍጥረተ-ዓለማት የተዘረጉበትን ምሥጢር ለማወቅ ምርምሩ በምድርና በኅዋ እንደቀጠለ መሆኑ የታወቀ ነው። የኅዋው ምርምር ያተኮረው ፣ ካሜራም ሆነ ቴሌስኮፕ የጫኑ መንኮራኩሮችን (ሰው- ሠራሽ ሳቴላይቶችን )በማምጠቅ ሲሆን፣ የየብሱ ደግሞ በተለይ አውሮፓ ውስጥ በፈረንሳይና እስዊትስዘርላንድ ድንበር ላይ 100 ሜትር ጥልቀት ባለው ከርሠ- ምድር 27 ኪሎሜትር ርዝማኔ ባለው ክብ መሿለኪያ መሰል ቦታ የአቶም ቅንጣቶችን ፤ Protons ከዚህ ቀደም ታይቶ ባልታወቀ ፍጥነት በመግነጢሳዊ ኅይል በሚሽከረከር፣ Large Hadron Collider በተሰኘው የአቶም ጨፍላቂ መሣሪያ በተቃራኒ አቅጣጫ አስፈንጥሮ በማጋጨት፣ ባለፈው ኅዳር 21 ቀን 2002 ዓ ም፣ አዲስ ክብረ-ወሰን መሆኑ የተመዘገበለትን 1,18 ቴራኤሌክትሮንቮልት (TeV)ማመንጨቱ የሚታወስ ነው። ከዚያ በፊት የነበረው ክብረ ወሰን፣ እ ጎ አ በ 2001 ዓ ም፣ የዩናይትድ እስቴትሱ፣ Fermi National Accelerator Laboratory’s Tevatron ፣ የአቶም ቅንጣቶችን በመጨፍለቅ ያስመዘገበው 0,98 TeV (ቴራኤሌክትሮንቮልት) ነበር።

CERN በሚል ምኅጻር የታወቀው፣ የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ጣቢያ፣ በተቻለ መጠን 7 ቴራኤልክትሮንቮልት ወይም አንድ ትሪሊዮን ኤሌክትሮቮልት በማመንጨት ለፍጥረተ-ዓለማት መከሠት ሰበብ እንደሆነ የሚነገርለትን ከዐቢዩ ፍንዳታ (ቢግ ባንግ)ጋር የሚስተካከል ድርጊት በምርምር ጣቢያ ለማሳየትና ፣ በዚሁም ውጤት አማካኝነት (ከ ቢግ ባንግ) ከዐቢዩ ፍንዳታ በኋላ ምን እንደተከሠተ፣ ምሥጢሩን ለማወቅ፣ የፍጥረተ-ዓለም ሥረ-መሠረት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለማግኘት ነው ጥረቱ!።

በኅዋ፣ ጽልመት የለበሰ ገዝፍ ያለው ነገርና ጽልመታዊ የኅይል ምንጭ የሚባለው፣ በፍጥረተ ዓለም ኮስሞስ፣ 96 % የሚሸፍነው ነገር ምንድን ነው? ከዚሁ፣ ከእኛ ኮስሞስ ሌላ ጎን ለጎን የሚገኝ፣ ስፋቱና ጥልቀቱ ያልታወቀ ነገር ይኖር ይሆን?ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ የ CERN የፊዚክስ ሊቃውንት መልሱን ማግኘት ይችሉ ይሆን? ለመስማትም ሆነ ለማወቅ ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን።

እ ጎ, አ በመስከረም ወር 2008 ዓ ም፣ ሥራውን የጀመረውና ወዲያው ባጋጠመው እንከን ሳቢያ ለአያሌ ወራት፣ እንደገና ዝግጅት በማድረግ ባለፈው ኅዳር 11 ቀን 2002 ዓ ም፣ የምርምር ሥራውን የጀመረው CERN፣ የምርምሩን ጣቢያ ለማደራጀት፣ በ 4,9 ቢልዮን ዶላር ወጪ፣ 20 ዓመት እንደወሰደበት ታውቋል።

በ CERN ምንድን ነው የሚካሄድው? ጥቂት ለማብራራት ባለፈው ዝግጅት ያልነውን እናስታውሳችሁ--

(ድምፅ)

መላው ዓለም፣ ፊቱን፣ ከትናንት በስቲያ በኮፐንሃገን ወደተከፈተው ዓለም-አቀፍ የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ ጉባዔ የመለሰ ሲሆን፣ በፕላኔታችን ህይወት ያላቸውን ፍጡራን ሁሉ ለመታደግ ሲሆን ፣ እስከ ታኅሳስ 9 ቀን 2002 ዓ ም፣ ምን ዓይነት ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል በግልጽ ባይታወቅም፣ በጉጉት በመጠበቅ ላይ መሆኑ የታወቀ ነው። የምድራችን የሙቀት መጠን ፣ በሰው ሠራሽ ጥፋቶች እጅጉን ቢባባስም ተፈጥሮም አልፎ-አልፎ በተለያየ መልክ በመጋልም ሆነ በመራድ በውስጧ ህይወት ባላቸው ፍጡራን ላይ ባለፉት ምዕተ-ዓመታት ያስከተለችው ድቀት፣ በሥነ-ፍጥረት ጠበብት በሰፊው የተመዘገበ መሆኑ እሙን ነው።

የዓለም የአየር ጠባይ ተመራማሪ ድርጅት ዋማና ጸሐፊ Michel Jarraud እንደገለጹት የአየር ጠባይ ፣ በሳይንሳዊ መልክ መጠናትና መመዝገብ ከጀመበት ከ 1850 ዓ ም ወዲህ እጅግ ሞቃት ከተባሉት ዓመታት መካከል አንዱ ፣ ሊያከትም 22 ቀናት የቀሩት ጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓ መተ-ምህረት ነው። ባለፉት 159 ዓመታት ውስጥ 2009 ፣ 5ኛው ሞቃት ዓመት መሆኑን ነው የአየር ጥናት ጠበብት የሚናገሩት።

የዓለም የአየር ጠባይ ተመራማሪ ድርጅት እንዳብራራው የፕላኔታችን አማካይ የሙቀት መጠን እ ጎ አ በ 1961 እና 1990 ዓ ም ከነበረው ፣ በአማካዩ በ0,4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ንሯል። ከ 2000-2009 የተለካው አማካኝ የሙቀት መጠን ፣ ከዚያ በፊት ከነበሩት ዐሠርተ-ዓመታት ጋር ሲነጻጻር፣ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ አላጠራጠረም።

ዘንድሮ፣ የዓለም የአየር ጠባይ ተመራማሪ ድርጅት እንዳለው፣ በአማካይ የሙቀት መጠን ቀዝቀዝ ብሎ የታየበት የዓለም ክፍል ሰሜን አሜሪካ ነው። ከዚህ አንጻር እስያና አፍሪቃ ግለት ሆኗል ያጋጠማቸው። በቻይና ከ 50 ዓመታት ወዲህ እጅግ አስከፊ የሆነ ድርቅ አጋጥሟል። ብርቱ ድርቅና ረሃብ በተለይ በምሥራቅአፍሪቃ መከሠቱ የታወቀ ነው። ባለፈው ሐምሌ ሚሸል ዣሮ፣ እንዳሉት ፣ በአውሮፓ አገሮች በጀርመን ጭምር ሐሩር ነበረ ያጋጠመው። በአንዳንድ አካባቢዎች፣ የሚከሠት እጅግ ሞቃትም ሆነ ቀዝቃዛ ወቅት፣ ለምድራችን የአየር ንብረት ለውጥ መለኪያ አይሆንም ። በአጠቃላይ ግን የምድራችን ግለት እየጨመረ መምጣቱን በየዘመናቱ የተመዘገቡ የሙቀት መጠኖች ያመላክታሉ አልፎ-አልፎ ብርቱ ቀዝቃዛ ወራት ሊያጋጥሙ ይችላሉ፣ ይሁንና ለምድራችን አማካይ የአየር ጠባይ ጠቋሚዎች አይደሉም። ከ 800,000 ዓመታት ወዲህ ከከባቢ አየር ጋር የተቀላቀለ አየር ክምችት ያጋጠመ በአሁኑ ዘመን ነው።

ስለቅዝቃዜ ካነሣን ፣ በተለይ በአውሮፓ እጅግ አደገኛ ርደት ያጋጠመው እ ጎ አ ከጥቅምት ወር 1708 ዓ ም አንስቶ እስከ ሚያዝያ ወር 1709 ዓ ም በዘለቁት 7 ወራቶች ነው። ያም፣ በ 10 ሺ ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ብርቱ ቅዝቃዜ እንደነበረ ነው የሚነገርለት። በመኖሪያ ቤቱና በጉዞ ላይ ያለቀው ሰው ሥፍር ቁጥር አልነበረውም። በብርቱ ቆፈን ሳቢያ፣ አፍንጫቸው፣ ጆሮአቸውን ያጡ ጥቂቶች አልነበሩም። ላሞችና ጥጆች፤፣ በየበረቱ በኃይለኛ ቅዝቃዜ ሳቢያ ተረፈረፉ። የዱር እንስሳትም እንዲሁ!እ ጎ አ በ 1708 በገና ሰሞን አየሩ ትንሽ ጋብ ቢልም፤፣ በጥር ወር መግቢያ ገደማ ላይ እንደደገና ብርቱ ቅዝቃዜ አጋጠመ። እ ጎ አ ጥር 9 ቀን 1709 ዓ ም፣ በርሊን ውስጥ ጧት በ 2 ሰዓት (ማለትም በመሃል አውሮፓ ሰዓት አቆጣጠር በ 8 ሰዓት)የሙቀቱ መጠን ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደነበረ መዝገቦች ያስረዳሉ። በዚያ \{ጨካኝ ክረምት» የሚል ተቀጥላ ስም በተሰጠው የክረምት ወቅት ራይን ፣ ኤልበ፣ ማይን፣ ቴምስ፣ ጋሮን፣ ሴን፣ ሌላው ቀርቶ የቬኔሲያ ከተማ ዳር ባህር ፣ ለብዙ ወራት ወደ ጠጣር በረዶ ተለውጦ ነበረ።

ፈረንሳይ ውስጥ ፣ በማርሴይ ከተማና በኢጣልያው ሊጉሪያ ግዛት መካከል ያለው የማዕከላዊው ባህር እምብርት ወደ በረዶ ተለውጦ ነበር። ከዚያም በጸደይ፣ አስፈሪ ማጥለቀለቅ ህዝቡን አስጨንቆ እንደነበረ ነው የሚነገረው። ዛፎችና አትክልቶች ከጥቅም ውጭ በመሆናቸው፣ አውሮፓ፣ በ 1709 ሞቃት ወራት፣ ሰኔ፤ ሐምሌና ነሐሴ፣ ታይቶ ባልታወቀ የረሃብ አለንጋ መገረፉንም የጥናት ሰነዶች ያረጋግጣሉ።

ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ