1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጉግልና ጤና

ረቡዕ፣ ኅዳር 22 2008

በጎርጎሮሳዊው 1995ዓ,ም መጋቢት ወር በሁለት ተማሪዎች መረጃ የመፈለግ ሂደት የተመሠረተው ጉግል የተሰኘዉ በኢንተርኔት መረጃ መፈለጊያ ኩባንያ የሚሠራቸው የጥናትና ምርምር ዘርፎች ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ነዉ። ኩባንያው አዲስ እቅዱ በሽታን አስቀድሞ መከላከል እና እርጅናን ማዘግየትን ጨምሮ በርካታ ምርምሮች ላይ አተኩሯል።

https://p.dw.com/p/1HG3X
Google Logo Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/O. Spata

ጉግልና ጤና

ጉግል ምንድነው?

ኩባንያው የተሠማራባቸው የሥራ ዘርፎች ብዛትና ውስብስብነት ይህን ጥያቄ ለመመለስ አስቸጋሪ ያደርገዋል። መኪኖች፤ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና የመኖሪያ ቤት ቁሳቁሶች... አሁን ደግሞ ወደሰዉ ልጅ የሰውነት አካል ተሻግሯል።

መቀመጫውን በካሊፎርኒያ ማውንቴንቪው ያደረገው የጉግል ኩባንያ ‘የህይወት ሳይንስ ቤተ-ሙከራ (Life Sciences labs) ሲል የጠራው አዲሱ እቅድ ሰዎች ወደ ፊት የሚገጥሟቸውን ህመሞች መተንበይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ቶማስ ሹልዝ ህመሞችን አስቀድመው ለመከላከል ታቅደው የተሠሩትን የህክምና ቁሳቁሶች ተመልክቷቸዋል። መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ አድርጎ ዴር ሽፒግል ለተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ይዘግባል። እንደ ቶማስ ሹልዝ ከሆነ ከጉግል ኩባንያ አስደናቂ ግኝቶች መካከል አንዱ በደቂቅ አካላት (nanoparticles) የተሞላው እንክብል እንደሆነ ይናገራል።

«አንድ እንክብል ከወሰድክ በኋላ እንክብሉ በሰውነታችን ውስጥ የተወሰኑ ፍተሻዎችን/ልኬታዎችን ያካሂዳል። ከዚያ በእጅ ላይ የሚታሰር ሌላ መሣሪያ ውጤቱን ያነበዋል። ይህ በሚቀጥሉት ጊዜያት የጤና ሁኔታህን በበርካታ መንገድች ለመተንተን የሚያስችል እድል ይሰጣል የሚል እምነት አላቸው። ምን አልባት በመጪዎቹ ጊዜያት ድንገተኛ ህመም ሊገጥምህ ይሆናል። ነገር ግን አታውቀውም።»

Google Gründer Sergey Brin mit Google Brille Archivbild
የጉግል ተባባሪ መስራች ሰርጌ ብሪንምስል Reuters

የጉግል ኩባንያ በዓይን ላይ የሚለጠፉ ሌንሶች (contact lenses) በሰውነት ውስጥ የሚገኝ የጉሉኮስ መጠንን መለካት በሚችሉበት ዘዴ ላይ እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው ከዓመት በፊት ነበር። የዚህ እቅድ ኩባንያው በጤና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ የተመራማሪዎች ቡድን ለማቋቋም መነሻ ሆኖ የህይወት ጤና ቡድን ተመሠረተ። ይህ በጉግል አዲሱ አደረጃጀት የአልፋቤት ኩባንያ አንድ የሠራ ዘርፍ ሆኗል።

የዓይንን የማየት አቅም ለማገዝ ተሠርተው በዓይን ብሌን ላይ የሚለጠፉት ሌንሶች በሃሳብ ደረጃ ቀድመው ከነበሩት ተመሳሳዮቻቸው የተለዩ በመሆናቸው ተግባራዊነታቸው አጠራጣሪ ይመስል ነበር። ሃሳቡ ሰዎች ከታመሙ በኋላ ከማከም ይልቅ አስቀድሞ እንዳይታመሙ መከላከልን ያቀደ ነው። ኖቫርቲስ ከተሰኘ የጤና ክብካቤ ኩባንያ ጋር በጥምረት የተጀመረው ሥራ ለገበያ ባይበቃም ግን ወደ ተግባር ተሸጋግሯል። በዓይን ላይ የሚለጠፉት ሌንሶች በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የጉሉኮስ መጠን በመከታተል መጠኑን መለካት ወደሚችል መሣሪያ በገመድ አልባ ቴክኖሎጂ ያሸጋግራል። አሁንም -ቶማስ ሹልዝ፤

«በዓይን ላይ የሚለጠፉት ሌንሶች ለስኳር ህሙማን የተዘጋጀ ነው። የሰውነት የስኳር መጠንን ለማወቅ ሁል ጊዜ መርፌ መጠቀም አያስፈልግም ማለት ነው።»

አሁን የቴክኖሎጂዎቹ ግኝት አስደሳች ቢሆንም ጉግል በህክምናው ዘርፍ ምን ሊሠራ አቅዷል? የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ለነገሩ በጤናው ዘርፍ በመሠማራት የጉግል ኩባንያ ብቸኛው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አይደለም። ለምሳሌ የአፕል ሰዓቶችና አይፎን እንዲሁም ማይክሮሶፍት የጤና መረጃ ይመዘግባሉ፤ እንዲሁም ይተነትናሉ። ጉግል የሚሠራቸው የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ወደ ህክምና ማዕከላት ደርሰው በተግባር ለህሙማን ግልጋሎት ከመስጠታቸው በፊት በአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ከጉግል ኩባንያ መሥራቾች አንዱ ሰርጌ ብሪን ከ50 እስከ መቶ አመታት ወደ ፊት ቀድሞ መመልከት የሚፈልግ ነው ይባልለታል። ከምሥረታው ጀምሮ በኢንተርኔት ቴክኖሎጂና አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ የቆየው ጉግል ኩባንያ አሁን እጅግ ተለጥጧል። በውስጡ የሚሠራቸው ቴክኖሎጂዎችና ምርምሮች ገዝፈዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች የሰው ልጅ የጤና ችግሮችን ለመፍታት ተመሳሳይ ጥናትና ምርምሮች ያደርጋሉ። ጉግል ግን ቀድሞ ዝናን ካተረፈበት እና ትርፋማ ከሆነበት የኢንቴርኔት የቴክኖሎጂ በተጨማሪ በጤናው ዘርፍ ስኬታማ መሆን አቅዷል። እንደ ቶማስ ሹልዝ ከሆነ ዘርፉን በኮምፒውተር ሳይንስ ዘርፍ ወደ ፊት ሊያራምደው ጉግል አቅዷል።

Google I/O 2013 San Francisco
የጉግል ተባባሪ መስራች ላሪ ፔጅምስል Getty Images

« መድኃኒት በኮምፒውተር ሳይንስ ወደ ፊት የሚራመድ አዲሱ ዘርፍ መሆኑን ጉግል ያምናል። ከመድኃኒት ጋር የተገናኙ ማናቸውም ነገሮች በመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ቁጥጥር ውስጥ መሆናቸው ይቀራል ማለት ነው። ለኮምፒውተር ኩባንያዎች በዚያ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ እድል አላቸው። ኩባንያዎቹ በዘርፉ በርካታ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመቶ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች ቀጥረዋል። የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግም ይችላሉ።»

በመድኃኒትና የህክምና ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረውን እቅድ አንዲሪው ኮንራድ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ይመሩታል። ሥራ አስፈጻሚው የሚመሩት ቡድን ከሳይኮሎጂ፤ ባዮኬሜስትሪ እና ሞለኪዩላር ባዮሎጂ የተውጣጡ ሳይንቲስቶችን ጭምር ያካትታል። አንድሪው ኮንራድ ከአስር አመታት በፊት በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ካሮላይና በዴቪድ ሙድሮክ ባለቤትነት የሚተዳደር ተመሳሳይ የመድኃኒት የምርምር ተቋምን በበላይነት ይመሩ ነበር። ጉግል በጥናትና ምርምር ድረ-ገጹ እንዳሰፈረው የፊዚክስ፤ ማቲማቲክስ፤ የእንስሳት በሽታዎች ጥናት ልሂቃንን ያካተተው የአንድሪው ኮንራድ ‘የህይወት ሳይንስ ቤተ-ሙከራ’ አንድ ቀን ካንሰርን የመፈውስ አቅም እንደሚያጎለብት ተስፋ ተደርጓል። ተስፋቸውም ሆነ ትኩረት ያደረጉባቸው ህመሞች ግን ጥቂት አለመሆናቸውን ቶማስ ሹልዝ ይናገራል።

«የጥቂት መቶ ሺ ሰዎች ችግር የሆኑ ህመሞችን መርጠው ትኩረት እንደማያደርጉ ተናግረዋል። ምንም ነገር ሲያደርጉ ቢያንስ ለአንድ ቢሊዮን ሰዎች የሚጠቅም መሆን ይኖርበታል። ይህ ሁሉንም ሥራዎቻቸውን የተመለከተ ነው። ይህ ደግሞ በጤናና መድኃኒት ዘርፍ የጀመሩትንም ያካትታል።»

ሌላው መንገድ

ጉግልም ይሁን አልፋቤት በጥቂት ቤተ-ሙከራዎችና በመቶዎች በሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች የዓለም የጤና ችግርን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀርፉት ይናገራሉ። በህክምናው ዘርፍ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮችን ለማበረታት የሳይንስ እና ሳይንቲስቶችን ማበረታታት ሌላው አማራጭ ሆኗል። ለዚህ ስኬት ደግሞ ዘ ብሬክ ስሩ (the Breakthrough Prize) የተሰኘ ሽልማት ተዘጋጅቷል።

የጉግል ተባባሪ መሥራች ሰርጌ ብሪን እና የቀድሞ ባለቤቱ አን ዎጄሲስኪ የዚህ ሽልማት ሃሳብ አመንጪዎች መስራቾችም ናቸው። ሽልማቱ የሳይንስ ኦስካር የሚል ስያሜም አትርፏል። በሰው ህይወት፤ መሠረታዊ ፊዚክስ እና ማቲማቲክስ ዘርፎች አመርቂ አስተዋጽዖ አበርክተዋል ብሎ ለመረጣቸው ባለሙያዎች 22 ሚሊዮን ዶላር ይሸልማል። የሽልማት ስርዓቱ በቀይ ምንጣፍ በተንቆጠቆጠ አዳራሽ አሉ የሚባሉ የክብር እንግዶች በተገኙበት የሚካሄድ ነው።

ይህ ሽልማት ከተበረከተላቸው ተመራማሪዎች መካከል ጆን ሃርዲ አንዱ ናቸው። ጆን ሃርዲ በአልዛይመር ወይም የመዘንጋት በሽታ ተከከታታይ ጥናቶች ሠርተዋል። አንድ ማለዳ ከቁርስ ጠረጴዛቸው ላይ ቁጭ ብለው የደረሳቸው የስልክ ጥሪ ነበር አሸናፊነታቸውን ያበሰራቸው። በሽልማቱ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም 2.8 ሚሊዮን ዩሮ አግኝተዋል።

«ለሽልማቱ እንደታጨሁ እንኳ የማውቀው ነገር አልነበረም። ማሸነፌን ያወኩት በደረሰኝ የስልክ ጥሪ ነው። አስቤው የማውቀው ነገር አልነበረም። ለእኔም ሆነ ለምሠራበት ተቋም ጥሩ አጋጣሚ ነው። ለጥናትና ምርምራችን የሚያገለግል ህንጻ ለማስገንባት ገንዘብ እያፈላለግን ነበር።»

Porträt - Professor John Hardy
ፕሮፌሰር ጆን ሃርዲምስል Rolf Eckel

የጎግል መሥራቾች ከአልፋቤት መመሥረት በኋላ ለህይወት ሳይንስ ቤተ-ሙከራ የሚያወጡት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ሰርጌ ብሪን በግልና በከፍተኛ ትኩረት በሚከታተለው ዘርፍ የጀመረውን ሽልማት የሚያካሂደው ግን በግል ነው። ሰርጌ ብሪጅም ይሁን ላሪ ፔጅ ትርፋማ የህክምና ቁሳቁሶችን በፍጥነት ወደ ገበያው ለማስገባት በመሥራት ላይ ናቸው። ሰለሞን ካሳ ጉግልም ይሁን ተመሳሳይ ኩባንያዎች የሚሠሯቸው የምርምር ሥራዎች እጅግ የራቀቁ መሆናቸውን ይናገራል።

የጎግልን ምኞት የተመለከተ መጽሐፍ ለጻፈው ቶማስ ሹልዝ አሁን አልፋቤት የተሰኘ ግዙፍ ኩባንያ ላይ የደረሰው የላሪ ፔጅ ስርጌ ብሪን እቅድ ከዚህም በላይ ነው።

«መጀመሪያ ለሁለት አመታት ሳይሆን ለሚቀጥሉት 50 ወይም 100 አመታት እጅግ ጠቃሚና ስኬታማ ኩባንያ መሆን ይፈልጋሉ። ይህ በተለየ ደረጃ ሥራን ለማከናወን ያግዛል። ሁለተኛ በአጠቃላይ በሰው ልጅ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይፈልጋሉ። ለዚህም ቁርጠኛ ናቸው። ማስታወቂያ አይደለም። ከምር ዓለምን መቀየር ይፈልጋሉ።»

ሰለሞን ካሳ ጉግል በተሰማራባቸው የሥራ ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በገንዘብ አቅሙም እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል። ኩባንያው በሙከራ ሥራ የጀመራቸው እቅዶች ደግሞ አስደናቂ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ