1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

‘ገንዱማ’ የሚፈትነው የኦሮሞ ፖለቲካ

ዓርብ፣ ጥር 17 2011

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ-ሸኔ) ሠላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ከመጣ ወዲህ ሥሙ ከርዕሰ ጉዳይነት ወርዶ አያውቅም። መሪው ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሥም የኢትዮጵያ ፖለቲካ “ወሬ ማጣፈጫ ነው” ይበሉ እንጂ፣ ጉዳዩ እርሳቸው እንደሚሉት የወሬ ጉዳይ ብቻ አይደለም።

https://p.dw.com/p/3C9zH
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ኃይሉ

ከትጥቅ አለመፍታት ጋር ተያይዞ ያለው እሰጥ አገባ ብቻ እንኳን የክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ኦነግ፣ እንዲሁም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ድርጅቶችም ጣልቃ እየገቡ ብዙ ምክክሮች እና ሥምምነቶች ቢደረሱም ችግሩን አልቋጩትም። የመጨረሻው ሥምምነት ትላንት (ጥር 16፣ 2011) በአባ ገዳዎች እና አደ ሲቄዎች እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ሽምግልና “ተፈትቷል” ተብሏል፤ ኦነግም ትጥቅ ፈትቶ ወደ ‘ካምፕ’ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ግን የውዝግቡ መጨረሻ ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይሆናል።

ሥሙ የከበደው ኦነግ

ኦነግ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ሥም ነው፤ ወይም ደግሞ ቢያንስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደዚያ ብንል ትክክል ነበር። የኦሮሞ ብሔርተኝነት ንቅናቄ ጀማሪ መሆኑ እና ከተመሠረተ ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በመንግሥት ተሳዳጅ መሆኑ ተጠቂ የነጻነት ታጋይ ተደርጎ እንዲሳል አድርጎታል። በሥሙ የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ተንገላትቷል ማለት ይቻላል፤ ብዙዎቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለእስር እና ስደት የተዳረጉት በኦነግ ሥም ነው። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ኦሮሞዎች ኦነግ መሳደዱን ካላቆመ እነርሱም እረፍት እንደሌላቸው ያውቁ ነበር። በዚህም ከየትኛውም ድርጅት የበለጠ ቅቡልነት ነበረው። ይሁን እንጂ ኦነግ በውስጥ ለውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተለየ አልነበረም። 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ኦነግ ወደ አምስት የተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍሏል። ሦስቱ ‘ኦነግ’ የሚለው ሥያሜ ላይ የተለያየ ቅጥያ ሲጨምሩ፥ ሁለቱ ግን ሙሉ ለሙሉ የተለየ አዲስ ሥም እየተጠቀሙ ነው። አሁን ትጥቅ ‘አልፈታም’ አለ በሚል ሥሙ በተደጋጋሚ የሚነሳው እና ከፍተኛ አቀባበል በአዲስ አበባ ተደርጎለት የነበረው ቡድን ‘ኦነግ-ሸኔ’ የሚባለው ነው። ይሁን እንጂ አቀባበሉ ለሥሙ እንጂ ለዚህ ቡድን የተለየ ዕውቅና መስጠት እንዳልሆነ ብዙዎች ሲናገሩ ይሰማል። ነገር ግን ልክ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታየው በአካባቢ የመከፋፈል ፈተና የኦነግ እና ሌሎችም የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያገጠጠ ችግር ሆኗል። ኦነግ-ሸኔ ለምሳሌ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው በወለጋ አካባቢ ብቻ እንደሆነ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይመሰክራሉ። ይህ ዓይነቱ የተለያዩ ድርጅቶች በተለያዩ አካባቢዎች ብቻ ተቀባይነት የማግኘት ጉዳይ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደሚሉት የኦሮሞን አንድነት (‘ቶኩማ’) ይጎዳል፤ መከፋፈሉንም ‘ገንዱማ’ ይሉታል። 

የምርጫ ምዝገባ ጉዳይ

የምርጫ ምዝገባ ጉዳይ ቀጣዩ የኦነግ የተለያዩ ክፍሎች የውዝግብ መንሥኤ እንደሚሆን መጠርጠር ይቻላል። ከአምስቱ የኦሮሞ ድርጅቶች ውስጥ እስካሁን ወደ ምርጫ ቦርድ ቀርቦ የተመዘገበ ድርጅት የለም። ይባስ ብሎ ዳውድ ኢብሳ “ከዚህ በፊት ተመዝግበናል” ብለው እንደዋዛ ማለፋቸው አሁንም ሌላ ውዝግብ እየመጣ እንደሆነ አመላካች ነው። በዚህ ሒደት ከውጭ ከገቡት ድርጅቶች አንዱ ኦነግ የሚለውን ሥም ይዞ መደበኛ ምዝገባ ቢያካሒድ እና ከሌሎቹ ቀድሞ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ቢያገኝ ከፍተኛ የሆነ እሰጥ አገባ መከሰቱ አይቀርም። ምክንያቱም በኦሮምያ ኦነግ የሚለውን ሥም ይዞ ለምርጫ መወዳደር ከፍተኛ ተቀባይነት ያስገኛል። እነዚህ የአግድም ውዝግቦች የቀጣዩ ምርጫ ቅድመ ሒደት ከመጀመሩ ቢያንስ አንድ ዓመት በፊት መጠናቀቅ ካልቻሉ ደግሞ ለምርጫው ሠላማዊነት ከፍተኛ አደጋ መሆኑ አይቀሬ ነው።

‘ገንዱማ’፦ የጎንዮሹ ፈተና

ከዚህ በፊት ለኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚፈትናቸው ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር የሚያደርጉት ትግል ነበር። ይሁንና አሁን የፖለቲካ ትግላቸው ከማዕከላዊ መንግሥቱ ፍረጃ እና ተሳዳጅነት በተላቀቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀድሞም የነበረው፣ ነገር ግን ቢያንስ በሌሎች ዘንድ በይፋ ያልተስተዋለው የእርስ በርስ ግጭት አዲሱ ጉልህ ፈተና ሆኖ ብቅ ብሏል። ይህን በወንዜ ልጅነት የመከፋፈል ፈተና ‘ገንዱማ’ ይሉታል። አሁን በእንቅስቃሴ ላይ ያሉት የኦሮሞ ድርጅቶች በአብዛኛው በአካባቢ ተከፋፍለዋል።

በኦሮሞ ትውፊት ውስጥ መከፋፈል የነበረ እንደሆነ የሚያረዳ ትርክት አለ። ሁለቱ የኦሮሞ ታላቅ ጎሳዎች ቦረናና ባሬንቱ ልጆች አንዳቸው ሌላኛቸውን ገድለዋል፣ በዚያም ምክንያት ‘ገንዱማ’ የእርግማን ውጤት ነው የሚሉ አፈታሪካዊ ትርክቶች አሉ። ይህንን ትርክት በማመንም ይሁን ባለማመን፣ የድርጅቶቹ የመከፋፈል መንሥኤ የፖለቲካ ፍልስፍና ችግር መሆኑ ላይ የፖለቲካ ልኂቃኑ ይኼ ነው የሚባል ጠንካራ ውይይት እያደረጉ አይደለም። 

በአብዛኛዎቹ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ዋነኛው መርሕ ብሔርተኝነት ትልቁ መርሕ እንደመሆኑ በአባላቱ ዘንድ ‘በኦሮሞነት’ መበላለጥ ያልተጻፈ ሕግ ይመስላል። ይሁን እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ብዛት፣ የአሰፋፈር ሁኔታ እና የሰፈረበት አካባቢ ስፋት፣ የሃይማኖት እና ሌሎችም የባሕላዊ ልምዶች ልዩነት በዚህ የብሔርተኝነት ቅኝት ውስጥ ብዙ ቦታ አልተሰጣቸውም። ስለሆነም ሁሉም የድርጅት መሪ የራሱን አካባቢ ሃይማኖት፣ ልምድ እና ባሕል የተሻለ የኦሮሞ መገለጫ አድርጎ ማመኑ እና ‘የበለጠ’ የመሆን ስሜት ማዳበሩ ለመከፋፈሉ ዋነኛ መንሥኤ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያለው የትግል ስሜት ድርጅቶቹ የውስጥ ችግሮቻቸውን እና ልዩነታቸውን በቅጡ እንዲፈትሹ ዕድል አልሰጣቸውም ነበር። አሁን መድረኩ ተከፍቶ ለውድድር ሲቀርቡ ከበፊቱ የበለጠ የመከፋፈል እና የእርስ በርስ መገዳደር ፈተና እንደሚገጥማቸው ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። 


በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።