1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጊኒ ቢሳው፣ የመፈንቅለ መንግሥቱ 1ኛ ዓመት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2005

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጊኒ ቢሳው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር የጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግሥት አስወግደው ከጥቂት ቀናት በኋላ መደረግ የነበረበትን ሁለተኛ ዙር ወይም የመለያውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሰረዙት።

https://p.dw.com/p/18F7p
uምስል DW

በዚያን ወቅት ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቶ  የነበረው የዚቹ አፍሪቃዊት ሀገር ውዝግብ የአንሳር ዲን አክራሪ ሙሥሊሞች እና የቱዋሬግ ዓማፅያን የማሊን ሰሜናዊ ከፊል በተቆጣጠሩበት ድርጊት የመረሳት ዕጣ ገጥሞታል። የጊኒ ቢሳው ጊዚያዊ ሁኔታ ግን፣  አሁንም አሳሳቢ እንደሆን ይገኛል።       

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ካርሎስ ጎሜሽ ጁንየር መፈንቀለ መንግሥቱን ያካሄዱት ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ዓማፅያኑ የጦር ኃይሉ አባላት 12. 04.2012ምሽት ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ የወሰዱትን የኃይል ተግባር ከሥልጣን ከተወገዱ ከጥቂት ቀናት በኃላ ለዶይቸ ቬለ እንዲህ ነበር የገለጹት።

Guinea Bissau Afrika PAIGC
ምስል DW

„ መኖሪያ ቤቴን በጠቅላላ አውድመው የሚዘረፈውን ዘርፈዋል። አልከፈት ያላቸውን ደግሞ በጥይት ሰባብረዋል። ይኸው ድርጊታቸው በፊልም እና በፎቶግራፍ ተቀርፆ ተይዞዋል። በአንድ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ፍትሕ ሊኖር ይገባል ብዬ ስለማስብ በዚህ አንፃር ክስ እመሠርታለሁ። እነዚህ ሰዎች ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ ለማድረግ እጥራለሁ።     „

በመጀመሪያው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ 49 ከመቶ የመራጩን ድምፅ ያገኙት ካርሎስ ጎሜሽ ጁንየር መፈንቅለ መንግሥቱ ባይካሄድ ኖሮ በመለያው ምርጫ ጥሩ የማሸነፍ ዕድል ነበራቸው። በዚያን ጊዜ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት ካርሎስ ጎሜሽ በሀገሪቱ የተወሰነ መረጋጋት እና ኤኮኖሚያዊ ዕድገት በማስገኘታቸው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ።

ያም ቢሆን ግን ከጦር ኃይሉ ትልቅ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር። በጊኒ ቢሳው ደግሞ ካለ ጦር ኃይሉ ፍላጎት በሀገሪቱ የሚንቀሳቅስ ነገር የለም።  ካርሎስ ጎሜሽ ልክ እንደ ጊኒ ቢሳው የፖርቱጋልኛ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆነችው አንጎላ ጋ በመተባበር የሀገራቸውን ጦር ኃይል በዘመናይ ዘዴ እነደገና ለማዋቀር  የጦር መኮንኖችን ቁጥር ለመቀነስ እና በሲቪሉ ኮማንዶ ዕዝ ሥር ለማዋል ዕቅድ ነበራቸው።     ጎሜሽ ጁንየር ተሳክቶላቸው ታመው የሞቱትን ፕሬዚደንት ማላም ባካ ሳናን ተክተው ቢሆን ኖሮ  የጦር ኃይሉን ሥልጣን ለመቀነስና  ከደቡብ አሜሪካ ሕገ ወጥአደንዛዥ ዕፅ ቡድናት ጋ የሚያካሂዱትን ንግድ ለማብቃት ከፍትኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ዝተው ነበር።  ጎን በዚህ ፈንታ ያጋጠማቸው እስራትና በኋላም ወደ ቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ሀገር ፖርቱጋል ተሰደዱ።

Carlos Gomes Junior
ካርሎስ ጎሜሽ ጁንየርምስል DW/João Carlos

ከዚያ ዓማፅያኑ በሥልጣን ላይ በቆየው PAIGC ፓርቲ ፈንታ በሲቭሉ ግን በዴሞክራሲያዊ ዘዴ ያልተዋቀር የሽግግር መንግሥት አቋቁሞዋል፤ ግን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተከናወነ ነገር የለም፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ይደረጋል የተባለው ምርጫም እስካሁን ገሀድ አልሆነም። በዚህም የተነሳ የኖቤል ሰላም ተሸላሚ እና የተመድ የጊኒ ቢሳው ልዩ ልዑክ የቀድሞው የምሥራቅ ቲሞር ፕሬዚደንት ኾዜ ራሞስ ሆርታ ምርጫው ባፋጣኝ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

„ ምርጫው እስከዚህ አውሮጳዊ ዓመት መጨረሻ መደረግ አለበት። ከዚህ ሌላም ባፋጣኝ ማለትም በዚህ በተያዘው የሚያዝያ ወይም በቀጣዩ ግንቦት ወር ከሰፊው የሕዝብ ክፍሎች የተውጣጣ እና በይበልጥ ሕጋዊ የሆነ የሽግግር መንግሥት መቋቋም ይኖርበታል። ከዚያ ይኸው መንግሥት የምርጫውን ሂደት ሊያዘጋጅ ይችላል። ለምርጫ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እና ቁሳቁስ ማዘጋጀቱ የሚከብድ አይደለም። አዳጋች የሚሆነው ፖለቲካዊው ሂደት ነው።    “

በጊኒ ቢሳው በመፈንቅለ መንግሥት ለተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ዕውቅና የሰጠው ብቸኛው ቡድን፣ ማለትም፣ የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ፣ በምሕፃሩ ኤኮዋስም የተያዘው አውሮጳዊ ዓመት 2013 ሳያበቃ በፊት እንዲደረግ አሳስቦዋል። ይሁንና፣ ምርጫ ብቻውን የጊኒ ቢሳውን ችግር ሁሉ ያቃልላል ብለው እንደማያስቡ በምሕፃሩ ኢፕሪስ በመባል የሚታወቀው የፖርቱጋላውያኑ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተቋም ተንታኝ ፓውሎ ጎርኻዮ ገልጸዋል።

„ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት መልሶ ማረጋገጡ ብቻውን አይበቃም፤ ምንም እንኳን ይህ በጣም አስፈላጊ ሂደት ቢሆንም። ሀገሪቱን ወደፊት አላራምድ ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሔ መሻቱ የግድ ነው። ማንም ግለሰብ፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያለው ሁሉ ችግሮቹ የትኞቹ መሆናቸውን በግልጽ ያውቃል። የመጀመሪያው በጦር ኃይሉ ውስጥ ተሀድሶ ማድረግ ሲሆን፣ ሌላው በሕገ ወጡ አደንዛዥ ዕፅ አንፃር ጠንካራ ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ፖለቲካ መከተል ይሆናል። “

 ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጊኒ ቢሳው በላቲን አሜሪካ እና በአውሮጳ መካክል  በሚካሄደው የሕገ ወጡ አደንዛዥ ዕፅ ንግድ ላይ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። ሰሞኑን እንደተሰማው፣ የዩኤስ አሜሪካ ጠረፍ ጠባቂዎች ባለፈው ሚያዝያ ሁለት 2013 ዓም የቀድሞውን የጊኒ ቢሳውን የባህር ኃይል መሪ ኾዜ አሜሪኮ ቡቦ ና ቹቶን በኬፕ ቬርዴ ደሴቶች አቅራቢያ በሕገ ወጡ አደንዛዥ ዕፅ ንግድ ሰበብ አስረው ለዩኤስ አሜሪካ አስረክበዋል።

ዮሐንስ ቤክ/አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ