1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ገደብ አልባው የኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት

ረቡዕ፣ ኅዳር 22 2008

የኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት የጊዜ ገደብ እንዳልተደረገለት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። የአውሮጳ አገራት አገልግሎቱ በአስራ ስምንት ወራት ተወስኗል በሚል የኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎች ማመልከቻን አንቀበልም እያሉ መሆኑን ተቋሙ ያወጣው ዘገባ ጠቁሟል።

https://p.dw.com/p/1HG32
Eritrea Präsident Isayas Afewerki
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

የኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት ባለመገደቡ ወደ አውሮጳ የሚደርሱ የአገሪቱ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ስደተኞች ሊባሉ እንደማይገባ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። ድርጅቱ ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዘገባ የተገን ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ ወደ ኤርትራ የሚመለሱ ስደተኞች የእንግልትና ስቃይ ይጠብቃቸዋል ሲል አስጠንቅቋል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪቃ አጥኚ የሆኑት ክላይር ቤስተን የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎትን ለመገደብ የገባውን ቃል አላከበረም ሲሉ ይናገራሉ።

«በ2014 ዓ.ም. መገባደጃ የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ሰዎችን በብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ ማሰማራት እንደሚቀር አስታውቀው ነበር። የብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት አስራ ስምንት ወራት ብቻ ይሆናል ብለውም ነበር። ነገር ግን ይህ ዘገባ ምንም አይነት ለውጥ አለመኖሩንና የኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት የጊዜ ገደብ እንደሌለው ሰዎች ከ15 እስከ 20 አመታት በዝቅተኛ ክፍያና የሥራ ሁኔታ ለመቆየት እንደሚገደዱ ይፋ አድርጓል። እረፍት አይሰጣቸውም። አንዳንዶቹ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ይሄዳሉ። »
በተ.መ. የስደተኞች መርጃ ድርጅት መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም መገባደጃ በየወሩ 5,000 ኤርትራውያን አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። በዚያው አመት በኅዳር ወር ወደ አውሮጳ ከደረሱ ኤርትራውያን መካከል 90% እድሜያቸው 18-24 ነበር።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ያወጣው ዘገባ በምስራቅ አፍሪቃዊቷ አገር ያለው ነባራዊ ሁኔታ መሻሻል ባላሳየበት ሁኔታ የአውሮጳ አገራት የኤርትራ ስደተኞችን ተገን እየከለከሉ መሆኑን አትቷል።ሁኔታውን አሳሳቢ ያሉት ክላይር ቤስተን የአውሮጳ አገራት በኤርትራ ያለው ነባራዊ ሁኔታ አለመሻሻሉን ይናገራሉ።

«ኤርትራውያን ተገን ከሚጠይቁባቸው አገራት መካከል የተወሰኑት በአገሪቱና በብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት መሻሻል እንዳለ ለመጠቆም እየሞከሩ ነው። ለምሳሌ ባለፉት ስድስት ወራት የብሪታኒያ መንግስት ከኤርትራውያን ከቀረበለት የተገን ማመልከቻ 64% አልተቀበለም። እነዚህ መንግስታት ተሳስተው ኤርትራውያኑን የኢኮኖሚ ስደተኞች ናቸው እያሉ ነው። በኤርትራ ያለው ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት በግዴታ የሚደረግ ነው። ሰዎችን ለሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያጋልጣል። ይህን የሚሸሹ ሰዎች የፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ ስደተኞች አይደሉም።»
በአሁኑ ዘገባ ላይ የኤርትራ መንግስትን አስተያየት ለማካተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም። ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት አስፈላጊነት ከዚህ ቀደም ጥያቄ የቀረበላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በምክንያትነት ያቀርባሉ። ክላይር ቤስተን ለጥናቱ ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች በኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት ያለፉበትን አስከፊ ሂደት መገንዘባቸውን ይናገራሉ።
«ቃለ-መጠይቅ ያደረግንላቸው በሙሉ ከብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት ለመሸሽ አሊያም ከስርዓቱ ለማምለጥ ከአገሪቱ ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘው ያለምንም ክስና የፍርድ ሂደት ታስረዋል። በመሬት ውስጥ የሚገኙ እስር ቤቶችን ጨምሮ በእቃ ማጓጓዣ ኮንቴነርና የቤት እስረኛ ነበሩ። አንዳንዶቹ እንግልትና ስቃይ እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል። በብሄራዊ የውትድርና አገልግሎቱ ውስጥ ሲቪል ሰራተኞ ሊሰሯቸው የሚችሉ ስራዎችም ይገኛሉ። በመንግስት እርሻዎች፤የግንባታ ስራዎች፤መምህርነት፤የመሰረተ-ልማት ግንባታ ጭምር ማለት ነው።»
የኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎትን ለማስቆም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ላለው ፍጥጫ እልባት ማበጀት አንደኛው መፍትሔ መሆኑን ክላይር ቤስተር ተናግረዋል። ይህ ለጊዜው የሚሆን አይመስልም።
ኤርትራ ዜጎቿን ለስደት በከፍተኛ ደረጃ እየዳረገ የሚገኘውን የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ማቆም ይገባታል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አስተላልፏል። የአውሮጳ አገራትም ለኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎችን ማመልከቻ በጥንቃቄ እንዲመለከቱ ክላይር ቤስተር ተናግረዋል። ተገን ጠያቂዎቹ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎትን ሸሽተው ወደ መጡበት ኤርትራ ሊመለሱ አይገባም ያሉት አጥኚዋ ዓለም አቀፍ ከለላ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። የኤርትራን የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ማንኛውም ዜጋ በምንም አይነት ምክንያት መቃወም አሊያም በሲቪል አገልግሎት መተካት እንደማይችል ዘገባው ጠቁሟል። ከ16 ዓመት ታዳጊ ጀምሮ እስከ አረጋውያን ድረስ የሚያካትተው ይህ አገልግሎት የሚከፈለው ወርሃዊ ክፍያ 30 ፓውንድ አካባቢ ብቻ ነው ተብሏል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ

Flüchtlinge Eritrea
ምስል AP
Schweden Ankunft Flüchtlinge aus Eritrea
ምስል picture-alliance/dpa/R. Nyholm