1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋምቤላ፤ ቢያንስ 140 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8 2008

ጋምቤላ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ ሰዎች ዐርብ ሚያዝያ 7 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ተገደሉ። የኑዌር ጎሳ አባላት የመኖሪያ መንደሮች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ221 በላይ መሆኑን ሱዳን ትሪቡዩን ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1IX5G
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በጥቃቱ ሴቶች እና ህጻናት ጭምር መገደላቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የጽ/ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሰዒድ ጥቃቱ መፈጸሙን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥቃት አድራሾቹ ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል።

ሱዳን ትሪቢዩን የደቡብ ሱዳን ጦር መለዮ የለበሱ እና የታጠቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የተደራጁ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር በማቋረጥ በዐሥር መንደሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ዘግቧል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ በደቡብ ሱዳን የቡማ ወይም ጆንጊሌ ግዛት የሚገኙት የሙርሌ ጎሳ አባላት መሆናቸውንም አትቷል። በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 221 መድረሱን የዘገበው ሱዳን ትሪቢዩን 170 የኔዌር ጎሳ አባላት እና 51 የሙርሌ ጎሳ አባላት መገደላቸውን አትቷል። ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን የታጣቂዎቹ ማንነት እንደማይታወቅ እና «መከላከያ ሰራዊት ጭፍጨፋውን የፈጸመው ቡድን ላይ ተከታትሎ አርምጃ እየወሰደ መሆኑን ዘግበዋል። እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ