1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግሎሪያ እና የመረጃዉ አደን

ዓርብ፣ ጥር 29 2007

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ከተቋቋመ አንስቶ በተለያዩ ሃገራት የፈጸሙ የዘር ማጥፋትና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን በመከታተል አጥፊዎች በነፃ መንቀሳቀሳቸዉ እንዲያከትም ለማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/1EXRe
Gloria Atiba-Davies
ምስል Sonja Heizmann

እንዲህ ባሉ ወንጀሎች የተሳተፉና ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብም እንደግሎሪያ አቲባ ዳቪስ ያሉ የወንጀል መርማሪዎች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች፣ እልም ወዳሉ የገጠር መንደሮችና በዓለም ላይ አደገኛ ወደተባሉ ስፍራዎችም ሳይቀር መረጃዎችን ለማደን ተጉዘዋል።

ግሎሪያ አቲባ ዴቪስ በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ICC በተለይ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችና ልጆችን ጉዳይ የሚከታተለዉ ክፍል ኃላፊ ናቸዉ። ግሎሪያ ለ18 ዓመታትም በሀገራቸዉ ሴራሊዮን በአቃቤ ሕግነት አገልግለዋል። ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዉስጥ ስለተፈፀመ ወንጀል የዛሬ ስድስት ዓመት እማኞችን ለማግኘትና መረጃ ለማሰባሰብ ያደረጉትን ያስታዉሳሉ።

Internationaler Strafgerichtshof mit Logo
ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2009 ዓ,ም በዚህች ሀገር የተፈፀመዉ ጉዳይ ለ ICC ቀርቧል። በዚሁ የዘመን ቀመር በ2002 ማለቂያና እና 2003 መጀመሪያ አካባቢ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመዉን ወንጀል ለሄጉ ፍርድ ቤት መረጃዎችን ለማቅረብ ግሎሪያ እና ሁለት ባልደረቦቻቸዉ እማኞችን ለማነጋገርና ወደማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ባንጊ ተጉዘዋል። በማዕከላዊ አፍሪቃ ዳግም የዛሬ ሁለት ዓመት ተጨማሪ አለመረጋጋት ተቀስቅሶ ሲቪል ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ተፈፅሟል። የጦር ወንጀል ተመልካች ዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤቱም ዳግም ጉዳዩን ተመልክቷል። ግሎሪያ ወደዚያ ሲያቀኑ ታዲያ የስነልቡና ባለሙያም አስከትለዉ ነዉ ነበር።

«ወደፍርድ ቤት ሄደዉ ምስክርነታቸዉን እንዲሰጡ እማኞቹ በስነልቦናእና በአካል ብቁ መሆናቸዉን እርግጠኛ መሆን አለብን።»

የስነልቡና ባለሙያዋ የጥቃት ሰለባዎቹ ማንነታቸዉ ሳይገለፅ ደህንነታቸዉ ተጠብቆ መረጃዎቹን መስጠት እንደሚችሉ በመግለጽ ካበረታቷቸዉ በኋላ አንዷ የገጠማትን ፊቷ ተከልሎ ገለጸች።

«ወደቤታችን መጡ። ሶስት ወንዶች ነበሩ። ከመካከላቸዉ ሁለቱ ባለቤቱን መሬት ላይ ደፍተዉ በመጫን በያዙት መሳሪያ አስፈራሩት። ሶስተኛዉ እኔን አስገድዶ ደፈረኝ። ሁሉም በተመሳሳይ ከፈፀሙ በኋላ በታችናዉ የሆዴ ክፍል ከፍተኛ ህመም ተሰማኝ። በጣም አስከፊ ነበር።»

ቀጠለችና የጥቃት ተጎጂዋን ይህ ድርጊት በዐይነ ልቡናዋ ተቀርጾ እንደሁ የስነልቡና ባለሙያዋ ጠየቀች። እሷም።

Gloria Atiba-Davies
ግሎሪያ አቲባ ዴቪስምስል Sonja Heizmann

«እረፍት ሳገኝና ቁጭ ስል ሁኔታዉ ሁሉ ዳግም በሀሳቤ እየመጣ አየዋለሁ።»

እማኞቹን የመጠየቁ ሂደት ወደሁለት ሰዓት ገደማ ፈጀ። ICC እያንዳንዱ ምስክርነት አሳማኝ እንዲሆን ይፈልጋል ይላሉ ግሎሪያ። ያን ለማድረግ ደግሞ እማኞቹን ወደዚያ መዉሰድ ግድ ሊሆን ይችላል። ይህን ግን ለእማኞቹ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ነዉ የሚናገሩት።

«በምንሠራዉ ነገር ሁሉ የጥቃት ሰለባዎቹን ፍላጎትና ደህንነት ግምት ዉስጥ ማስገባት ይኖርብናል። አንዳንዶቹ ከመንደራቸዉ እንኳ ወጥተዉ አያዉቁም፤ ከመንደራቸዉ ቢወጡም እንኳን ከአካባቢያቸዉ ወይም ከሀገራቸዉ ርቀዉ ተጉዘዉ አያዉቁም። እናም እንዴት ነዉ ይፋ ሊወጡ የሚችሉት? በዚያ ላይ በችሎት ላይም ይህን ምስክርነታቸዉን ወይም ቃላቸዉን እንዲሰጡ ከተደረገ ዳግም ሰቀቀን አይሆንባቸዉም?»

Logo Internationaler Strafgerichtshof

ግሎሪያና የስነልቡና ባለሙያዋ ከምስክሮች ጋ ስለገጠሟቸዉ ጉዳዩች በየጊዜ ይነጋገራሉ። የተፈፀመዉ ወንጀልና የተጎጅዎችን ብዛት ሲመለከቱም ስንቱን አነጋገግረዉ እንደሚዘልቁት ሲያስቡት ይደነቃሉ። ግን ደግሞ የተጠቂዎቹ ጉዳይ አደባባይ እንዲወጣና ተጠያቂዎቹ ተገቢዉን ቅጣት ተቀብለዉ ሰለባዎቹ እፎይ ሲሉ ለማየት በማሰብ ተጠናክረዉ ሥራቸዉን ይቀጥላሉ። የዛሬ ስድስት ዓመት ግሎሪያ ምስክሮቹን ወደፍርድ ቤቱ አምጥተዉ ነበር። እንዲያም ሆኖ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም አንስቶ ፍርድ ቤቱ ዉሳኔዉን አልሰጠም። እስካሁን ጥፋተኛ የተባሉት ሁለት ብቻ ናቸዉ።

ራሳቸዉ የ59ዓመቷ ግሎሪያና ቤተሰባቸዉ ከሴራሊዮን የእርስ በርስ ጦርነት ለጥቂት የተረፉ ናቸዉ። በሀገራቸዉ መፈንቅለ መንግሥት ሲካሄድ እሳቸዉ ስዊድን ዉስጥ አዉደጥናት ላይ ነበሩ። ብቻቸዉን የሚያሳድጓቸዉን ሶስት ልጆቻቸዉን ለማዉጣት እጅግ ተቸግረዉ ነበር። ከ18 ወራት በኋላ ግሎሪያና ልጆቻቸዉ ጋምቢያ ዉስጥ ተገናኙ። በተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ርዳታም ከነልጆቻቸዉ ወደኒዉዮርክ ሄዱ። አሁን በየጊዜዉ የICCን ደረጃዎች እየወጡ የጀመሩትን የወንጀል ምርመራ ተግባር ቀጥለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ