1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋና ፣ ለአፍሪቃ የዴሞክራሲ አርአያ፣

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2001

ጋና ውስጥ፣ በተካሄደው የፕሬዚዳንትነት ምርጫ፣ የተቃውሞው ወገን መሪ ፣ ጆን አታ-ሚልስ፣ እንደ መቅድማዊው ምርጫ፣ የመጨረሻውን ወሳኝ ምርጫም ከ 9 ሚልዮን መራጮች መካከል በ 40,000 ድምፅ ሰጪዎች ብልጫ ለማሸነፍ መብቃታቸው በአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ተረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/GSVF
የተቃውሞው ወገን እጩ ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረብ ፣ የጋናውን ምርጫ ያሸነፉት አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆን አታ ሚልስ፣ምስል AP

ጋና ሰላማዊ ምርጫ ከማካሄዷም ዴሞክራሲዋ መደላደሉን በማስመሥከሯ፣ አርአያነት ያለው ተግባር አከናውናለች ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን አስታወቁ። የጋናውን የምርጫ ሂደት ያደነቁ የአፍሪቃ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ግለሰቦችም አልታጡም። ----ተክሌ የኋላ ዝርዝር ዘገባ አለው።

(ድምፅ)------

«ክቡራትና ክቡራን በተሰጠው ይፋ የምርጫ ውጤት መሠረት፣ በተሰጠኝ ኀላፊነት ፣ ፕሮፌሰር ጆን አታ ሚልስ ፣ ፕሬዚዳንት ይሆኑ ዘንድ መመረጣቸውን አውጃለሁ»።

ይህን ያሉት የጋና የምርጫ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት አፋሪ ጃን ናቸው።

2ኛ የአገልግሎት ዘመናቸውን ፣ በአጠቃላይ 8 ዓመት የሥልጣን ጊዜያቸውን በመጨረሳቸው ፣ ፓርቲያቸውን በመወከል ናና አኩፎ አዶ እንዲወዳደሩ ያደረጉት፣ በአፍሪቃ እጅግ ከተከበሩት ጥቂት መሪዎች መካከል አንዱ ፕሬዚዳንት ጆን ኩፉር፣ ከነገ በሰቲያ ሥልጣኑን ለአሸናፊው ጆን አታ ሚልስ በሥነ ሥርዓት ያስረክባሉ። በጋና ነጻ የመድበለ ፓርቲ ምርጫ ሲካሄድ ያሁኑ 5ኛ ነው። በጋና ለመጀመሪያ ጊዜ በነጻ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ የሥልጣን ዝውውር የተደረገው፣ የቀድሞው ወታደራዊ መሪ፣ የአየር ኃይል አብራሪ መቶ አለቃ ጀሪ ሮውሊንግስ፣ እ ጎ አ በ 2000 ዓ ም ሥልጣን ለጆን ኩፉር እንዳስረከቡ ነው። በአሁኑም ምርጫ ፣የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት

ክጋሌማ ሞትላንቴ፣ እንዳሉት ፣ ጋናውያን ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር አክብሮት እንዳላቸው አሥመስክረውበታል። ደቡብ አፍሪቃ ራሷ በመጪው ሚያዝያ ወር ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን ፣ ገዥው ፓርቲ ከሁለት የተከፈለ እንደመሆኑ መጠን፣ ውድድሩ እንደሚያይል ይታሰባል። ከአንድ ዓመት በፊት በምርጫ ሳቢያ፣ ገና ውጤቱ መቆጠር እንደጀመረ ተሽቀዳድመው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ «አሸንፌአለሁ» ሲሉ በመግለጣቸው የጎሣ ግጭት ተከሥቶባት የነበረችውና በመጨረሻ ለውዝግቡ በሽምግልና መፍትኄ ያገኘችው የኬንያ ጠ/ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ፣ «የ ጆን አታ ሚልስ ድልና የጋና ህዝብ ጨዋነት ዴሞክራሲ በአፍሪቃ መሥራት እንደሚችል ያሳየ ብርቅና አርአያነት ያለው ክንዋኔ ነው» ብለዋል። ፕሬዚዳንት ጆን ኩፉር ፣ ለምርጫው የቀረቡት የተወዳደሩት ሁለቱ ተወዳዳሪዎች፣ የምርጫውን የመጨረሻ ውጤት እንዲያከብሩ በማሳሰባቸውም ጨዋ የሀገር መሪ ተብለው በጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ተወድሰዋል። በጋና የናይጀሪያ አምባሳደር ሙሲሉ ኦባኒኮሮ፣ «ተስፋ የማደርገውና የምጸልየው፣ የምርጫው ውድድር፣ የተካሄደበት መንፈስና ውጤቱ፣ በጋና ብቻ ሳይሆን በምዕራብ አፍሪቃም እንዲዛመት ነው» ብለዋል። ከጋራ ንብረት (ኮመንዌልትዝ)አገሮች የምርጫ ታዛቢዎችን የመሩት የብሪታንያዋ ተወላጅ ወ/ሮ ቫሌሪ አሞስ ፣ «የምርጫው ሂደት በአጠቃላይ፣ ተዓማኒነት ያለበት ነው ሲሉ ያገሪቱ ዜጎችም የ ምርጫውን ሂደት እስከ ውጤቱ አድንቀዋል።

ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ አንስቶ ነጥረው የወጡ አከራካሪ ጉዳዮች የትኞቹ እንደነበሩ፣ ከዚህ ቀደም በኅዳር ወር መጨረሻ ገደማ ላይ አክራ ውስጥ የምርጫውን ሂደት በመከተታል ላይ የነበረውን የሃውሳውን ከፍል ባልደረባ ቲጃኒ ላዋልን ያኔ ጠይቄው እንዲህ ሲል ማብራራቱ የሚዘነጋ አይደለም።

(ድምፅ)--------------